>
4:44 pm - Tuesday July 5, 2022

አፓርታይድ በኢትዮጵያና በደቡብ አፍሪካ ያለው አንድነትና ልዩነት!!! (ዶ/ር ግሩም ዘለቀ)

አፓርታይድ በኢትዮጵያና በደቡብ አፍሪካ ያለው አንድነትና ልዩነት!!!
ዶክተር ግሩም ዘለቀ (የuniversity of south eastern Norway አሶሽዬት ፕሮፌሰር)
 
የደቡብ አፍሪካ አፓርታይን ከኢትዮጵያ ጋር ማመሳሰል የማይቻለው የህግ ክፍፍል ባለመኖሩ ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ የህግ የበላይነት ገዢዎችን ስለማይመለከት ነው እንጂ ቢከበር ህግ ለሁሉም ዜጋ አንድና እኩል ነው። የመንግስት ወታደር ሰው በገደለ ቁጥር አፓርታይ ነው ማለት የማይቻለው በህግ ምክንያት ነው። በአፓርታይድ አገዛዝ ጥቁሮችን መግደል የሚፈቀድበት በህግ የተመቻቸበት ሁኔታ ነበረ። በኢትዮጵያ ዋናው ችግሩ መንግስት ሁልጊዜ ከህግ የበላይ መሆኑ ብቻ ነው እንጂ መንግስትም ቢሆን መግደል በህግ አይፈቀድለትም።
በደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ ዘረኝነት በበጎነት የሚታይ ህጋዊነት ነበረው። ኢትዮጵያን ከአፓርታይ ጋር የሚያመሳስላት በቁጥር ትንሽ የሆኑ ገዢዎች የቀረውን ኢትዮጵያ ከፋፍለው አንድ ላይ ሆኖ መነጋገር እንዳይችል ማድረግ መቻላቸው ብቻ ነው። በደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ 4 ሚሊዮን የማይሞሉ ነጮች ከ22 ሚሊዮን በላይ የሆነው ነጭ ያለሆነ ህዝብ አንድ ሆኖ ተስማምቶ እንዳይኖር በማድረግ ጥቂት ነጮች የበላይነት ይዘው ለብዙ አመታት አምባገነናዊ ስልጣን ይዘው ቆይተዋል። አብላጫው የኢትዮጵያ ህዝብ በክልል፣ በዞንና ልዩ ወረዳ በሚባሉ መንደሮች መከፋፈሉን እንደ ብሔረሰቦች ነፃነት እንጂ ወደ ባርነት መግባቱን ስለማይረዳው ከሌሎች ብሔረሰቦች ጋር በሚያደርገው ዘላቂ ግጭት በቁጥር አናሳ የሆነ አገዛዝ (ፓርቲ) የበላይ ሆኖ በአምባገነንነት እንዲገዛው አድርጓል። ለዚህ ሁሉ ተጠያቂው ህዝቡም ጭምር ነው።
የወልቃይት ፖለቲካዊ መብትና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በጉልበት በመደፍጠጥ የትግሬዎችን የበላይነትና ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ የወልቃይት ህዝብ ራሱ የተጫወተው ሚና መኖሩንም መዘንጋት የለብንም። የወልቃይት ህዝብ ከህዋሃት ወያኔ ጋር በአንድነት ሆነው የኢትዮጵያ ወታደሮችን ደምስሰዋል። ኮ/ል ደመቀ ሳይቀር ከህዋሃት ጋር እጅና ጓንት ሆነው የኢትዮጵያን ሰራዊት መደምሰሳቸውን ያምናል። ከሁሉም ብሔረሰብ የተወጣጣው የኢትዮጵያ ምርድ ጦር መሪዎች የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባርን ለመምታት ወልቃይቶች ይዋጉናል የሚል ጥርጣሬ አልነበራቸው።
