>

እየጫራችሁት ያለው እሳት ቀድሞ የሚበላው እናንተኑ መሆኑን እወቁት!!! (ቬሮኒካ መላኩ)

 

እየጫራችሁት ያለው እሳት ቀድሞ የሚበላው እናንተኑ መሆኑን እወቁት!!!
…ቬሮኒካ መላኩ
እነዚህ ሰዎች የአእምሮ መቃወስ ውስጥ ከሆኑ ወደ ህክምና አስገቧቸው ወይም አደብ እንዲገዙ አድርጓቸው!
 
እንግሊዛውያን  ‘Fools rush in where angels fear to tread’ ( ቅዱሳን መላእክት ለመረገጥ የሚፈሩትንና የሚርበተበቱበትን ቦታ ጅሎች ይሯሯጡበታል ፣ይዘሉበታል)  ይላሉ ።
ኢንጅነር ስመኜው በቀለን ያክል የአገሪቱን የመደራደር አቅም ሰማይ ያደረሰ የሜጋ ፕሮጀክት  CEO ደህንነቱን የሚጠብቅለት አንድ ኮስማና አጃቢ እንኳን መመደብ አቅቶት ህይወቱ እንዲያልፍ ያደረገ መንግስት ጃዋር መሀመድ ለሚባል አደገኛ አገር አጥፊ አንድ ጋንታ ጦር አጃቢ መድቦ አገሪቱን ዶግ አመድ የሚያደርጉ ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን እያስጠመደብን  ነው።
 አቶ ጃዋር በህዝቦች መካከል ያለፈ የታሪክ ቁርሾዎችን እያራገበ በብሄር መሀል ልዩነት ከመፍጠር ባለፈ ዛሬ ደግሞ ወደ ሀይማኖት ዙሯል። በሀይማኖት መከፋፈል ስለሚፈልግ ብቻ እና ብቻ ነው ይሄን አጀንዳ ይዞ ብቅ ያለው።
እንዲህም አለ፦
“ፊንፊኔ ላይ ቤተ ክርስቲያኖች የያዙት ሰፋፊ መሬት ቢያንስ በግማሽ ሊቀነስ ይገባል!”
 
ጃዋር መሀመድ ከ አሀዱ ሬድዮ ጋር ባደረጉት ቆይታ ፊንፊኔ የኦሮሞ ገበሬዎችን በማፈናቀል ፋንታ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የያዘቻቸው አላስፈላጊ ሰፋፊ መሬቶችን ለህዝብ ጥቅም በማዋል ላይ ስራ መሰራት እንዳለበት አሳስቧል፡፡ እንደምሳሌም ቦሌ የሚገኘውን መድሀኒያለም ቤተ ክርስቲያን ከ 20 በላይ ህንፃ ሊሰራ እንደሚችልና መንግስት የቦታውን አስፈላጊነት በመረዳት ለቤተክርስቲያኑ ሌላ ተተኪ ቦታ እንዲያመቻች ጠይቋል፡፡
አላማው ግልፅ ነው ልዩነት መፍጠር እነ አብይን ተቀባይነት ማሳጣት ፣ በ አዴፓ እና ኦዴፓ መሀል ልዩነት መፍጠር መከፋፈል ነው።
ይሄ  አስነዋሪ አጉራ ዘለል ግለሰብ እንደለመደው እምነትአልባ የነበረው  ኮሚኒስቱ ደርግ እና ህውሃት እንኳን ያልደፈሩትን  አይነኬ የሆነውን የሀይማኖት ጉዳይ ውስጥ ዘሎ በመግባት  “ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አዲስአበባ የያዘችው መሬት ሰፊ ስለሆነ መነጠቅ አለባት ” በማለት ጦርነቱን ለማስጀመር ፊሽካ ለመንፋት  እየተዘጋጀ ነው።
..
ከላይ በመግቢያዬ የጠቀስኩት የታዋቂው እንግሊዛዊ  ፀሀፊ E. M. Forster   “For fools rush in where angels fear to tread ” መላእክት ለመረገጥ የሚፈሩትን መሬት ቂሎች ይሯሯጡበታል ፣ይዘሉበታል ” የሚለው ድንቅ አባባል ለጃዋር እና ለእነ ታከለ ኡማ  በትክክል የሚሆን ነው።
እነዚህ ሰዎች አይነኬ የሆነውንና  አገርን በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የሚማግድ አደገኛ ቀይ መስመር እያለፉ ነው ።
እኔ አሁን እጅግ Humble (ትሁት) በመሆን የምመክራችሁ  አገር ከመጥፋቱ  በፊት እነዚህ ሰዎች የአእምሮ መቃወስ ውስጥ ከሆኑ ወደ ህክምና አስገቧቸው ወይም አደብ እንዲገዙ አድርጓቸው ።  አንድ ነገር መታወቅ ያለበት  ነገር እሳቱ ከተጫረ በኋላ የተጫረው እሳት መብላት የሚጀምረው ራሳችሁን ነው።
Filed in: Amharic