>
9:47 am - Wednesday November 30, 2022

ለውጡ በሕዝብ ለሕዝብ ወይስ ለወያኔ/ኢሕአዴግ (ከይኄይስ እውነቱ)

 

ለውጡ በሕዝብ ለሕዝብ ወይስ ለወያኔ/ኢሕአዴግ

 

ከይኄይስ እውነቱ

 

ካለፉት 6 ወራት ጀምሮ በኢትዮጵያ የታየው ጅምር የለውጥ ሂደትና አንፃራዊ ነፃነት የተገኘው የኢትዮጵያ ሕዝብ (ሕፃናት፣ ሴቶች እናቶቻችንና አረጋውያን ጭምር) የሕይወትና የአካል መሥዋዕትነት ከፍሎበት ነው፡፡ የወያኔ ትግሬና ለሱ ያደሩለት አሽከሮች አገዛዝ ሊመጣ ካለው የሕዝብ የቁጣ ማዕበል የተረፈው አሁን የጅምር ለውጡን ሂደት እየመሩ ያሉና ከሕወሓት ባርነት ራሳቸውን ነፃ ባወጡ ጥቂት የወያኔ/ኢሕአዴግ አባላት  – የለማ ቡድን በሚባለው – መሆኑ ይታወቃል፡፡ በዚህም ምክንያት ለውጡ በዚህ ‹አገር አጥፊ ወንጀለኛ ድርጅት› ማዕቀፍ የሚካሄድበት መራር እንቆቅልሽ ተፈጥሯል፡፡ ለጊዜው የአገራችንን ህልውና ከማስቀደም አኳያ የለውጥ አመራር ኃይል የተባለው ደረጃ በደረጃ የሕዝብን ጥያቄ – ከዘር ፖለቲካና ካስከተለው ጥፋት ወጥተን የሕዝብ ሉዐላዊነት የሚረጋገጥበት ዜግነትን መሠረት ያደረገ መንግሥተ ሕዝብ መመሥረት – እንዲመልስ ነው፡፡ በለውጡ አመራር ቡድን በመጀመሪያዎቹ  3 ወራት የተወሰዱ በጎና አበረታች ርምጃዎች ለመሠረታዊው የለውጥ አጀንዳ መንገድ ጠራጊ ውሳኔዎች እንጂ በራሳቸው መሠረታዊ ለውጦች አይደሉም፡፡ ከመጀመሪያዎቹ 3 ወራት በኋላ የጅምር ለውጡ ሂደት የኋልዮሽ ጉዞ የጀመረ ይመስላል፡፡ መንግሥትን እመራለሁ የሚለው የለውጥ ኃይል የአገርን ሰላምና ፀጥታ፣ የሕዝብን ደኅንነት ለማስጠበቅ ባለመቻሉ ጥያቄው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ሂደት ጭማሪና እመርታ እያሳየ ነው የሚለው ቀርቶ አገር እንዳትረጋጋ ለውጡን ለመቀልበስ የሚታገሉ ሽብርተኞችን (ወያኔ ትግሬና ተረፈ-ወያኔዎችን) የማስታመም ሥራ ውስጥ ተገብቷል፡፡ ዛሬም ሕዝብ ያመጣው ለውጥ የተንጠለጠለው በግለሰቦች በጎ ፈቃድ ላይ እንጂ በተቋማት፣ በሕግ፣ በፖሊሲ፣ በመዋቅር፣በሥርዓት ዝርጋታ የተደገፈ አይደለም፡፡ ወንጀለኞች ባደባባይ በነፃ ከመፈንጨታቸው አልፎ በዝርፊያ ባካበቱት አገራዊ ሀብትና የፓርቲና መንግሥታዊ መዋቅሮችን በመጠቀም ሕዝብን እያሸበሩ አገርን እየናጡ ይገኛሉ፡፡

አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎችና ብዙኃን መገናኛዎችም የለውጡ ኃይሎች ባንድ በኩል በወያኔ ትግሬ በሌላ በኩል በጽንፈኛ ጎሠኞች ዙሪያውን ተወጥረው ስለሚገኙ ተዉ ዝም በሉ፤ የሚያደርጉትን በትእግስት እንጠባበቅ ይላሉ፡፡ ከዚህም አልፈው ከለውጡ ኃይሎች ውጭ ምንም አማራጭ የሌለና እነሱ በሌሉበት ኢትዮጵያን ለማሰብም አይቻልም፤ ብቸኛ አዳኛችን÷ አሻጋሪያችንም እነሱ ናቸው፤ እነሱ ላይ ሙሉ እምነታችንን ጥለን ‹እናግዛቸው› ይሉናል፡፡ የተሟላው አገራዊ ሥዕልና ዕውነት ይሄ ነው ወይ? እገዛው በምን እንደሆነም አልገባኝም፡፡ የተመቻቸ ሁኔታስ አለ ወይ? እገዛውም እኮ የፓርቲ ግንኙነትና የጎሣ መስመር የሚጠይቅ ይመስላል፡፡ እነዚህ የለውጥ ኃይሎች በተለይ ካለፉት 3 ወራት ጀምሮ በቃላቸውና በድርጊታቸው ለለውጡ ባለቤት ሕዝብ ታማኝ ሆነው ተገኝተዋል ወይ? እስከ መቼ ሕዝብ በነሱ ታምኖ ባንድ ወገን የአገሩን ህልውና ለማጥፋት ሲታገል በኖረና አሁንም በዚሁ የጥፋት ተልእኮው የቀጠለ፤ በሌላ ወገን ሕይወታችንን፣ አካላችንንና ቤት ንብረታችንን (የኑሮ ዋስትናችንን) ባሳጣን፤ መሠረታዊ አገልግሎት (ውኃና ኤሌክትሪክ) ሲነፍገን በኖረና አሁንም አለተጠያቂነት እነዚህን አገልግሎቶች ማቅረብ ላልቻለ ነውረኛ ድርጅት አሳልፈው ይሰጡናል? መሠረታዊው ጥያቄ እነ ዐቢይ ከዚህ ነውረኛ ድርጅት ፈቃድ ውጭ መፈጸም የሚችሉት ጉዳይ አለ ወይ? እነ ዐቢይ ከሕዝብ ይልቅ ለነውረኛ ድርጅታቸው ሲታመኑና ለአገርም ለለውጡም የማይጠቅሙ ውሳኔዎች ሲያስተላልፉ መንቀፍ መተቸት በተፃራሪ የቆመውን አገር አጥፊና ለውጥ ቀልባሽ ኃይል እንደ መደገፍ ወይም ለነዚህ የጥፋት ኃይሎች ዱላ እንደማቀበል ተደርጎ ለምን ይቆጠራል? ወያኔ ትግሬና ሌሎች ጽንፈኛ ጎሠኞች/መንደርተኞች በማኅበራዊው ብዙኃን መገናኛ በርካታ የጥፋት ሠራዊት አሠማርተው ግጭት አቀጣጣይ÷ መርዘኛ ÷ ዘርን መሠረት ያደረጉ የጥላች ንግግሮችንና ጽሑፎችን እንዲሁም መሠረተ ቢስ የሐሰት መረጃዎችን በመልቀቅ ውዥንብር እየፈጠሩ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ባንፃሩም የነዚህ ቡድኖች ተቃዋሚ ነኝ የሚለው ወይም ሚናው በውል የማይታወቅ ክፍል በማን አለብኝነት መፍትሄ ሰጭ ከሆኑ ይልቅ በዘር ቆጠራ ላይ ያተኮሩ÷ ያልታረሙ÷ ከማነፅ ይልቅ የሚያፈርሱ÷ አንዳንዶቹም የአገር ህልውና አደጋ ላይ መሆኑን እስከነጭራሹ ዘንግተውት ተራ የልጆች ብሽሽቅ ውስጥ የገቡ÷ ስለሚናገሩት/ስለሚጽፉት ጉዳይ ዕውቀቱም ልምዱም ሳይኖራቸው ከማን አንሼ መንፈስ እየዘባረቁ ከጨለማው ወገኖች ያልተናነሰ ጥፋት እያደረሱ እንደሚገኙም በሚገባ እናውቃለን፡፡

ሆኖም ለዐቢይና ቡድኑ የቅርብም የሩቅም፣ አንዳንዴም ግምታዊና መሠረት የሌለው፣ አንዳንዴም ስልትና ብልሃት የሚል  ምክንያት እየደረደርን ከለውጡ ሀዲድ እየወጡ ሲጓዝ ዝም ማለቱ ለጨለማው ወገኖች እንጂ ለአገርና ሕዝብ የሚጠቅም አይመስለኝም፡፡ ነገሮች አንዴ ከእጅ ካፈተለኩ በኋላ መጯጯኹ ጅብ ከሄደ ዓይነት ጩኸት እንዳይሆን ከፍተኛ ሥጋት አለኝ፡፡ አገራዊ ለውጥ በግለሰቦች ላይ ባለን እምነት ከታሰበው ግብ ይደርሳል ማለት ቅዠት ነው፡፡ ያውም እንደ ኢትዮጵያ እጅግ ውስብስብ ችግሮች ባሉባት አገር፡፡

