>
5:20 am - Thursday December 9, 2021

ለፖለቲካ ምዕመናን፦ ጠ/ሚ ዐብይ እኮ አምላክ አይደሉም!! (ሳምሶም ጌታቸው)

ለፖለቲካ ምዕመናን፦ ጠ/ሚ ዐብይ እኮ አምላክ አይደሉም!!
ሳምሶም ጌታቸው
* ዐብይንም ሆነ መንግሥታቸውን ማገዝ የሚቻለው በዕውር ድንብር ቲፎዞነት፣ በጎሰኝነት አይደለም። ሥራቸውን በአግባቡ እንዲወጡ በድጋፍም በተቃውሞም በመረባረብ እንጂ። ለማንኛውም የፖለቲካ አካኼዳችን መለኪያ ሚዛናችን ቢያንስ፣ ሀገራችንና “ሰው”ነት፣ ርዕሳችን ደግሞ ፍትሕና እኩልነት ይሁን!
 
የኢትዮጵያ ሕዝብ ለጠ/ሚ ዐብይ ድጋፍ የቸራቸው፤ ብሔራቸውን ጠይቆ፣ ሐይማኖታቸውን አጥንቶ እንዳልሆነ ሁሉ ኦሕዴድ/ኢሕአዴግ መሆናቸውን ደግሞ ዘንግቶ አይደለም። ጠ/ሚሩ በሠላምና እርቅ በተሞላ የተዋጣለት አንደበታቸው፣ በተግባርም የታጀበው አስደሳችና ቅን እርምጃዎቻቸው፤ ሀገራችን ለብዙ አመታት የራቃትን የእርስ በርስ መግባባት፣ ያጣችውን ሠላም፣ የራባትን ዕርቅና ፍቅር ማስፈን የሚችሉ፣ እስርና መሳደድ የሚያስወገዱ መሪ እንደሆኑ በመታመኑ እንጂ። በእርግጥም በበጎ እርምጃዎቻቸው በእንጥልጥል የኖረው ከኤርትራ ጋር የነበረን የጠላትንት ስሜት በአስደማሚ ሁናቴ በአንዴ ተናደ። ከተቃዋሚዎች ጋር ታላቅ የእርቅ ድልድይ ተገነባ። የግፍ እስረኞች ተፈቱ። በሆነው ሁሉ ልጅ አዋቂው፣ ምሁር ጨዋው፣ እስላም ክርስቲያኑ በአጠቃላይ ለሀገሩ ቀናኢ የሆነ ዜጋ ሁሉ ተደሰተ።
ክብሩን፣ ፍቅሩን አድናቆቱን ገለፀ። በየሠፈሩ በየቤቱ ዐብይን የነካ፣ ለማን የገላመጠ እኔን አያርገኝ፤ የሚል ከልብ የመነጨ የእኔነት ስሜት ከዳር እስከ ዳር ያለ ክልል ገደብ፣ ያለ ሐይማኖት ልዩነት ከየሕዝቡ አንደበት ተሰማ። የዚህን ያህል ድጋፍና ፍቅር ያገኘ መንግሥት ነገሮችን ለረዥም ጊዜ መጓዝ እንዲያስችሉት አድርጎ አያያዙን ማወቅ የነበረበት/ያለበት ራሱ ነው። ሆኖም ግን ከቀን ወደ ቀን በጠ/ሚሩና መንግሥታቸው በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ በርካታ ጥያቄዎች የሚያስነሱ ጥፋቶች ተባብሰው እንዲቀጥሉ ሆነ። የሕዝብ ለሕዝብ መገዳደሉ፣ መፈነቃቀሉ፣ መሳደዱ በአስፈሪም በአሳፋሪም ደረጃ፣ ያለ ሀይ ባይ ቀጠለ። በየክልሉ ዘግናኝ ወንጀሎች ሲፈፀሙ በሚዲያ ከሚሰማው እግዚኦታ ውጭ ከመንግሥት በኩል ይሄ ነው የሚባል ጠንካራ ርምጃ ሲወሰድ አልታይ አለ። በተለይ የመምራቱ ዕድል በእጁ የገባው ኦዴፓ/ኢሕዴግ መራሹ መንግሥት ፍፁም ያልተማከለ አሰራርን በተከተሉ፣ የመንግሥታቸውን አቋም “የማይወክሉ” መግለጫዎችን በማን አለብኝነት በሚያጧጧፉ አባላቱ ብዙ ፋወሎችን ሲያስመዘግብ ከረመ።
