>

“እነዚህ ሰዎች እንወክለዋለን የሚሉትን ሕዝብ ጨርሶ አያውቁትም”  (ወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን)

“እነዚህ ሰዎች እንወክለዋለን የሚሉትን ሕዝብ ጨርሶ አያውቁትም” 
ወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን
ግድ የላችሁም እነዚህ ሰዎች ሕዝብን ጨርሶ አያውቁትም፡፡ “እነዚህ ሰዎች” ያልኩት የብሔር ፖለቲካ አቀንቃኞችን በጠቅላላ ነው፡፡ ለዚህ አባባሌ ሰበብ የሆኑኝ ግን በተለይ በተቃውሞ ጎራ የተሰለፉትና ዕለት ከዕለት ወደ “አክራሪነት” የብሔር ፖለቲካ አቀንቃኝነት የተሸጋገህሩት ናቸው፡- እንደ ኦቦ በቀለ ገርባ ያሉት፡፡
.
ኦቦ በቀለ ገርባ ከጥቂት ቀናት በፊት ከ LTVዋ ጋዜጠኛ ቤተልሔም ታፈሰ ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ ተከታትዬ ነበር፡፡ ፕሮግራሙን በጥሞና ተከታትዬ ስጨርስ ነው “እነዚህ ሰዎች እንወክለዋለን የሚሉትን ሕዝብ ጨርሶ አያውቁትም” አልኩኝ፡፡ ሕዝቡን ማወቅ ብቻ አይደለም፤ “ሶስት ጊዜ ለካ፤ አንድ ጊዜ ቁረጥ” የሚለውን  ብሒልም አያውቁትም፡፡
.
ይህንን የምለው ካለምክንያት አይደለም፡፡ ኦቦ በቀለ ለሚጠየቁት ጥያቄ ምላሽ ሲያጥራቸው በመታዘቤ ነው፡፡ ኦቦ በቀለ፤ ቀድመው ለተናገሩት ነገር አሳማኝ ማብራሪያ ወይም ማስተባበያ መስጠት አለመቻላቸው ብቻ ሳይሆን፣ “ምክንያት” ብለው የደረደሯቸው ሰበቦች የሚያስተዛዝቡ መሆናቸው ያስገርማል፡፡
.
ለምሳሌ ያህል አንድ ምላሻቸውን ብቻ ልጥቀስ፡፡ ጋዜጠኛዋ “አዲስ አበባ የኦሮሞ ናት” የሚለውን መግለጫ በተመለከተ ማብራሪያ ጠየቀቻቸው፡፡  ኦቦ በቀለ ለመግለጫው ሰበብ ናቸው የሚሏቸውን “የኦሮሞ ብሔር ጥቃት” ደርድረው ሲያበቁ እንዲህ አሉ፡-
“….ከ100 ዓመት በፊት አዲስ አበባ የኦሮሞ ነበረች። ….የማን እንደነበረች እንዲያውቁ ነው…”
.
ይህ ምላሻቸው ገረመኝ፡፡ መገረም ብቻ አይደለም፡፡ ከ5 ስድስት ዓመት በፊት የገጠመኝን ትልቅ ቁምነገር አስታወሰኝ፡፡ ያኔ ወደ ኦሮሚያ ክልል ገጠር የመሄድ ዕድል አግኝቼ ነበር፡፡ እዚያ ካገኘኋች የኦሮሞ አባቶች መሃል በአንደበተ ርቱዕታቸው ያስገረሙኝን አዛውንት ጠጋ ብዬ ጠየቅኳቸው፡፡ ኦሮሚያ ስለሚባለው ክልልና ስለኦሮሞ ብሔር አሰፋፈር፡፡
.
ቃል በቃል ባይሆንም “ክልል የሚባለውን እርሳው” የሚል ዓይነት መልስ ነበር የሰጡኝ፡፡ እናም “ሉከ መሌ ብየ እንቀቡ” የሚል ተረት ነገሩኝ፡፡ “እግር እንጂ ሀገር የለኝም” ማለት ነው ትርጉሙ፡፡ “እግሬ የደረሰበት ሁሉ አገሬ ነው” አሉ እጅግ የረቀቀና የሚያስደምም ማብራሪያ ሰጡኝ፡፡ “ፈጣሪ ለሰው ልጅ ድንበር አልከለለም፤ ወሰን አላበጀም” የሚል አንደምታ የለው ነበር ማብራሪያቸው፡፡
.
በእኚህ አዛውንት ጥልቅ ማብራሪያ የተነሳ (ኦሮምኛ ቋንቋ ባልችልም) አባባላቸውን ልረሳው አልቻልኩም፡፡ አንድ ቀን፣ ከዕለታት አንድ ቀን አባባላቸው በውስጤ ሲብላላ ከርሞ በ“ግጥም” መልክ ፈንድቶ ወጣ፡፡ “ሉከ መሌ ብየ እንቀቡ” የሚል ግጥም ፃፍኩ፡፡
.
