>
4:42 pm - Sunday January 16, 2895

«የሀሮምሳ ፊንፊኔ»  ነበር. . .( አቻምየለህ ታምሩ)

«የሀሮምሳ ፊንፊኔ»  ነበር. . . 
አቻምየለህ ታምሩ
ሐጂ ጃዋር መሐመድ የሚመራው የኦ.ኤም.ኤን. ቴሌቭዥን «ሀሮምሳ ፊንፊኔ» የሚባል ማኅበር ምስረታን አስመልክቶች የተዘጋጀን «የፊንፊኔ የኦሮሞ የወጣቶች» ውይይት «እናቀርባለን» ሲል ሰንብቶ በትናንትናው እለት  የውይይቱን የተወሰነ  ክፍል አስተላልፎ ነበር። «የአዲስ አበባ ተወላጅ  ኦሮሞዎች»   አደረጉት ተብሎ በቀረበው «ውይይት» ላይ  የተነሱ  ትርክቶች   ትችት ሊቀርብባቸው ስለሚገባ  የተወሰኑ ነገሮች ላይ አስተያየት ለመስጠት እነሆ ብዕሬን አነሳሁ 🙂
የማኅበሩ መጠሪያ የሆነው «ሀሮምሳ ፊንፊኔ»  ፍቺው ፊንፊኔን ወደ ነበረችበት መመለስ ማለት እንደሆነ ተነግሯል።  ስለዚህ «ሀሮምሳ ፊንፊኔ» የሚባለው ማኅበር ተግባር ፊንፊኔን ወደነበችበት መመለስ ነው። ይህ ምን ማለት ይሆን?
ከዚህ በፊት ታሪክ ጠቅሰን እንዳቀረብነው ፊንፊኔ የዛሬው አዲስ አበባ አይደለም። ፊንፊኔ የሚለውም ቃል አማርኛ እንጂ ኦሮምኛም  አይደለም። ትርጉሙም ፊን ፊን  አለ ከሚል የተወሰደና  ፍልውሃ ማለት ነው። ፊንፊኔ የሚለው ቃል  ፍቺም  ፍል ውሃ  እንደሆነና ይህም  የዛሬ ፈጠራ  አለመሆኑን  የታሪክ ማስረጃ የሚፈልግ ቢኖር ዶሴ መምዘዝ እንችላለን።
ፊንፊኔ የሚለው ቃል  ትርጉሙ ፍል ውሀ ወይንም በፈረንሳይኛ  source chaude ማለት እንደሆነ ከነገሩን  አሳሾች  መካከል ከንጉሥ ሣህለ ሥላሴ ጋር እ.ኤ.አ. በ1830ዎቹ በቦታው አልፎ ዛሬ አራዳ ጊዮርጊስ በተሰራበት ቦታ  በግራኝ ዘመን የፈረሰን  የማርያም ቤተ ክርስቲያን የጎበኘው ፈረንሳዊው  ተጓዥ  ቴዎፍሎስ ልፌቭረ አንዱ ነው።  በነገራችን ላይ ዛሬ ፊንፊኔ ወይንም ፍል ውሀ እየተባለ የሚጠራው ቦታ ከግራኝ  ወረራ በፊት በግዕዝ ስሙ  «ማይ ሕይወት» እየተባለ ይጠራ ነበር።  ስለዚህ ማይ ሕይወት፣ ፊንፊኔ፣ ፍል ውሃ ሶስቱም   አዲስ አበባ የሚገኘው የተፈጥሮ ምንጭ ስያሜዎች  ናቸው።
«ሀሮምሳ ፊንፊኔ» የተባለው አዲሱ «የአዲስ አበባ  ኦሮሞዎች» ማኅበር   የተቋቋመው ፊንፊኔን ወደነበረችበት ለመመለስ ነው ተብሏል። ጥሩ! ግን   ማኅበሩ «ፊንፊኔን ወደነበረችበት መመለስ»  ሲባል ከግራኝ ወረራ በፊት  በግዕዝ  ቋንቋ ሲጠራበት ወደነበረበት  ወደ «ማይ ሕይወት» ነው የሚመልሳት? ይህ ከሆነ ደግሞ በዚያ ዘመን ቦታው  ኦሮሞም የኦሮሞ መሬትም አልነበረም! ነው ወይንስ ማኅበሩ ፊንፊኔን  ከግራኝ ወረራ  በኋላ በቦታው በተገኘ የቤተ ክርስቲያን ፍርስራሽ ዙሪያ ተሞልቶ ወደነበረ ዳዋ ነው የሚመልሳት?