ሲጀመር ወልቃይት አማራ ነን ሳይሆን የሚሉት አማራ ክልል መሆንን ነው የሚፈልጉት። አማራ ነን ብለው አያውቁም። እንደነ አዜብ መስፍን ያሉ አማራነት የሚጠሉት ወልቃይት እንደ ራያ ራሱን የቻለ መሆኑን ስለሚያምኑ ነው። በጌምድር አማራ ብቻ አልነበረም። ወልቃይቶች የደርግ ወታደሮን ከህዋሃት ጋር ሆነው የደመሰሱት ልክ እንደ ህዋሃት ደርግ ጨቋኝ የአማራ አገዛዝ ነው ብለው ያምኑ ስለነበረ ነው። አማራ አለመሆናቸው እንዳለ ሆኖ ክልል መምረጥ ግን መብታቸው ነው። አማራ ክልል ስር መሆን አማራ መሆን አይደለም። ብዙ ችግር እንዲህ አይነት ችግሮች ከሻዓቢያ ከኦነግና ከሌሎችም ጋር የተፈጠረው ከህዋሃት ጋር የነበራቸው የጫካ ቃልኪዳንን ሲያፈርሱ ነው።
በዚያ አካባቢ ከሃዲነት አዲስ ነገር አይደለም። የህወሀት መስራቹ አማራው አብተው ታከለ (የህዋሃት ቼ -ጉቬራ) ግንቦት 1991 ህዋሃት አዲስ አበባን ሲቆጣጠር ዜናዊን አጅቦ የገባው ህዋሃት (ትግሬ) ሆኖ ነበረ። ከሃዲነት ጫፍ ሲደርስ በዚህ መልኩ ይገለጻል። ወልቃይቶች “ከህወሀት ጋር አብረን የታገልነው ደርግን ለመጣል እንጂ ትግሬ ለመሆን አልነበረም” ማለት ከመጀመራቸው እስከ ሽግግር መንግስቱ መጨረሻ ወቅትና ከዚያም የተወሰነ ጊዜ ድረስ በትግራይ ስር መሆንን ጭራሽ እንደ ድል ውጤት እንጂ የአማራ ማንነት አጀንዳቸው እንዳልነበረ ራሳቸው ይመሰክራሉ። “ትግሬ ለመሆን አልነበረም” ሲሉም አማራ ለመሆን ነው ማለት አይደለም። ወልቃይት ወልቃይቴ ነው። የወልቃይት አማራ ማለት ወልቃይት ውስጥ የሚኖር አማራ ማለት ነው።
የህዋሃት መሪዎች ግን ችግር ሊፈጠር እንደሚችል ቀድሞ ስለገባቸው የትግራይ ህዝብን ወልቃይት ላይ ማስፈር የጀመሩት የጀመሩት እ.ኤ.አ በ1995 ነበረ። በትግሉ ወቅት ደርግን ለማጥፋት በሚል የጋራ ዘመቻ በተፈጠረው ትስስር የትግራይ ህዝብ ራሱን የወልቃይት ህዝብ ባለ ውለታ አድርጎ ስለሚቆጥር ዛሬ ከፊሉ ወልቃይቶች ትግሬ አይደለንም ሲሉ ትግራዮች ክህደት እንደተፈጸመባቸው ያምናሉ።
 ህዋሃቶች ወልቃይቶች ላይ የሚፈጸሙት ግፍ አስከፊነቱም ከብቀላ የመነጨ ነው። የህዋሃት ተዋጊ መስራችና “ጀግና” አማራው አብተው ታከለም ህዋሃት አዲስ አበባ ሲገባ ተረስቶ የሚያሳክመው አጥቶ በድህነት ትግሬ ሆኖ ተሳቆ ሞተ።
የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ 50 አመት ሊቆይ የቻለው 10በመቶ ጥቁርም ነጭም ስርዓቱን ይደግፍ ስለነበረ።
 80 በመቶ ጥቁርም ነጭም ደቡብ አፍሪካዊ እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ለስርዓቱ ግድ የሌለው ውሎ መግባቱንና ለራሱን ጉዳይ ብቻ የሚጨነቅ ስለነበረና ቀሪው 10 በመቶ ደቡብ አፍሪካዊ ብቻ እስከሞት ድረስ ዋጋ ለመክፈል ዝግጁ ስለነበረ ነው። በሁሉም ስርዓት ውስጥ ለሚፈጸመው ግፍ በከሃዲነትና አድርባይነት መጀመሪያ ተጠያቂ መሆን ያለበት እየተጎዳ መሆኑ የሚነገርለት ተጨፍልቄያለው፣ ግፍ ተሰርቶብኛል የሚለው ህብረተሰብ ራሱ ነው።
Filed in: Amharic