>
4:35 pm - Sunday August 7, 2022

አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ  የኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝዳንት

አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ 
የኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝዳንት
ጀማል ሙሄ
ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ሲሆን የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በሊሴ ገብረማርያም ትምህርት ቤት ነው። አራት ሴት ልጆች ለነበሯቸው ወላጆቻቸው የመጀመሪያ ልጅ የሆኑት ሳህለወርቅ ዘውዴ ገና በ17 ዓመታቸው ነጻ የትምህርት ዕደል አግኝተው ወደ ፈረንሳይ በማቅናት ሞንትፔልየር (Montpellier) በምትባለው የፈረንሳይ ከተማ በሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሞንትፔልየር (University of Montpellier) የተፈጥሮ ሳይንስን አጥንተዋል። በሀገረ ፈረንሳይ ለዘጠኝ ዓመታት ከቆዩ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ የሕዝብ ግንኙነት ክፍልን ማገልገል ጀመሩ። ቆይተውም የሕዝብ ግንኙነት ክፍሉን በበላይነት መርተዋል። ከዚያም ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመዘዋወር በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች አገልግለዋል።
ወሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ በአምባሳደርነት ለመሾም ከአምባሳደር ዮዲት እምሩ ቀጥሎ ሁለተኛዋ እንስት ናቸው። በመጀመሪያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙትም ሴኔጋል ሲሆን የአምባሳደርነት ስልጣናቸውም ሴኔጋልን ጨምሮ ማሊን፣ ኬፕ ቨርዴን፣ ጊዚ ቢሳውን፣ ጋምብያን እና ጊኒን (እ.ኤ.አ 1989–1993) ያጠቃልል ነበር። ቀጥሎም እ.ኤ.አ 1983–2002 በጅቡቲ የኢትዮጵያ አምባሳደርና በኢጋድ (IGAD) የኢትዮጵያ ተጠሪ ሆነው አገልግለዋል። እ.ኤ.አ ከ2002 ጀምሮ እስከ 2006 ድረሰ በፈረንሳይ (ሞሮኮን ጨምሮ) የኢትዮጵያ አምባሳደርና በዩኔስኮ (UNESCO) የኢትዮጵያ ተጠሪ ሆነው አገልግለዋል። እ.ኤ.አ ከ2006 ጀምሮ እስከ 2009 ድረስ በአፍሪካ ህብረት (AU) እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) የኢትዮጵያ ተጠሪ ሆነው ሀገራቸውን አገልግለዋል።
ከሀያ ዓመታት በላይ በተለያዩ ሀገራትና ዓለማቀፋዊ ድርጅቶች የኢትዮጵያ አምባሳደርና ተጠሪ በመሆን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትን ያገለገሉት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ እ.ኤ.አ በ2009 የተበባሩት መንግስታት ድርጅትን (ተመድ) በመቀላቀል የድርጅቱ በመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ የተቀናጀ ሰላም ግንባታ መሪ (Head BINUCA) በመሆን ማገልገል ጀመሩ። ይህ አገልግሎታቸውም ወደ ሚቀጥለው ኃላፊነት አሸጋግሯቸው እ.ኤ.አ በ2011 ዓም የዚያን ጊዜ የተመድ ጠቅላይ-ጸሀፊ ባን ኪ-ሙን (Ban Ki-moon) አዲስ ለተቋቃመው በናይሮቢ የተመድ ጽህፈት ቤት (UNON) የመጀመሪያዋ ጠቅላይ-መሪ አድርገው ሾማቸው። በዚያም ለሰባት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ እ.ኤ.አ በሰኔ ወር 2010 የአሁኑ የተመድ ጠቅላይ-ጸሀፊ አንቶንዮ ጉቴሬስ (António Guterres) አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴን በተመድ ጠቅላይ-መሪ ስር (Under-Secretary-General) የአፍሪካ ህብረት ልዩ ተጠሪ (UN’s Special Representative to the AU) እና በአፍሪካ ህብረት ውስጥ የተመድ ጽህፈት ቤት ዋና ኃላፊ (Head of UNOAU) አድርገው ሾሟቸው እስካሁን ድረስ በዚሁ ሹመታቸው እያገለገሉ ይገኛሉ።
የአምባሳዶር ሳህለወርቅ ዘውዴ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝዳንት ሆኖ መመረጥ ይበል የሚያሰኝ ነው።  በዚህ አጋጣሚ የግለሰቧን በፕሬዝደንትነት መመረጥ የአገራችንን የፖለቲካ ገጽታ ለማደስ ብቻ ታስቦ የተደረገ የፖለቲካ ውሳኔ አድርጎ መቁጠር ተገቢ አይመስለኝም። እኚህ ሴት ከዚህ ቀደም እንደነበሩት ሲጠሩዋቸው አቤት ሲልኳቸው ወዴት ይሉ እንደነበሩ ፕሬዚዳንቶች ይሆናሉ ብዮ አላምንም። ያም ብቻ ሳይሆን አሁን በአገሪቱ ያለውም የፖለቲካ ሁኔታ እንዲህ አይነት ሁኔታን የሚፈጥር ነው ብዬ አላምንም። በመሆኑም ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ያላቸውን እውቀት፣ በመንግስታቱ ድርጅት እና በተለያዩ አገራት ያካባቱትን ሰፊ እውቀት እና ክህሎት በመጠቀም የተጀመረው እና ብዙ ፈተናዎች የተጋረጡበትን የለውጥ እንቅስቃሴ በማጠናከር እና ለአገር የሚበጅ እንዲሆነ በማድረግ እረገድ ጥልቅ ሚና ይጫወታሉ ብዮ አምናለሁ።
መልካሙን ሁሉ እየተመኘሁላቸው አገሪቱ ወደ ዲሞክራሲያዊ አቅጣጫ እንድታቀና፣ ሰብአዊ መብቶች እንዲረጋገጡ እና ሰላም እንዲሰፍን ችሎታቸው የፈቀደውን እንደሚያደርጉ ተስፋ አደርጋለሁ።
አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ባለትዳርና የሁለት ወንድ ልጆች እናት ናቸው። ዛሬ ከፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ስልጣን ተረክበዋል። መልካም የስራ ዘመን ይሁንልዎ።
Filed in: Amharic