አዲስ አበባ  እንደገና በተቆረቆረች በ20 ዓመቷ ወደ አዲስ አበባ የመጡ  ያሬድ ገብረ ሚካኤል የሚባሉ ሰው በ1958 ዓ.ም. «ኑ  በዝና አዲስ አበባ» በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፍ እሳቸው አዲስ አበባ በገቡበት ወቅት  እንኳ ማለትም በ1900 ዓ.ም. አካባቢ ዛሬ ፊንፊኔ ወይንም ፍል ውሃ የሚባለው አካባቢ  ወባ መራቢያ፣ ብዙ ሰውም  ወባ እየተያዘ ያልቅበት የነበረና ከተማው እስኪሰለጥን ድረስ  ብዙ ሰው በወባ እየተዘ ይሞት እንደነበር  የአይን ምስክርነታቸው ጽፈዋል። ፊንፊኔን ወደነበረችበት ለመመለስ የተቋቋመው «የሀሮምሳ ፊንፊኔ» ማኅበር «ፊንፊኔን ወደ ነበረችበት መመለስ» ሲለን ሰው ወደማይኖርበትና  ወባ ይራባበት ወደነበረበት ውድሞ መመለስ ማለቱስ ይሆን?  ይገርማልኮ እናንተዬ!
በኦ.ኤም.ኤን. በተላለፈው የሀሮምሳ ፊንፊኔ ምስረታ ውይይት በብዛት ስትናገር የነበረች አንድ ስሟ ያልተጠቀሰ ቆንጆ ልጅ አለች። ልጅቷ አዲስ አበባ እንደተወለደችና በአማርኛ አፏን እንደፈታች ትናገራለን። ይህን ከተናገረች በኋላ በኦሮምኛ እንድትማር ባለመደረጓ ጭቆና እንደደረሰባት ትናገራለች። ይቺ ቆንጆ ልጅ ጥላቻ ያስተማሯት የፖለቲካ ነጋዴዎች ሰለባ ነች። የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ሕግ ወይንም በተለምዶ  «የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት» ምክረ ሀሳብ [recommendation]  ሕጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ ይደነግጋል። የመንግሥታትም ኃላፊነት ሕጻናትን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ ማድረግ ነው። በኛ አገር ግን ፖለቲካው የጥላቻ ስለሆነ «ሕጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማር አለባቸው» የሚለው የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት ምክረ ሀሳብ  «ሕጻናት  [አፋቸውን ባልፈቱበት] በብሔራቸው ቋንቋ መማር አለባቸው» በሚል ተወስዷል።  ሀሮምሳ ፊንፊኔ ላይ ቀርባ የተናገረችዋ ቆንጆ ልጅ የመንግሥት ግዴታ አፏን በፈታችበት ቋንቋ እንድትማር ማድረግ እንጂ «በብሔሯ» ቋንቋ እንድትማር ማድረግ የመንግሥት ግዴታ አለመሆኑን ስለማታውቅ አለማወቋን በአደባባይ እያሳወቀች መሆኗን አታውቅም።
