>
10:33 am - Sunday May 22, 2022

ቦኮሐራም በምሥራቅ ኢትዮጵያ!!!  (ዘመድኩን በቀለ) 

ቦኮሐራም በምሥራቅ ኢትዮጵያ!!!
      “ብር ክፈሉን”፤ “ለቃችሁም ውጡ “!
       
ዘመድኩን በቀለ 
 
* ” ውጣ አትበለው-እንዲወጣ ግን አድርገው ” 
 
*  ሐረርጌ ሆይ !  አንቺ የየዋሆች ምደር፣ የፍቅር አድባር፤ እትብቴም የተቀበረብሽ የአባቶቼ ርስት ፈጣሪ ይድረስልሽ። አሜን። 
 
* ጅጅጋ፣ ሐረር፣ አሰቦት… እያለ ይቀጥላል፣ ይገሰግሳልም። ማነህ ባለ ሳምንት? ተረኛውን ና ወዲህ በለውማ
 የሥርዓተ አልበኝነት አደጋና ስጋት በሚገርም ፍጥነት ከዳር ሀገር ወደ መሃል ሀገር እየገሰገሰ ነው። የፌደራል መንግሥት የሚባለው አካል ምን እያሰበ እንደሆን ባይታወቅም በነገሮች ሁሉ #ጮጋ ብሏል።
~ ሐረር፦ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በውኃ ጥምና በቆሻሻ ክምር እየተቀጣች ያለች አሳዛኝ ከተማ።
ሐረር በኢትዮጵያ ውስጥ ከተቆረቆሩ ረጅም ዘመናትን ካስቆጠሩ ጥንታውያን የኢትዮጵያ ከተሞች መካካል አንዷ ናት። በዚህች ከተማ ውስጥ የሐረሪ፣ የዐማራ፣ የኦሮሞ፣ የጉራጌ፣ የትግሬና የደቡብ ብሔረሰብ አባላት በአንድነት የሚኖሩባትና ከነ ስሟም የፍቅር ከተማ ተብላም እንድትጠራ በዩኔስኮ ጭምር እውቅና ተሰጥቷት የምትገኝ ከተማ ናት።
አሁን ይህቺ የፍቅር ከተማ በመባል የምትታወቀው የሐረር ከተማ በዓለም ላይ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ እጅግ ሰብዓዊነት በማይሰማቸው አካላት ጭካኔ በተሞላበት ግፍ እንድትቀጣ የተወሰነባት ምስኪንና አሳዛኝ ከተማ ሆና ተገኝታለች። በሟቹ አቶ መለስ ዜናዊ መልካም ፈቃድ በአንድ ግምብ አጥር ውስጥ የሚኖሩትን የሐረሪን ነገድ አባላት ክልል የሚል ስያሜን በማጎናፀፍ ሐረር ከ9ኙ የኢትዮጵያ ክልሎችም ራሷን ችላ ራሷን በሯሷ እንድታስተዳድር የተደረገች ከተማም ናት። ዛሬ በክልሉ ለተነሳው መተራመስ የህውሓት መራሹ መንግሥት ዋነኛ ተጠያቂም ነው።
በሐረር የኦሮሞና የዐማራ ነገድ አባላት በቁጥር የሚበዙ ቢሆንም የሐረር ከተማን የማስተዳደሩ ሥራ ግን የሐረሪዎች ብቻ ፀጋ እንዲሆንም ተደርጎ ነው በአቶ መለስ የተደነገገላቸው። አቶ መለስ በወቅቱ ይህን ያደረገው የከፍተኛ ፍርድ ቤትና የምርጫ ኮሚሽኑ ኃላፊ ተደርገው የተሾሙት ሐደሬያዊ ግለሰብ ለህውሓት በዋሉት ውለታ መሠረት እንደሆነም ይነገራል። የሲዳማ፣ የወላይታ፣ የጉራጌ፣ የከፋ፣ የሸኪቾ ሰፋፊ ግዛቶችን ጨፍልቆ ደቡብ የሚል ክልል የሰጠው የህውሓት መንግሥት በሐረሪ ግንብ ውስጥ ለሚኖሩ የቤተሰብ አባላት ክልል የሚል ማዕረግ ሲሰጥ ቅሽሽ አላለውም ነበር።
መኖሪያቸውን በሐረር ከተማ ያደረጉ የዐማራና እና የጉራጌ ነገድ አባላት በተለያዩ ጊዜያት የሐረር ከተማን ለቅቀው እንዲወጡ ተደጋጋሚ ሙከራ መደረጉ ይታወሳል። በአሰቃቂ ግድያ፣ የንግድ ቤቶቻቸውን በማቃጠል፣ በውኃ ጥምና አሁን ደግሞ በቆሻሻ ክምር በሐረር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በግፍ ቀጥቶ ከከተማዋ ለማስወጣት ሲሠራበት የኖረ ጉዳይም ነው። አሁንም እየተሠራበት እንደሆነ ይሰማኛል።
