ታድዮስ የትነበርክ
* እኛ ራያዎ 3ት ፕላኖች ነው ያሉን
የመጀመሪያው ራያ ማንነቱ ራያ ነው ሌላ አይደለም እንደ ራያ’ነቱ ነው ፖለቲካሊ መደራጀት ያለበት። የፕላን ‘ቢ’ ራያ ማንነቱ ወሎ አማራ ነው ፤ እንዲህም ካልሆነ ፕላን ‘ሲ’ ማነታችን ኦሮሞ(ከሚሴ)ነው። በፍጹም ትግራዋይ አይደለንም!“
አላማጣ የመምህሬ ዶ/ር መሰንበት አሰፋ፤የዶርም ሜቴ ሐይሎም ልዑል ፤የጌቻቸው ረዳ አገር ነው። ትንሽ ዝቅ ብሎ የዶ/ር ሲሳይ መንግሥቴም አገር ነው።
በቀደመው ጊዜ በወሎ ክ/ሀገር ስር የነበረው ራያ በሦስት ተከፍልሏ። ራያ አላማጣ፤ራያ አዘቦ እና ራያ ቆቦ። ዛሬ ሁለቱ በትግራይ አንዱ በአማራ ክልል ተካለዋል።
የወቅቱን የአካባቢ ፖለቲካ ከመቐለ አላማጣ የሚወስደን ሹፌር እየነገረን ነው። ጌታቸው አሰፋ የክልሉ የአስተዳደርና ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ፤ ዶ/ር አብርሃም ተከስተም የፋይናንስ ዘርፉ ላይ እንደሾሙ ቀድሞ ነገረን ።
በህሊናየ በጀኔራል ከማል ገልቹ፤በጀኔራል አሳምነው ጽጌና በቀደሞው የደህንነት ሹም ጌታቸው አሰፋ መካከል የሚፈጠረውን እንትን ሳመላልሰው ውየ አደርኩ….
አላማጣ መንገዱ አስቸጋሪ ነው። በጣም አስከፊ የሚባል። በዛ ላይ ያለወቅቱ የሚወርደው ዝናብ አስፖልቱን የበረዶ መንሸራተቻ አስመስሎታል። ለዚህም ነው ከጀብጀብ እስከ አዲ መስኖ 5ኪሎ በማትሞላ መንገድ ውስጥ 9 ያክል የመኪና አደጋ ያየነው።የመከላከያ አምቡላንሱ ቦይ ውስጥ ተጋድሟል፤ቪትዟን ልማደኛው ሲኖ በትክሻው ገፍቷታል፤ ታታ የተባለው አውቶብስ ይዋጣልን ብሎ ገልባጩን ከመቀመጫው በቴስታ አውልቆታል፤ብረት የጫነው ገልባጭ በአፍጢሙ ተደፍቷል፤ ከመድረሳችን ጥቂት ደቂቃዎች በፊት አዲሱ ዶልፊን አላርሙን እንዳበራ በጎኑ ተጋድሟል በስማም ለጥቂት እኮ ነው ከገደል የተረፈው? ይሄን ሁሉ እያየን የሞቀው ጨዋታችን በቅጽበት ወደ ጭንቀት ተለወጠ.. ….
አላማጣ አድረን ውለናል፤ ከሩጫ መልስ በሌሊት ሲገሰግስ ተጭኖ የደረሰውን የኮረም ኮረፌ በጣሳ ለብጠናል። አላማጣ ከዚህ ቀደም እንዳየናቸው የትግራይ ከተሞች አይደለችም። የራሷ ቀለም አላት። በቋንቋ ደረጃ በጣም በብዛት ትግርኛ የተጫነው ቅላጼም ቢሆን የሚነገረው አማርኛ ነው። ሽርጥ በስፋት ይለበሳል። አንዱን ወዳጃችን ባክህ ሽርጥ አጋዛን ብለነው ነበር። ዋጋውን ሲነግረን በቦልት ፍጥነት ወደሓላ አፈገፈግን እንጅ። አንደኛ ደረጃ የሚባለው ሽርጥ በቀለበት ሁሉ ይሾልካል ዋጋው 6ሺህ ነው አላለም?! ቀለል አድርጎ?
ሆ…ሆ…..ይሄኔ ነው መሸሽ።
በቆየንበት ጊዜ ሁሉ ከአማርኛ ሙዚቃ ውጭ ሌላ መስማታችን እርግጠኛ አይደለሁም። ኮረፌ የጠጣንበት ቤት የነበሩት ወጣቶች በጥርጣሬ ሁኔታችን ይከታተላሉ።ለነገሩም ከተማው ውስጥ ነገር እንዳለ ያስታውቃል። እድሜያቸው ከሃያዎቹ አጋማሽ የማይዘሉ የትግራይ ክልል ልዩ ኃይሎች በልዩ የአረማመድ ስታይል መሳሪያቸውን ይዘው፤ በቁጥር በርከት ብለው ዋናውን አስፖልት ሲመላለሱበት ውለው ሲመላለሱበት ያድራሉ።
ባለ ባጃጅ ነው። ኮንትራት ወሰደንና ሒሳብ ከፍየ መልስ ለመቀበል ጠጋ ባልኩበት አጋጣሚ
“እኔ ምልህ ራያ አላማጣ ግን ማንነቱ ትግራይ ነው አማራ?አልኩት እንደዋዛ
“ራያ አላማጣ? “አለኝ ብሩን እየዘረጋጋ
“እ….?