ከማኅበሩ ጀርባ ያሉ የፖለቲካ ነጋዴዎች አብዛኛዎቹ አውሮፓና አሜሪካ ልጆች የወለዱ ዲታዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ልጆቻቸው አፋቸውን የፈቱት በየሚኖሩበት አገር ከተማ ባለው ቋንቋ ነው። ልጆቻቸውንም የሚያስተምሩት አፋቸውን በፈቱበት ቋንቋ ነው። ለተከታዮቻቸውን ግን  «ሕጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማር አለባቸው» የሚለውን  የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት  ምክተ ሀሳብ  እየጣሱ  አፋቸውን ባልፈቱበት በብሔራቸው ቋንቋ  ስላልተማሩ ጭቆና እየተደረገባቸው እንደሆነ አድርገው ይሞሏቸዋል። በኦሮምኛ አፋቸውን የሚፈቱ የአማራ ልጆች መማር ያለባቸው አፋቸውን በፈቱበት በኦሮምኛ ነው።  ሌላውም እንደዚያው መሆን ይኖርበታል። ይህ  የተባበሩበት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት  በወላጆችና በመንግሥታት ላይ የሚጥለው ኃላፊነት ነው።
በአማርኛ አፌን ፈትቼ  በብሔሬ ቋንቋ  በኦሮምኛ ያልተማርሁት ጭቆና ስለሚደረግብኝ ነው፤ በኦሮምኛ ቋንቋ አፉን ፈትቶ  በብሔሬ ቋንቋ በአማርኛ ያልተማርሁት ጭቆና ስለሚደረግብኝ ነው የሚለው ድንቁር፣ ጥላቻና የእውቀት ጾመኛነት ነው። እያንዳንዱ ሰው ከአፍ መፍቻ ቋንቋው ውጭ ባለ በብሔሩም ይሁን በሌላ የውጭ ቋንቋ መማር ቢፋልግ በራሱ ይማር አልያም ወላጆቹ ያስተምሩት  እንጂ መንግሥት ሕጻናት አፋቸውን ባልፈቱበት ቋንቋ የማስተማር ግዴታ የለበትም። ስለሆነም ሕጻናት አፋቸውን ባልፈቱበት በብሔራቸው ቋንቋ አለመማራቸው በምንም መልኩ ጭቆና ሊሆን አይችልምና የማያውቁ ልጆችን ጥላቻ አትሙሏቸው!
በሀሮምሳ ፊንፊኔ ውይይት ላይ ከተናገሩት ወንድ ወጣቶች መካከል አንዱ የተናገረው በጣም የሚገርም ነው። እንዴት አይነት ቤተሰብ ቢያሳድገው ነው የሚያሰኝ ነው። ፊንፊኔን አዲስ አበባ፤ ቢሾፍቱን ደብረዘይት፤ አዳማን ናዝሬት ብሎ ለማይጠራ ሰው መልስ አልሰጥም አይነት መልዕክት  ያዘለ ንግግር በዚህ በ21ኛ መቶ ክፍለ ዘመን አድርጓል።  ይህ ወንድሜ ቋንቋ መግባቢያ መሆኑን፣ ኦሮምኛ መናገር ኦሮሞ እንደማያደርግ፤ አማርኛ መናገር አማራ እንደማያደርግ የነገረው ሰው የለም። ለዚህ ልጅ ኦሮሞ ማለት አዲስ አበባን ፊንፊኔ፤ ደብረ ዘይትን ቢሾፍቱ፤ ናዝሬትን አዳማ ብሎ የሚጠራ ሰው ብቻ ነው።  ባገራቸው የተካሄደው  የጎሳ ፖለቲካው ሐሳብ ከማቀጨጩ  አልፎ  ገና በለጋ እድሜያቸው እንደዚህ አይነት  ልሙጥና በጥላቻ  ዝቅጠት ውስጥ የወደቁና ወደፊት ሊራመዱ የማይችሉ ለጋ ልጆችን መቅጨቱ እጅጉን የሚያስቆጭ ነው።