ከዚያ ጊዜ ወዲህ ኦሮሞ፣ በተለይም የኦሮሞ አዛውንቶች ጥልቅ አሳቢዎች እንጂ “ጠባብ” አለመሆናቸውን አስባለሁ፡፡ በሰውነት ደረጃ እንጂ በብሔር ማዕቀፍ እንደማይሰቡ፣ ምድር በሙሉ የሰው ልጅ እንጂ “የእከሌ” ወይም “የእኔ” የማይሉ መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ ከዚህ ትልቅ ነገድ የወጡ የዘመኑ ፖለቲከኞች ናቸው እንግዲህ ከክልልም ወርደው “አዲስ አበባን” በጠባብ አጥር ውስጥ ለመቀንበብ የሚከጅሉት፡፡ ለዚያውም በማያሳምን መልኩ፡፡ አቶ በቀለ “….አዲስ አበባ ዓመት ከመቶ በፊት የኦሮሞ ነበረች” ነው ያሉት፡፡ ከዚያ በፊትስ? … የሚል ጥያቄ ቢከተል ምላሻቸው ምን ሊሆን  እንደሚችል እንጃ፡፡
.
እኚያ አዛውንት ግን “ፈጣሪ ለሰው ልጅ ድንበር አልከለለም፤ እግሬ የረገጠበት ሁሉ ሀገሬ ነው” ነው ያሉት፡፡ ሌላውም ሰው የተባለ ሰው እግሩ የረገጠው (እሳቸው የሚኖረበት ኦሮሚያ ክልልም ቢሆን) ሃገሩ ነው ማለታቸው ነው፡፡ አቤት ርቀታቸው…..!
.
ለማንኛው ከኤል.ቲቪ የኦቦ በቀለ፣ እንዲሁም ከበቀደሙ የአብን ሊቀመንበር ተብዬው ዶ/ር ደሳለኝ ቃለምልልስ፤ የዘር ፖለቲካ የሚያራምዱ ፖለቲከኞች ቢያንስ አንድ ነገር መማር አለባቸው፤ መማር ይገባቸዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ከመናገር በፊት መጠንቀቅን፡፡ “ሶስት ጊዜ ለካ አንድ ጊዜ ቁረጥ” የሚለውን ብሒል ከልቦናቸው ያስገቡታል ብዬ አስባለሁ፡፡ በሌላ አነጋገር “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” ለማለት ያህል ነው፡፡ መማር ፊደል መቁጠር ብቻ አይደለማ! እሱ “መፈደል” ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ መማር የሕዝብን ስነ ልቦና ጭምር ጠንቅቆ መረዳት፣ማወቅ ጭምር ነው፡፡
ይኸው ነው፡፡
.
በመጨረሻ  “ሉከ መሌ ብየ እንቀቡ” ግጥሜን ተጋበዙልኝማ
.
“ሉከ መሌ ብየ እንቀቡ” ይላል ኦሮሞ ሲተርት
እግር እንጂ፣ ሀገር የለኝም ለማለት፡፡
የሀገሬ ሰው በትውፊቱ – ከዘመን ሁሉ ቀድሞ
የፈጣሪን ቀዳሚት ሕግ – በልቡ ፅላት አትሞ
በክብር ስላኖረው ነው – ሀገር የለኝም ማለቱ
በአምላኩ ቃል ነው ቅናቱ፡፡
የአበው ሕገ-ልቦና
ትውፊት ሥነ-ቃል ሲያፀና
እንዲሁ አይደለም ለወጉ – ጥልቅ ነው ኃያል ምስጢሩ
ከዘመን ዘመንም ያልፋል – እውነትን እያሻገሩ፡፡
እናም የሀገሬ ኦሮሞ – በጥቂት ቃላቶች ብቻ
በአንዲት ስንኝ ሰንጎ – ቋጥሮ የእምነቱን ስልቻ
“ብየ እንቀቡ” ብሎ – ሐቁን አፍረጥርጦ – እምነቱን ሲናገር
“የሰው ልጅ ነኝና – አያሻኝም ድንበር” – ማለቱ ነው ከምር፡፡
“ሉከ መሌ” ሲልም – እውነት ነው ከልቡ
“እግሬ የደረሰበት – ፅንፍ ዓለም ሁሉ ክበቡ
ምድሪቷን በሙሉ -የረገጥኩት መሬት
የትም ሆነ የትም – ሀገሬ ነው በእምነት”
ማለቱ ነው ጃርሳ
የአምላኩን ስጦታ – ከፍ አርጎ ሲያወሳ፡፡
ደግሞም እውነቱን ነው – አንዳች ሐቅ አልሳተም
ፈጣሪ ለሰው ልጅ – ድንበር አልገደበም፤ ክልል አልፈጠረም፡፡
አምላክ፤ ለሰው ልጆች – የሰጠው መመሪያ – ቀዳሚተ- ቃሉ
ባሻችሁ ሂዱ ነው ያለው – “ምድርን ሁሉ ሙሉ”
………………..
…………………
(በነገራችን ላይ ጋዜጠኛዋ ቤቲ ዛሬም ጎበዝ ነበረች)
Filed in: Amharic