አንገቱን ቀና አድርጎ “ራያ አላማጣ ኢትዮጵያዊ ነው!” ብሎኝ ባጃጁን በኮብልስቶኑ እያስነጠረ ሸመጠጠ።
ራት በልተን እጃችን ስንታጠብ ወደ ኋላ ቀርቶ የነበረውን አንድ ፋርማሲስት “ራያ በልዩ ዞንነት ሊደራጅ ነው አይደል?”አልኩት
“ባክህ ተዋቸው ሲያወሩ ነው፤እነሱ ለኛ ምንም አያደርጉም፤እንዲያደርጉም አንፈልግም!” ኮስተር አባባሉን ስላልጠበኩት ሌላ ጥያቄ ጠፋብኝ።የኋላየኋላ እንደሰማሁት ከአንድም ሁለቴ በአስተባባሪነት ተከሶ ታስሮም ነበር።
ይሄኛው ደግሞ እሳት የላሰ ፖለቲከኛ ሹፌር ነው። የጌታቸው ረዳ የቅርብ ዘመድ ። ያወራዋል አይገልጸውም።ራያ በልማት ከሌሎች የክልሉ ከተሞች እንዴት ወደ ኋላ እንደቀረ ምሳሌዋችን እያነሳ ይሞግታል። በቅርብ ያለችው ማይጨው እንኳን ስንት ፋብሪካ እንደተገነባላት በቁጭት መሪውን እየጎሰመ አወራን በዚህ መሐል ትኩረቴን የሳበው” ይህም የሆነው ራያን ስለማያምኑት ነው አንድ ቀን እንደምንሄድ ያውቃሉ”ሲል ነው።
“ወደየት ነው ምትሄዱት?”
“ወደ አማራ ነዋ!”
“እዛ ብትሄዱ ምን የተለየ ነገር ይኖራል?
“ቢያንስ ልማት እናገኛለን!”
“እዛስ ያሉት ከተሞች ከዚህ የተለየ መች ለሙ ብለህ ነው? እዲደያውም በትግራይ ያሉ ከተሞች አይሻሉም ብለህ ነው?”
“ለማንኛውም። እኛ ራዎ ፫ት ፕላኖች ነው ያሉን
የመጀመሪያው ራያ ማንነቱ ራያ ነው ሌላ አይደለም እንደ ራያ’ነቱ ነው ፖለቲካሊ መደራጀት ያለበት። የፕላን ‘ቢ’ ራያ ማንነቱ ወሎ አማራ ነው ፤ እንዲህም ካልሆነ ፕላን ‘ሲ’ ማነታችን ኦሮሞ(ከሚሴ)ነው። በፍጹም ትግራዋይ አይደለንም።”
እንደዚህ የሚለን ወደ መቐለ እየመልለስን ነው።
እግዚኦ ነው!!ሌላ ምን ይባላል። ይሄንን ፍላጎት የሚያስተናግድ ምን አይነት ፖለቲካዊ መፍትሔ አበጅተን ይሆን?
መቼ ነው ይሄ የማንነት ጥያቄ መፍትሔ የሚያገኘው? እንዴት አድርገን ፖለቲካችን ብናዋቅረው?እንዴት አድርገን ሕገመንግሥቱን ብናሽሻለው? ወይንም መሬት ብናስነካው ይሆን ማንነትን መሠረት ያደረጉ ተጨማሪ ግጭቶችንና አለመረጋጋቶችን መቀነስና ማስወገድ የምንችለው?
ይሄን እያሰብኩ አዲስ አባ በገባሁ ማግስት ያች ኮረፌ የጠጣንባት፤ ኤርትዊቷ ሶፊያ በኢትዬጵያ ሆቴል የኤርትራ ቡናን(በዝንጅብል) ያጠጣችን ፤በሌሊት እድሜ ለግርማ ስፓርት ብሎ እግሬ እስኪዝል የሮጥንባት ራያ አላማጣ ዛሬ በጥይት ስትቆላ ውላለች ።
የሚያሳስበኝ የአሁኑ ብቻ ሳይሆን የልጆቹ መቁረጥ ለምንም የማይመለስ መሆኑን ሳስታውስም ጭምር ነው።
“ኢትዬጵያ ታበጽህ እደዊሃ…….