ከቀረበው ውይይት ተሰብሳቢዎች መሠረት ያለው ቁም ነገር ሲያነሱ አላየሁም። ከሌላው ለመለየት ካልሆነ  በስተቀር  አዲስ አበባ ውስጥ የሚኖር አፉን በአማርኛ የሚፈታ የኦሮሞ ልጅ  በቀሪው አዲስ አበቤ የተለየ ጭቅና የለበትም።  በውይይቱም  የተመለከትሁት እዚህና እዚያ ሲነሳ የነበረው ትርክት  በፌስቡክና በብሔርተኛ ሜዲያዎች ሲባል የሰሙበትን  ቅራቅንቦ  ለቃቅመው   እንደ እውቀት  የሚያወሩና  እነሱና እኛ የሚል ብሽሽቅ  ውስጥ የገቡ ወጣቶችን ነው።
አንዷ ቆንጆ ልጅ ተነሳችና «ኦሮሞ ነኝ ስላቸው  ኦሮሞኮ አትመስይም» ይሉኛል እያለች ትናገራለች። ይቺ ልጅ ይህንን አይነት ነገር በተደጋጋሚ ሲነገር  ስለሰማች በማንነቷ  ላይ የደረሰባት ነቀፌታ አድርጋ  ወስዳዋለች። «አንተኮ አማራ አትመስልም» ፤ «አንቺኮ  ጉራጌ አትመስይም» ወዘተ በሚል የሚተረቡ ሌሎች ሚሊዮኖች እንዳሉ የሞሏት ሰዎች አልነገሯትም። ይህም ከተሜነት የፈጠረው እንጂ የማንነት ጥላቻ እንዳልሆነ አታውቅም። ምናልባትም ኦሮሞ አትመስይም ያላት ሰውኮ ራሱ ኦሮሞ ሊሆን ይችላል።  እኔን ራሴን ከየት እንደሆንሁ ሲጠይቁኝ «ከጎጃም»  ስል ፤«ጎጃሜ አትመስልም» ያለኝ  ስንቱ ነው?!  ሆኖም ግን  ይህን  አንድም ቀን ጎጃሜ ስለሆንሁ፤ ወይንም አማራ በመሆኔ እንዲህ ተባልሁ ብዬ ሰዎች በጨዋታ መሀል ያነሱትን ማንኛውንም «ተረብ»   ፖለቲካ አድርጌው አላውቅም!
እንግዲህ!  “ተው ማነህ ተው ማነህ የተኛ ሰው አለ ትቀሰቅሳለህ” የሚል የኢትዮጵያ ተረት አለ።  ይህ  የኛ ብቻ ነው  የሚለው አባዜ   የበለጠ  የኛ ነው የሚል  በጣም ከፍተኛ ሕዝብ አለና ተዉ የተኛ ሰው አትቀስቅሱ፤ ያ ቢነሳ  ደግም  አይደል!  «ሀሮምሳ ፊንፊኔ» የሚለው  ጸብ አጫሪነት ሲጀመር «ሀሮምሳ ኢትዮጵያ» የሚል  እንቅስቃሴ  ይከተልና ኦሮሞም  ከግራኝ በፊት  ወደነበረበት Bar’ gama ይመለስ  የሚል ግብረ መልስ ሊከተል  እንደሚችል እንዴት ማሰብ ይናሳል?
በስተመጨረሻ ዶክተር ከበደ ሚካኤል «የእውቀት ብልጭታ»  በሚለው የሞራል  መጽሐፋቸው ጥላቻን፣ ስግብግብነትን፣ብልጠትንና ተንኮልን ያለመጠን ማብዛት የኋላ ኋላ በራስ አንገት ላይ እባብ እንደመጠምጠም እንደሆነ  የሚመክሩበትን ጋብዤ ልሰናበት. . .
መርዝም መድሃኒት ነው ሲሆን በጠብታ፣
እንዲሁም ለተንኮል አለው ቦታ ቦታ፣
ምን ቢሰለጥኑ ቢራቀቁ በጣም፤
ሁልጊዜ ደጋግሞ ብልጠት አያዋጣም፤
በጅ የተበተቡት ተንኮል ዞሮ ዞሮ፣
ማጋለጡ አይቀር እጅና እግር አስሮ፤
መጽሓፉም ይለናል ሲያስተምረን ጥበብ፣
ብልጥ ሁን እንደባብ የዋህ ሁን እንደርግብ፤
ስለዚህ በብልጠት ተንኮል ስትሰሩ፣
በዝቶ እንዳይገላችሁ ገርነት ጨምሩ።
Filed in: Amharic