የዐቢይ አገዛዝ እውን ከሚመራው ድርጅትና የግል ፖለቲካ ሰብእና በላይ ለአገርና ለሕዝብ ቅድሚያ የሚሰጥ ከሆነ፤ ሕግና ሥርዓትን በማስከበር የሕግ የበላይነትን ለማሰፈን ፍላጎት ካለው፤ ኢትዮጵያውያን ባገራቸው ኹለንተናዊ ሕይወት (ፖለቲካውን ጨምሮ) የሚያደርጉት ተሳትፎ ጎሣ/ነገዳቸውን እንዲሁም የድርጅት/ፓርቲ አባልነታቸውን በመምዘዝ ሳይሆን በዜግነታቸው÷ በብቃትና ችሎታቸው÷ በቅንነትና በሞራል ልዕልናቸው ከሆነ፤ እንደፉከራው ሕግን የማስከበር አቅም ካለው፤ እስካሁን ባደባባይ የተናገራቸውና የገባቸው ቃሎች ንግግርን ከማሳመር (ሬቶሪክ) አልፈው ከልቡ ከሆነ፤ ሊያሻግረን የሚፈልገው የጎሠኝነትን ሳይሆን የዜግነትን ፖለቲካ ይዞ ከሆነ፤ ቢያንስ የሚከተሉትን ርምጃዎች መውሰድ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

1/ ባስቸኳይ አገራዊ ጉባኤ መጥራት (ይህንን ጥሪ ለሁለተኛ ጊዜ ያነሳሁት ሲሆን፣ ዝርዝሩንና አስፈላጊነቱን በቀደመ አስተያየቴ ስላመለከትኹ ጽሑፉን በሚከተለው አድራሻ ማግኘት ይቻላል፡፡) https://www.ethioreference.com/archives/14361

2/ የለውጥ ቀልባሽ ኃይሎችን/ሽብርተኞችን በሕግ ቊጥጥር ሥር ማዋል፤

3/ በየግዛቱ በፓርቲ/ድርጅት ቊጥጥር ሥር የሚገኙና ከሕገ ውጭ የተደራጁ ‹ልዩ ኃይሎችን› በሥርዓት ማፍረስ፤

4/ በአዲስ አበባ ወጣቶች ላይ የተፈጸመውን ሕገ ወጥ ድርጊት በይፋ በማውገዝና ይቅርታ በመጠየቅ በዚህ ውንብድና ተግባር የተሳተፉ ባለሥልጣናትን በሙሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ ከማድረጉ በተጨማሪ ከቦታቸው ማንሳት፤ ወጣቶቹን በሚመለከት ማናቸውም ዓይነት ወያኔያዊ ድራማ በብዙኃን መገናኛ ሳይደረግ ጤንነታቸውን በማረጋገጥ በካሣ መልክ ችሎታቸው በሚፈቅደው ሥራ እንዲሠማሩ ማድረግ፤

5/ በዐቢይ አገዛዝ ሁለቴም የተደረጉት የካቢኔ አባላት ስየማዎች የወያኔ ትግሬን የጎሣ ተዋጽዖ እና የፓርቲ አባልነት መሥፈርትን ሙሉ በሙሉ መሠረት ያደረገ (አልፎ ተርፎም የለውጡ ቀልባሽ ኃይሎች የተካተቱበት) በመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ በለውጥ ኃይሎች የመከዳት ድርጊት አድርጎ ወስዶታል፡፡ ይህም ብቻ አይደለም ሕዝብ በደም መሥዋዕትነት ያመጣው ለውጥ ለደም አፍሳሾቹ መሾሚያና መሸለሚያ መሆኑ እጅግ አስቆጥቶናል፤ አሳዝኖናልም፡፡

6/ ዝርፊያን ሌብነትን መጸየፍ፣ ማውገዝ በጎና አንድ ነገር ሆኖ፤ የሕዝብ ሀብት አሁንም በዘራፊዎች እጅ ሆኖ በዝምታ መመልከትና ከዘራፊዎች መካከል አንዱ የሆነውን ወያኔ ባደባባይ ማወደስ ግን በፍጹም ተቀባይነት የለውም፤ ሀብትና ንብረቱን ለባለቤቱ ሕዝብ የማስመለሱ ተግባር አመቺ ጊዜ እየተጠበቀ ነው የምንል ከሆነ ቢያንስ አሁንም በሕዝብ ሀብት ላይ ሠልጥነው የሚፏንኑ የወያኔ ትግሬ ባለሥልጣናትን (ለምሳሌ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያለ ብሔራዊ መለያችን የሆነ ተቋምን የግል ይዞታው አድርጎ የሚደነፋውን ተወልደን) በሚያስደነግጥ ዝምታ ማለፉና ለፍርድ አለማቅረቡ የለውጥ ኃይሉን ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ ካስገቡ በርካታ ጉዳዮች አንዱ ይመስለኛል፡፡

