>

ይድረስ ለክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ፤ ...  (ሃራ አብዲ)

ይድረስ ለክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ 

የኢህአዴግ ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊት ሪፑብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር፤  

ኢትዮጵያ፤አዲስአበባ                                                             (ሃራ አብዲ

ከቀናት በፊት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡትን ንግግር አዳምጫለሁ። ኢትዮጵያ በበዛዉ የመከራ ዘመን ተጨንቃና አምጣ የወለደችዉ የተስፋ ቀንዲል  ሲስለመለም ሳየዉ ልቤ በመታወኩ የግሌን ሃሳብ ለማካፈል ተገደድኩ። ህዝቡ ለዉጡን ካልደገፈ በቀር በስልጣን ለመቆየት ፍላጎት እንደሌለዎት የሚያመላክት ሃሳብ መሰንዘርዎን በቀላል ልወስደዉ ከበደኝ።

እንደሀገር የመቀጠላችን እዉነት፣ በእልፍ አእላፍ ጀግኖች መስዋእትነት የመጣዉ ነጻነት እና እንደ አንድ ኩሩ ህዝብ በዜግነት የመያያዛችን ራእይ ፈጥኖ እንዳያሸልብ፤ ይልቁንም፤ ወዳሳለፍነዉ ዘመነ-መርገምት እንዳንመለስ ከፍተኛ ጥንቃቄ ከህዝባችን፤ ቅንነትና ጥበብ የተመላዉ አመራር ከእርስዎና ከመንግስትዎ ይጠበቃል። ጥያቄዉ ፤ በጀመርነዉ የለዉጥ ጎዳና ላይ  ለመሄድ ምን እናድርግ? የሚለዉ ነዉ። ከብዙ ነገሮች መካከል፤ ጥቂቱን በጽሁፌ ማጠቃለያ ልጠቁም እወዳለሁ።ህዝቡ ድጋፉን እንዲቀጥል ለማድረግ ወዳጅ እያበረከቱ፤ አፍራሽ ተልእኮ ባላቸዉ ላይ የሃሳብ የበላይነት እየተጎናጸፉ መሄድስ እንዴት ይቻላል ?

ግልጽ እየሆነ እንደመጣዉ፤ ብዙዎቻችን የምንዋጋዉን ለይተን የማናዉቅ  ስንሆን፤እርስዎ ደግሞ የህዝብ መሪ በመሆንዎ በያዙት መልካም አመራርና ትእግስት፣ የተቻለዎትን ሁሉ ያደርጉ ዘንድ ሚሊዮኖች አብረንዎት እንቆማለን። ለማንም ብለን ወይንም በወገንተኝነት ስሜት ተገፋፍተን ሳይሆን፤ ሀገራችንንና ህዝባችንን ዳግም በመዳፋቸዉ አስገብተዉ፣ በቁም ሊቃረጡን ቢላዋ ስለዉ የተቀመጡ ጠላቶች እንዳሉን በደንብ ስለምንገነዘብ ነዉ።

ኢትዮጵያ ፣በህዝብዋ የአብሮነት ስነ-ልቦና፣በልዩ ልዩ ባህልዋ፤ ለዛና ጥበብ በተመሉት በርካታ ቁዋንቁዋዎችዋ፣ በደምና በአጥንት በተዛመደ የአንድነት መንፈስ፣ የዉጭ ወራሪዎችን እያንበረከከች ከእኛ ከልጅዎችዋ አልፎ የመላዉ አፍሪካዉያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ኩራት፣ የነጻነት አርማና የባርነት ዘመናቸዉ መጽናኛ ሆና ኖራለች።

