>

የህወሓት አይዲዮሎጂ በጃፓን ከነበረው ወታደራዊ ፋሽስት ጋር ይበልጥ ይመሳሰላል!!! (ስዩም ተሾመ)

የህወሓት አይዲዮሎጂ በጃፓን ከነበረው ወታደራዊ ፋሽስት ጋር ይበልጥ ይመሳሰላል!!!
ስዩም ተሾመ
ህወሓት ከትጥቅ ትግል ጀምሮ ይዞት የመጣው “#አብዮታዊ_ዴሞክራሲ” የሚል የፖለቲካ አይዲዮሎጂ አለው። ይህ አይዲዮሎጂ የፓርቲና የመንግስት ከመሆን አልፎ የህዝብ መስመር እንዲሆን ተደርጓል። ለዚህ ደግሞ “የህወሓት መስመር የህዝብ መስመር ነው፣ የህዝብ መስመር የህወሓት መስመር ነው” የሚለውን መርህ መጥቀስ ይቻላል። ይህ አይዲዮሎጂ፤ “በህወሓት አባላት መካከል ልዩነት አይኖርም፣ ከህወሓት ሌላ የትግራይን ህዝብ ጥቅም የሚያስከብር የፖለቲካ ቡድን የለም፣ በትግራይ ሕዝብ (ተጋሩዎች) መካከል ልዩነት አይኖርም፣ እና በህወሓት እና የትግራይ ሕዝብ መካከል ልዩነት የለም” በሚሉ የአንድ-ዓይነትነት እሳቤዎች ላይ የተመሰረተ ነው።
በዚህ መሰረት ህወሓት የሚከተለው የፖለቲካ አይዲዮሎጂ ማህብረሰብን ማዕከል ያደረገ ከመሆኑም በላይ ግለሰባዊነትን ሙሉ በሙሉ የሚጨፈልቅ፣ በሕዝብ ስም የግለሰቦችን መብትና ነፃነት የሚገድብ ነው። በዚህ ረገድ የህወሓት አይዲዮሎጂ በጀርመንና ሩሲያ ከነበሩት አምባገነንና ወታደራዊ ፋሽስት መንግስታት ይልቅ በጃፓን ከነበረው ወታደራዊ ፋሽስት ጋር ይበልጥ ይመሳሰላል።
የፖለቲካ አይዲዮሎጂ ከአፈጣጠሩ እስከ ውጤቱ ድረስ ከህወሓት አይዲዮሎጂ ጋር አንድና ተመሳሳይ ነው። ይህ የግለሰብን መብትና ነፃነት በመጨፍለቅ፣ ህዝብና ፓርቲን አንድ አድርጎ መጓዝ መጨረሻው አስከፊ ጦርነትና ዕልቂት ነው። በመሆኑም በጃፓን የነበረው ወታደራዊ ፋሽስት በስተመጨረሻ በሀገሪቱ ሕዝብ ላይ ያስከተለው ዕልቂት ህወሓት እየሄደበት ያለው መንገድ ነው። የጃፓን ወታደራዊ ፋሽስት እ.አ.አ. በ1944 የፈፀመውን ድንገተኛ ጥቃት ተከትሎ አሜሪካኖች የሁለተኛው ዓለም ጦርነትን በይፋ እንዲቀላቀሉ ማድረጉ ይታወሳል። ይህ ብቻ ሳይሆን በቀጣዩ አመት በሄሮሽማና ናጋሳኪ ከተሞች ላይ የኒኩለር ቦንብ እንዲጣል ምክንያት ሆኗል።
ፋሽስታዊ ስርዓቱ በግብዝነት በፈፀመው ጠብ-ጫሪ ድርጊት ሀገሪቱን ወደ አላስፈላጊ ጦርነት ከማስገባቱ ባለፈ በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ ዕልቂት አስከትሏል። ገና ከጅምሩ የጃፓን ጦር መሸነፉ እርግጥ ነበር። ሽንፈቱ የአሜሪካን ጦር የተሻለ ብቃትና ብዛት ሰለነበረው አይደለም። ከዚያ ይልቅ በዋናነት ጃፓኖች የሞራል ልዕልና (የበላይነት) ስላልነበራቸው ነው። ጦርነትን ማሸነፍ የሚቻለው በኃይል ብዛት አይደለም። ከኃይል ሚዛን ይልቅ የሞራል ሚዛን ለድል ያበቃል። የአንድን ሀገር ሉዓላዊነት በመግፈፍ ወረራ የፈፀመ ኃይል ምንም ያህል ጠንካራ ቢሆን መሸነፉ አይቀሬ ነው። ምንም ያህል የጦር ኃይል ቢኖረው ሰራዊቱ ግን የትግል ሞራል ሊኖረው አይችልም። በአንፃሩ ወረራ ወይም ጭቆና የተፈፀመበት ወገን የጦር መሳሪያ ባይኖረው እንኳን ጠንካራ የሆነ ሕዝባዊ ድጋፍ እና የሞራል የበላይነት ይኖረዋል። ይሄ ደግሞ ጦርነቱን በድል እንዲያጠናቅቅ ያስችለዋል። ለዚህ ደግሞ ራሱ ህወሓትን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።
በእርግጥ ህወሓት በ17 ዓመት የትጥቅ ትግል ከፍተኛ ቁጥር የነበረውን የደርግ ሰራዊት በማሸነፍ የፖለቲካ ስልጣን ይዟል። በዚህ መልኩ የያዘውን ስልጣን ከእኩልነት ይልቅ የራሱን የበላይነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አውሎታል። በዚህ ምክንያት የህወሓት የበላይነት በሕዝባዊ አመፅና ተቃውሞ ተገርስሷል። ሆኖም ግን፣ ከላይ ከተገለፀው መሰረታዊ ባህሪ አንፃር ህወሓት እውነታውን ተቀብሎ መቀጠል ይሳነዋል። ከዚያ ይልቅ በማህብረሰቡ ላይ ፍርሃትና ሽብር በመፍጠር ለውጡን ለማደናቀፍ ጥረት ያደርጋል። ይህ ውጤታማ ሳይሆን ሲቀር ግን የሂትለር ናዚ በፖላንድ ላይ፣ በተለይ ደግሞ የጃፓኑ ፋሽስት በአሜሪካን ላይ የፈፀመው ዓይነት ድንገተኛ እና ያልተጠበቀ ወረራ ይፈፅማል።
የህወሓትን አካሄድ ቀድሞ አውቆ መግታት ካልተቻለ በስተቀር አክራሪ አመለካከት ያላቸው የድርጅቱ መሪዎች የደረሰባቸውን ሽንፈት ላለመቀበል በሚያደርጉት ጥረት ከሽብርተኝነት አልፎ በአጎራባች ክልሎች፣ ከፌደራሉ መንግስት ወይም የጎረቤት ሀገራት ጋር ጦርነት መግባታቸው አይቀርም። ቀደም ሲል በመተገለፀው መሰረት በትግሉ ሰማዕታት ስም የዘረጉት “የአንድ-ዓይነትነት” ፖለቲካ ዓላማው የትግራይን ሕዝብ ለመስዕዋትነት ማዘጋጀት ነው። የራሱን የስልጣን የበላይነት ለማስቀጠል ሲል የትግራይን ሕዝብ ከጦርነት ውስጥ ለመማገድ የሚያስችል ነው። በዚህ መልኩ በሚቀሰቅሰው ጦርነት ህወሓት መሸነፉ አይቀርም። ነገር ግን፣ በትግራይ ሕዝብ ላይ የሚያስከትለው እልቂት እጅግ የከፋ ከመሆኑ በተጨማሪ በሀገራችን ፖለቲካ ላይ ለዘመናት የማይሽር ጠባሳ ጥሎ ያልፋል።
Filed in: Amharic