በተያያዥም ለኦሮሞ መብት እንታገላለን የሚሉ ፓርቲዎች አባላት በየአቅጣጫው የፉከራ፣ የአሸናፊዎች ነን ሽለላዎችን፣ በየሚዲያው አጎረፉ። የተገኘውን ድል ለሀገር በሚተርፍ መልኩ እንደመጠቀም በየዕለቱ የፀብ አጫሪነት “ከእኛ በላይ ማን አለ?” መግለጫዎቻቸውን አዥጎደጎዱ። ይባስ ተብሎ፣ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ቦታዎች የተከሰቱ እጅግ አስደንጋጭና ዘግናኝ የወጣቶች ጥፋትና ውድመት ተከስቶ እያለ፣ የአዲሳባ ወጣቶችን ያውም ያለበቂ ምክንያት ለይቶ የማሰርና ተኩሶ የመግደል አሳዛኝ ድርጊቶች ተፈፀሙ።
የአዲሳባ ወጣቶች ወደ አደባባይ የወጡት ከጅምሩ የእኔ መንግሥት አለ ብሎ በመተማመንና ሰሚ አለ በሚል ነበር። በዚህ ሁሉ ጊዜ ውስጥ ሕዝቡ በጠ/ሚሩ ላይም ሆነ በመንግሥታቸው ላይ አንዳንድ ሥጋቶቹን ቢገልፅም ደፍሮ ሊወነጅላቸውም ሆነ የድርጊቱ ተሳታፊ ናቸው ብሎ ለማመን አልፈለገም ነበር። ሕገ-ወጡን የወጣቶቹንም እስር ምላሽ ይገኝ እንደው በሚል፣ ከሚጠበቀው በላይ በትዕግሥት ሲጠባቀቅ ቆየ። ነገር ግን በመንግሥት በኩል የሚሰጡ መግለጫዎች (ማላገጫዎች) ሆን ተብሎ ሕዝብ ለማበሳጨት የተደረጉ የሚመስሉ ሆኑ። ውስጥ ለውስጥ ጠ/ሚሩ ግን ከነሙሉ ሥልጣናቸው ይሆኑ? ምናልባት ከአቅማቸው በላይ በሆነ መንገድ የሚታዘዛቸው ጠፍቶ ይሆናል። ዐብያችንማ ይኼን እያዩ፣ እየሰሙ ዝም አይሉም የሆነ ነገር ሆነው ነው ወዘተ ወዘተ ተባለ። ብቻ ሁሉም መሪውን አሳልፎ በማይሰጥ መልኩ ጥርጣሬዎቹን ሲያስቀምጥ ቆየ።
እያለ እያለ ሄዶ፣ ፍፁም ሕገ-ወጡን የአዲሳባ ልጆች እስርን አስመልክቶ በየባለሥልጣናቱ የማይገናኙ መግለጫዎች ሲሰጥ መቆየቱ አልበቃ ብሎ፤ ጠ/ሚሩ በፓርላማ ተገኝተው ስለጉዳዩ የሰጡት አስከፊና አናዳጅ አስተያየት እንዲሁም አንዳንድ ወቅታዊ ጉዳዮችን የገለፁበት መንገድ በብዙ ሰው ያልተጠበቀ መናኛ ሆኖ ተገኘ። ዐብይ ሸርተት የማለት ነገር እየታየባቸው ያለ የሚመስሉ ነገሮች መሽተት ጀማመሩ። ለካ ጠ/ሚሩ ጉዳዩን ያውቁታል ተባለ። ብዙ ነገሮችንም ወደ ኋላ እየተመዘዘ ሴራ ትንተና ተጧጧፈ። በአጠቃላይ የተጠቀሰው፣ የሆነው ስህተት ሁሉ  በመንግሥት እና በራሳቸው በጠ/ሚሩ ሆነ። በዚህም የተነሳ፣ ከፍ ያለ የቅዋሜና ትችት አስተያየቶች ከየአቅጣጫው መደመጥ ጀመረ። እናም የነገሮቹን አመጣጥ ለተመለከተ ጠ/ሚሩ ላይ የተሰነዘረው የሰሞኑ ትችት ያልተጠበቀና ምክንያት የለሽ አልነበረም።