ሀገራችን፤ አብሮአት እድሜ በጠገበዉ የዘመናት ሁዋላ ቀር የመንግስት አስተዳደር መበደልዋ እንዳለ ሆኖ፤ባለፉት ሃያ ሰባት አመታት በትግራይ ነጻ አዉጭዎች እጅ በዉስጥ ቅኝ አገዛዝ በየትኛዉም የአለም ክፍል ያልታየ  የሰቆቃ ኑሮ ገፍታለች። አሁንም የዚያ አረመኔያዊ የግፍ ቀንበር ጨርሶ ከህዝባችን ጫንቃ ላይ አልወረደም። ይሁን እንጂ፤ እጅግ በሚያስደንቅ ሁኔታ ሀገራችን አይታ የማታዉቀዉን የነጻነት ብርሀን አጮልቃ ማየት በመጀመርዋ  በዜጎችዋ መንፈስ ዉስጥ ለሞት ያጣጥር የነበረዉ ተስፋ፣ ነፍስ መዝራት ይዞአል። ዘመነ-ፍዳዋም እያከተመ መጥቶአል።

ለዚህ ንጋት ያበቁን እልፍ ወገኖቻችን፤ ሃሳባቸዉን በነጻነት መግለጽ ወንጀል ሆኖ፤ የተገኙበት ማህበረ-ሰብ ማነነት እንደጥፋት፣ የፖለቲካ አስተሳሰብ ልዩነታቸዉ እንደሀገር ክህደት ተቆጥሮ ይህ ነዉ የማይባል ግፍና መከራ ተቀብለዋል። ታስረዋል፣እርቃናቸዉን ተደብድበዋል፣የዝቅዝቅ ተሰቅለዋል፣ ከቤት ንብረታቸዉ ተፈናቅለዋል፤ ከሀገር ተሳደዋል፣በዉጭ በሚኖሩበት የሞት ፍርድ ተፈርዶባቸዋል፣ አካላቸዉ ጎድሎአል፣ህይወታቸዉን አጥተዋል። ልጆቻቸዉ ያለአሳዳጊ፣ወላጆቻቸዉ ያለጠዋሪ ቀርተዋል። ይህ ብቻም አይደለም።በእናታቸዉ ማህጸን የነበሩ የወደፊት ዜጎቻችን ሳይወለዱ በመርፌ የህይወትን ልምላሜ እንዳያዩ ተቀጭተዋል፣ በአባቶቻቸዉ አብራክ ሳሉ ነፍሳቸዉ እንድትመክን ተደርጋለች።

ይህን የመከራ አዝመራ በላያችን ላይ እያመረቱ እነሱ መላ ሀገራችንን እንደ ሾተላይ ወግተዉ ይዘዉ የህዝባችንን ሀብት ወደ መንደራቸዉ ሲያግዙ፣ በሀገራችን ታይቶ የማይታወቅ የሀብት ማማ ላይ ተቀምጠዉ በዉጭ ሀገራት ባንክ የኢትዮጵያን ህዝብ ገንዘብ ሲያከማቹና ሲነግዱ የነበሩት የትግራይ ነጻ አዉጭዎች  አሁንም አሉ። አሁንም ከራስ ጸጉራቸዉ አንዲቱ ሳትወድቅ የዘረፉትን (ዘረፋ የሚለዉ ባይገልጸዉም)እየበሉና እየተዝናኑ ሀገራችንን ለመበተንና ህዝባችንን ወደ መከራዉ ዘመን ለመመለስ በሙሉ ጊዜያቸዉ ተግተዉ በመስራት ላይ ይገኛሉ። በአንጻሩ፤ በክቡር መስዋእትነት በተገኘዉ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ እድል ተጠቅመዉ የተሰራዉን ስራ ብቻ እየተቹ ለጠላቶቻችን መግቢያ ቀዳዳ የሚያሰፉ የወዳጅ ጠላቶች እንደአሸን ፈልተዋል።ይህን መናገር ለቀባሪው ከማርዳትም በላይ እንደሆነ አልጠፋኝም። «የምንዋጋዉን ለይተን የማናዉቅ» እጅግ ብዙዎች ለመኖራችን እንደ አስረጂ ለማቅረብ እንጂ።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤ አንድ አመት ያልሞላዉ የለዉጥ ጉዞ በሀገራችን ያመጣዉን መረጋጋትና በህዝባችንና በጎረቤት ሀገራት ጭምር ያሳየዉን አስደናቂ ዉጤት ልበ-ብርሀን የሆነ ሁሉ የሚደነቅበትና የሚደመምበት ነዉ። እርስዎ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን  ከፍተኛ የሀገራችንን የስልጣን እርከን ከረገጡ ወዲህ ለቁጥር የበዙ፤ በሀገራችን ታይተዉ የማይታወቁ ድንቅ ስራዎችን በመሪነት አከናዉነዋል።ከሁሉም በላይ፤ ኢትዮጵያ ሳትበታተንና ህዝብዋ በደም አበላ ሳይነከር እንዲያዉም የዜግነት መንፈስና የሀገር ፍቅር በህዝባችን እሩህ (ነፍስ) ዉስጥ እንዲለመልም ያስቻሉት፤ በኢትዮጵያ ታሪክ በአድናቆት ሲዘከር የሚኖር ነዉ።