የደቡብ ጎንደሩ የጋይንት ህዝብ፣ የምዕራብ ሸዋው የአምቦ ህዝብና የምሥራቅ ሐረርጌው የሐረር ህዝብ ገና ድሮ ነበር በህውሓት መራሹ የኢህአዴግ መንግሥት ቂም ተይዞባቸው ለቅጣት የተዘጋጁት፣ ሲቀጡም የኖሩት። ምክንያቱ ደግሞ ግልጽ ነው። ደርግን ከኢትዮጵያ ለማስለቀቅ በተካሄደው ጦርነት ህውሓትን ክፉኛ ያወደሙ ጦርነቶች የተካሄዱት በእነዚህ ሦስት ቦታዎች እንደሆኑና በእነዚህ ቦታዎችም በተካሄዱ ጦርነቶች ነባር የህውሓት ታጋዮች የሚባሉት ከህዝቡም ጭምር በገጠማቸው መከላከል ” ጀግኖቻችን ” የሚሏቸውን ታጋዮች ህይወት ያጡበት በመሆኑ እጅግ አድርገው ሲቆጩ ይደመጣሉ። እናም ህውሓት መላው ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረች በኋላ ሦስቱን አካባቢዎች ከመሠረተ ልማት ነፃ እንዲሆኑና አይቀጡ ቅጣት እንዲቀጡ አድርጋ 27 ዓመት ሙሉ አሳር ፍዳቸውን ስታበላቸው ከርማለች።
ወደ መቐለ የሚሄድ መብራት በላዩ ላይ እያለፈ ደቡብ ጎንደር እስከ አሁን ድረስ መብራት የለውም። አምቦ አሁን በቄሮ ጉልበት እየተፍጨረጨረች እንጂ የዓለም አቀፉ የእግርኳስ ፌደሬሽን ፊፋ እንኳ በአምቦ ከተማ ሊገነባ ላሰበው ፕሮጀክት ተፈጻሚነት እንዳይኖረው ሲደረግ ነው የቆየው። ለአምቦ አውሮፕላን ማረፊያ ምን ያደርግለታል እንዲል መለስ ዜናዊ። ሐረርም የውኃ ያለህ ማለት ከጀመረች እነሆ ይኸው 27 ዓመታት አለፉ።
ህውሓት ለዚህ ሴራዋ ይጠቅማት ዘንድ ኮትኩታ የክልሉ ፕሬዘዳንት አድርጋ የሾመችውና “የሐረሩ ሙጋቤ” የሚል ቅጽል ስም የተሰጠው ፕሬዘዳንትም አላት። ቆንጂት ተሾመ ስለዚህ ሰው ስትገልጽ እንዲህ በማለት ነው።
~ እሳቸው የሐረር ከተማ ፕሬዝዳንት ሆነው… ኢትዮጵያ 3 ጠቅላይ ሚኒስትሮችንና 2 ፕሬዝዳንቶችን ቀየረች። 25 ጊዜ የቁልቢው ገብርኤል ነገሠ።  እኛም….. 12 የአፍሪካ ዋንጫዎችን፣ 6 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎችን፣ 3 የኦሊምፒክ ጨዋታዎችን፣ 5 የዓለም ዋንጫዎችን … ዐየን።
ይህ ፕሬዘዳንት በ27 ዓመታት የአገዛዝ ዘመኑ ውስጥ አንድም ትምህርት ቤት ያልሠራ ክልል መሪ ሆኖ ሥልጣን ላይ ሙጥኝ በማለት እንዲኖር የተፈቀደለትና “የሐረሩ ሙጋቤ” የሚል ስም ከማትረፍ ሌላ ምንም ያልፈየደ ግለሰብ ነው። አሁንም ይኸው ሰው ነው የሐረሬ ክልል ፕሬዘዳንት።
የሐረር ከተማ የውኃ አቅርቦትን የምታገኘው ከሦስት አቅጣጫዎች በተዘረጉ የውኃ መስመሮች ነው። አንደኛው ከድሬደዋ ሐሰሊሶ አካባቢ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከሐሮማያ ኢፋ ባቴ አከባቢ ነው። ሦስተኛው የሐረር የውሓ መገኛ ደግሞ ከኤረር አከባቢ ነው፡፡ አሁን ሦስቱም የውኃ መስመሮች ተቋርጠዋል።