ነገር ግን ሁሉንም ነገሮች በጎሰኝነት ሒሳብ ብቻ ማወራረድ የሚቀናቸው ልቡና ዕውር ሰዎች ደግሞ ጦራቸውን ሰብቀው ተነሱ። በጠ/ሚ ዐብይ እና በመንግሥታቸው ላይ የሚሰነዘረው የሰሞኑ ተቃውሞ፣ ያለምክንያት የተፈጠረ  እና ከብሔር ማንነታቸው ልዩነት የተነሳ እንደሆነ አስመስለው በመሳል፣ ጭራሽ ያልታሰበ ነገር በማራገብና በመቀስቀስ ላይ ተጠመዱ። እንዲህ ካለው የጎሰኝነት አመለካከት ቀጥሎ ደግሞ፣ በሀገራችን የፖለቲካ ልማድ ያለው ትልቁ ችግር፣ “መደገፍ” ወይም “መቃወም” በሚሏቸው ሁሉት የፅንፍ ጫፎች ላይ ብቻ ቆሞ የመገኘት ነገራችን አንዱና አደገኛው ነው። 100% ድጋፍ ወይም 100% ተቃውሞ ብቻ።
ለማንኛውም ስትደግፉ በጎሰኝነት እያሰባችሁ የእኔ የምትሉትን ሰው በአምላክ አምሳያነት ለመሳል የምትሞክሩ ሰዎች፤ የምትደግፏቸው ፓርቲዎችም ሆኑ ግለሰቦች የትም አታደርሷቸውም፣ እናንተም የትም አትደርሱም። የሚደግፉትን ፓርቲ በቤተ አምልኮነት፣ የሚደገግፉትን መሪ ግለሰብን በአምላክነት መቀበልና ራስን የፖለቲካ ምዕመን አድርጎ መቁጠር በዚህ ዘመን የሚገኝ ሰው ተግባር አይደለም። ስለሆነም አንድ ነገር አስታውሱ ወይም ዕወቁ። ጠ/ሚሩ ፍጡር ሰው ናቸውና በአነጋገራቸውም ሆነ በሥራቸው ከሳቱ ይተቻሉ፣ ይነቀፋሉ ባስ ካለም ይወገዛሉ። እንኳን ፍጡር-ሰው የሆነ መሪ ቀርቶ፤ ኑሮ ሲመር እግዜርንም ማማረር ያለ መሆኑን ከጎሰኝነትና ከስሜታዊነት ለራቀ ሰው ሁሉ የሚታወቅ ቀላል ሀሳብ ነው።
ጠ/ሚር ዐብይንም ሆነ መንግሥታቸውን ማገዝ የሚቻለው በዕውር ድንብር ቲፎዞነት፣ በጎሰኝነት አይደለም። ሥራቸውን በአግባቡ እንዲወጡ በድጋፍም በተቃውሞም በመረባረብ እንጂ። ለማንኛውም የፖለቲካ አካኼዳችን መለኪያ ሚዛናችን ቢያንስ፣ ሀገራችንና “ሰው”ነት፣ ርዕሳችን ደግሞ ፍትሕና እኩልነት ይሁን። ያኔ ለአንድ ግልፅ ስህተት የተለያዩ ውዝግቦችን ሳይሆን፤ ከዳር እስከ ዳር የትብብር ድምፆች የሚሰሙባት መብት የሚከበርባት የፍትሕና የሠላም ሀገር ትኖረናለች። ሰውነት ይቅደም፣ ዜግነት ይከተል፣ ጎሰኝነት ግን ይውደም። ጎሰኝነት የለየለት እርኩስ ሀሳብ ነው። አምላክን ሳይቀር የሚያስከዳ፣ ግለሰብን የሚያስመልክ፣ ከሳይንስ የሚያጣላ ነው። እናም ፖለቲካ የሐይማኖት ተቋም አለመሆኑ፣ መደገፍም ምዕመንነትን አለማስገኘቱ ሁሌም ይታወስ። እሺ?
Filed in: Amharic