በእርስዎ አመራር የደረስንበት የፖለቲካ አስተዳደር ና የትግራይ ነጻ አዉጭዎች የኢትዮጵያን መንግስት በትረ-ስልጣን በተቆጣጠሩበት ዘመን የነበረዉን ልዩነት ለማወዳደር ሰንጠረዥ የሚበቃ አይመስለኝም። ይህ ማለት፤ በእርስዎና በመንግስትዎ የሚመራዉ ፖለቲካ አልጋ በአልጋ ነዉ ለማለትም አይደለም። ሊሆንም አይችልም።  አመራርዎ ከወጣበትና ከወረሰዉ «የታመመ ፖለቲካ» ( ለክቡር ለማ መገርሳ አባባል እዉቅናና አድናቆት እሰጣለሁ) ጭብጥ ተነስቶ በአጭር ጊዜ ያከናወንዋቸዉን ነገሮች መረዳት የሚችል ሰዉ አሁን በሀገራችን ላይ እያንሰራራ የመጣዉን አደገኛ አዝማሚያ ይገነዘባል።ድሉን ከመንከባከብና የራስን ድርሻ ከመወጣት ይልቅ የነገር ድሃ እያሳደጉ ይባስ ብሎም አመራሩን ተስፋ ወደማስቆረጡ የተጠጉ ሃይሎች ሀገራችን ለትንሽ የሳታት የመፍረስ አደጋ ነፍስ እንዲዘራ አሉታዊ አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን ልብ የሚሉት አይመስልም። አላማቸዉ አድርገዉት ከሆነም ታግለን ልንረታቸዉ ይገባል።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ገና በጠዋቱ በቲም ለማና ቆይቶም በእርስዎ ወደስልጣን መምጣት በዉስጣችን የሰነቅነዉ ተስፋ አሁንም ስር  እንደሰደደ ነዉ። ይህ አመራር ለሽግግር ጊዜ የሚመጥን ህዝብን ወደ አንድነት የሚስብ ጥበብ ያለዉ ነዉ። ኢትዮጵያ በሶስት ሺህ ዘመን ምጥ የተገላገለችዉ ዘመን አሻጋሪ፣ በብዙዎች ልበ-ልቦና በምኞት የተጸነሰ፤ በአራቱም ማእዘናትና በመሀል ሀገር እንደ ንፍሮ ስትቀቀል የደም ላብ እያላባት እርግዝናዋን ደብቃ ድንገት የወለደችዉ መሪ ነዉ!! ይህ አባባል እርስዎን «ምሉእ-በኩለሄ» ማድረግ ወይንም አንድን ሰዉ ማምለክ አደርጎ የሚወሰድ እንደሚኖር አልስተዉም። እዉነቱ ግን ከዚህ በእጅጉ ይለያል። የመልእክቴ ማእከል የእርስዎ በስልጣን ላይ መቆየት ለአሁኑ አማራጭ እንደሌለዉ ማሳየት ነዉ።

በመሆኑም፤ እንደሀገር የመቀጠላችን እዉነት፣ በእልፍ አእላፍ ጀግኖች መስዋእትነት የመጣዉ ነጻነት እና እንደ አንድ ኩሩ ህዝብ በዜግነት የመያያዛችን ራእይ ፈጥኖ እንዳያሸልብ፤ ይልቁንም፤ ወዳሳለፍነዉ ዘመነ-መርገምት እንዳንመለስ ከፍተኛ ጥንቃቄ ከህዝባችን፤ ቅንነትና ጥበብ በተመላዉ አመራር  መግፋት ከእርስዎና ከአመራርዎ ይጠበቃል። ለዚሁም ህዝቡ ድጋፉን እንዲቀጥል፤የለዉጡ ወዳጆች እንዲበረቱና አፍራሽ ተልእኮ ባላቸዉ ላይ የሃሳብ የበላይነት እንዲያሸንፍ ከታች የሰፈሩት ነጥቦች ጠቃሚ ይመስሉኛል።

-በሀገራችን የመጣዉን ለዉጥ በስፋት የሚዘግቡ፤ ካለፉት የመንግስት አስተዳደሮች ጋር በንጽጽር እዉነተኛ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ፤ ማንኛዉንም የሃሳብ ነጻነት ሳይጋፉ በእርስዎ አመራር የተገኙ ድሎችን ደግሞ ያለምንም ይሉኝታ ወደህዝቡ የሚያሰርጹ ፤ የነጻነት ተጋድሎአችንንና የአንድነት ታሪካችንን በሚጥም መልኩ አቀናብረዉ የሚያቀርቡ በተዋጣላቸዉ የፕሬስ ባለሙያዎች የሚመሩ ጋዜጦች፤መጽሄቶችና የቴሌቭዥን አገልግሎቶች በአዲስ መልክ ማዋቀር፤

ይህን ፕሮጄክት ለመገንባት የፋይናንስ አቅም ያላቸዉና ለለዉጡ ፍጹም ወገንተኛ የሆኑ የግል ባለሃብቶች ወደፊት ቢመጡ ለሀገራቸዉ ትልቅ ዉለታ እንደሰሩ ይቁጠሩት።

ያለፈዉ የመከራ ዘመን ነጋሪት መቺዎች ዘመኑን በሚመጥኑ የጋዜጠኞችና የጥበብ ባለሙያዎች መተካት አለባቸዉ!! ጊዜ ያለፈባቸዉ፤ የግድ እየቀፈፋቸዉ ዜና የሚያነቡ የሚመስሉ፤ ድብርት የሚነዙ፤ ጫን ጫን የሚተነፍሱ ጋዜጠኞችን ወይም እንደአዲስ ትምህርት ቤት ማስገባት ካለዚያ ሌላ ስራ ላይ መመደብ  ጊዜዉ የሚጠይቀዉ ደረቅ ሀቅ ሆኖ ይሰማኛል።

ይህ ለእርስዎ አይጠፋዎትም። «እምነት ከመስማት ነዉ፤ መስማትም ከእግዚአብሄር ቃል» እንዲል፤ የህዝብ ድጋፍ ከመስማትና ከማየት ነዉ። መስማትና ማየትም ከለዉጡ ማህደር።

 