7/ አገር በአራቱም ማዕዝናት እየተናጠች ባለችበት በዚህ ቀውጢ ሰዓት፤ በግብር ከፋዩ ሕዝብ እና በመንግሥት ሀብትና ንብረት በመጠቀም በወያኔ/ኢሕአዴግ ሲደረጉ የቆዩ የውሸት ምርጫዎችን በማጭበርበሪያ መሣሪያነት ሲያገለግሉ የነበሩና አሁንም ያሉ፣ ከላይ እስከ ቀበሌ ድረስ የተዋቀሩ የፖለቲካ አደረጃጀቶች (የኮሙኒኬሽን ጽ/ቤቶች መዋቅር ጨምሮ) ሳይፈርሱና መፍረሳቸውም ለሕዝብ በይፋ ሳይገለጽ፤ አሁንም የመንግሥትና ፓርቲ ሚና በትክክል ተሰምሮ ባልተለየበት፤ ምርጫውን ነፃ፣ ገለልተኛ፣ ተአማኒና ፍትሐዊ ለማድረግ የሚያስፈልጉ ተቋማትና ሕጋዊ ማዕቀፎች – ለአብነት ያህል ምርጫ ቦርድ፣ ፍ/ቤቶች፣ መንግሥታዊ ብዙኃን መገናኛዎች፣ ወዘተ. – ገና በጅምር ሂደት ላይ የሚገኙ መሆናቸው፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በፈለጉት የኢትዮጵያ ግዛት ተንቀሳቅሰው ለመሥራት – በይፋ ክልከላና በጽንፈኛ ጎሠኞች ዛቻና የጥላቻ ቅስቀሳ ጭምር – በማይችሉበት ሁናቴ፤ ሀገር አቀፍ ምርጫው ወያኔ/ኢሕአዴግ ባስቀመጠው ከአንድ ዓመት ተኩል የማይበልጥ የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ እንዲካሄድ በነዐቢይ ጭምር መታሰቡ የተለመደውን የይስሙላ ‹ምርጫ›  ለማደረግ ካልሆነ በየትኛውም መመዘኛ ትክክል አይደለም፡፡ ስለሆነም ምድር ላይ የሚገኘውን ጽድቅ ባገናዘበ መልኩና ከተቃዋሚዎች ጋር በሚደረግ ስምምነት ምርጫውን ‹በቂ› ተብሎ ለሚታሰብ ጊዜ ማራዘሙ ተገቢ ነው፡፡

8/ ከውጭም (በተለይ ከኤርትራ) ሆነ ከውስጥ ኃይሎች ጋር የተደረገና ወደፊትም የሚደረግ ስምምነት ይፋ በማድረግ መንግሥታዊ አሠራር ግልጽና ተጠያቂነት ያለበት መሆኑን ማሳየት ግዴታ ከመሆኑም በተጨማሪ ለለውጡ ኃይል ተአማኒነት መሠረት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ አለበለዚያ አሁንም እንደ ዘመነ ወያኔ ትግሬ የፓርቲ አገዛዝና ድብብቆሹ ከቀጠለ ‹መንግሥት› ለመኖሩ ምን ማረጋገጫ አለ?

በመጨረሻም የዐቢይ አገዛዝ በሰየመው ‹አዲስ› ካቢኔ አባላትም ሆነ በበድንነቱ በሚታወቀው ‹ፓርላማ› ተስፋ የማደርገው ነገር የለም፡፡ ከፓርቲና ጎሣ ትስስር ውጭ ኢትዮጵያ ጅምር ለውጡን ወደተሻለ ደረጃ ሊያሸጋግሩ የሚችሉ ብሩህ አእምሮ ያላቸው በተለያዩ መስኮች የሠለጠኑ ባለሞያዎች ባገር ውስጥም ሆነ በውጩ ዓለም አሏት፡፡ ዕውነተኛ ለውጥ ከፈለግን ከተቃዋሚ ፓርቲዎችም ሆነ ከዚያ ውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ማሳተፍ ይቻል ነበር፡፡ ለዚህ የሚቀርበው ምክንያት ምን እንደሆነ አይገባኝም፡፡ በፖለቲካም (በለውጥ ሂደትም) ለላቀ ዓላማና የምንፈልገውን ውጤት ለማግኘት የሚያስከትለው አደጋ ሊኖር ይችላል በሚል ፍርሃት/ሥጋት ሳንታሠር የተጠናና በሚገባ የታሰበበት አዲስ አሠራርን መሞከር እንግዳ ጉዳይ አይደለም፡፡ የለውጡ አመራር ለውጡን ካመጣው ሕዝብ ከመተማመን ይልቅ በነውር የታጀለው ድርጅቱ ሥጋት ያመዘነበት ይመስላል፡፡ አሊያም…

በዚህም ምክንያት ጅምር ለውጡ እንደ አጀማመሩ ፍጥነቱን ጠብቆ ወይም እሴቶችን እየጨመረ የሚሄድ አይመስልም፡፡

Filed in: Amharic