-እስከአሁን ከተወሰደዉ የማረጋጋት ስራ ጎን ለጎን፤  በአፓርታይድ የከፋፍሎ መግዛት ህግ መሰረት ህዝባችንን ፍዳ ያስቆጠሩ፤ አሁንም በማሴር ላይ የሚገኙ  የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላቶች ሁሉ ለፍርድ የሚቀርቡበት ሂደት ማፋጠንና የህግ የበላይነት ማስከበር ተገቢ ከመሆኑም ሌላ የለዉጡ ወዳጆች እንዲበረክቱና እንዲበረታቱ ያደርጋል። አብዛኛዉ ሰዉ በ«ልደግፍ-አልደግፍ» የሚያነክሰዉ፤ እርስዎን ከኢህአዴግ ሙሉ ለሙሉ ነጥሎ ለማየት በመቸገሩ እንደሆነ ይነገራል።

-ሀገር ለመበተን፤ ህዝብ ለማቃቃርና ሰላም እንዲደፈርስ ለማድረግ፤ በተናጠልም ሆነ በህብረት የሚሰሩ ግለሰቦች፤ ቡድኖችና የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ በሃሳብ ከመሸናነፍ አልፎ የሀገር ገንዘብ በመበተንና መሳሪያ በማስታጠቅ ሁከቱና ብጥብጡ ለውጡን እንዲቀለብስ በማድረግ የሚቀጥሉ ከሆነ እርስዎም ሆኑ መንግስትዎ ሊታገሱዋቸዉ አይገባም። በየትኛዉም ሀገር የፖለቲካ መዋቅሩ ሲቀየር ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የሚቀየሩ አሰራሮች አይቀሬ ናቸዉ። «ስጋ መሬት ወድቆ አፈር ሳያነሳ አይቀርም »እንደሚባለዉ የለዉጡ ማእበል ጠራርጎ የሚያስወግዳቸዉ ነገሮችም ህልቆ-መሳፍርት የላቸዉም። ኢትዮጵያም ከዚህ ነባራዊ እዉነታ ዉጭ ሆና ለዉጡን በብቃት ማስቀጠልና ዴሞክራሲን ማስፈን ፈጽሞ አይቻላትም።

-ህዝቡ ግልጽነት ተጠምቶአል። ማንኛዉንም የለዉጥ እንቅፋት በጥበብና በማስረጃ አስደግፎ ሴራዉን እርቃን ማስቀረት ይገባል። የቀን ጅቦች የሚባሉትም ሆኑ ከጅቦቹ ጋር ማእድ የሚቆርሱት ተለይተዉ ለህዝብ ይፋ ይሁኑ። እርስዎና ጥቂት አጋሮችዎ ለብቻችሁ እነዚህን የታርክ ሻህላዎች መሸከም አይገባችሁም። ደግሜ እላለሁ። ህዝባችን ለዉጡን ደጋፊ ነዉ። « ሰይጣን እንደ ስንዴ ሊያበጥራችሁ ተመኘ እኔ ግን ስለእናንተ ማለድሁ» ብሎ ጌታ እየሱስ ለደቀመዛሙርቱ እንደተናገረ፤ ሰይጣን (የትግራይ ነጻ አዉጭ ግንባር) እንደስንዴ ሲያበጥረን ለኢትዮጵያዊነት እንደማለዱ ከአንድም ሁለት ጊዜ ህይወትዎ በተአምር እንደተረፈች ህዝቡ ተረድቶአል!!

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፤ እርስዎም ሳይሰለቹ ፤ከህዝቡ ጋር በመሆን ይህን የለዉጥ ዘመን  መርተዉና በተገቢዉ ሁኔታ ጨርሰዉ ህዝቡ በመረጠዉ መሪ እንዲተዳደር ለማድረግ የጀመሩትን ታሪክና እግዚአብሄር የጣሉብዎትን ሃላፊነት ይወጡ ዘንድ ምኞቴም ጸሎቴም ነዉ።

ኢትዮጵያንና ህዝብዋን እስካሉ ድረስ እንደ አንድ ዜጋ ሙሉ ድጋፌ አይለይዎትም።

ረጂም እድሜ ከጥበብና ከማስተዋል ጋር ይብዛልዎት። 

 

ጸሃፊውን ለማግኘት:- haraabdi@gmail.com

Filed in: Amharic