ከድሬ ደዋ ሐሰሊሶ የሚመጣው ውኃ የተቋረጠው በኢትዮጵያ መብራት ኃይል ተንኮል የኃል አቅርቦት እንዳይኖር በመከልከል ውኃው ወደ መስመር ገብቶ ሐረር እንዳይደርስ በመደረጉ ነው ተብሏል። በዚህም ምክንያት ውኃ በበቂ መጠን ለማምረትና ለማሰራጨት ባለመቻሉ እንደሆነ ይነገራል።
ከኤረር የሚመጠው ውኃ ደግሞ የተቋረጠው የውኃ መስመሩ በሚያልፍባቸው የኦሮሞ ነገድ አባላት በካሳና በመልካም አስተዳደር ጥያቄ ምክንያት ተገቢውን ካሳ መክፈል ባለመቻሉ ወደ ሐረር ከተማ የሚሄደውን የውኃ መስመር የአካባቢው ነዋሪዎች እንዳቋረጡት ተነግሯል። በዚህ ምክንያት የሐረር ከተማ ህዝብ በጅምላ በውኃ ጥም እንዲያልቅ ተፈርዶበት ይገኛል።
ሦስተኛውና ከሐሮማያ ኢፋ ባቴ የሚመጣው የውኃ መስመር የተቋረጠበት ምክንያት ደግሞ አስገራሚ ነው። የውኃው መቋረጥ እንደ ኤረሩ የመልካም አስተዳደር ጥያቄም አይነት አይደለም። የዚህ ለየት ያለም ነው። በአካባቢው እንደ ቦኮሐራምና እንደ አልሸባብ የታጠቁና የአካባቢውን መስተዳድር ጭምር የተቆጣጠሩ ቡድኖች የሐረሬን ክልል በደብዳቤ ጭምር ጠይቀው ነው ውኃውን ያቋረጡት።
ደብዳቤውን የጻፉት አካላት ” በአምስት ቀን ውስጥ 10ሚሊየን ብር ካልተከፈለን ለሐረር ህዝብ የሚሄደውን ውኃ ለማቋረጥ እንገደዳለን በማለት ለነው ለሐረሪ ክልል ውኃና ፍሳሽ ባለስልጣን የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ያስገቡት። በቃ ይኸው ነው።
የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ የደረሰው የክልሉ መንግሥት የውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣንም በጉዳዩ ዙሪያ መግለጫም ሰጥተው ነበር። ባለ ሥልጣኑ በሰጡት መግለጫ እንዲህ ነበር ያሉት “በሀሮማያ አካባቢ ለሚገኙ 1500 ወጣቶች ለሥራ ዕድል ፈጠራ የሚውል 10 ሚሊየን ብር በ5 ቀናት ውስጥ ይከፈለን የሚል ደብዳቤ በሀሮማያ #ኢፈባቴ ቀበሌ 01 ሊቀመንበር በኩል ደርሶናል፡፡” ብለው ነው ጉዳዩን ይፋ ያወጡት።
የሐሮማያ የ01ቀበሌ ሊቀመንበር በማኅተሙና በስሙ 1500 የአካባቢውን ነዋሪዎች ለማደረጀት በ5 ቀናት ውስጥ 10 ሚልዮን ብር በካሳ መልክ እንዲሰጠን ብሎ የመጠየቅ ድፍረትን ከየት አመጣ ?  ካሳስ መጠየቅ ያለበትና የሚገባው አንድ የቀበሌ ሊቀመንበር ነው ወይ? የሐሮማያን ቀበሌ የሚያስተዳድረው ኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ሲሆን ውኃው የሚያልፍበትን መሥመር የሚያስተዳድረው ደግሞ የፌደራሉ መንግሥት ነው። እናም ወጣቶቹን ለማድራጀትም ካስፈለገ የፌደራሉ መንግሥት በሚመድበው በጀት ነው እንጂ እንዴት ጉዳዩ የማይመለከተው ክልል ስለዚህ ነገር ተጠያቂ ሆኖ የሰው ልጆች በውኃ ጥም እንዲያልቁ ይፈረድባቸዋል?
በዚህ ምክንያት ነው የሐረር ከተማ ነዋሪዎች ላለፉት ስድስት ወራት ውኃ ተጠምተው፣ በቆሻሻ ክምርም ታፍነው በወረርሽኝ በጅምላ እንዲያልቁ የተፈረደባቸው። ክልሉም ለዚህ ህገወጥ ነውረኛ ተግባር የምሰጠው 10 ሚልየን ብር የለኝም ብሎ በአቋሙ ጸንቷል። ወጣቶቹም ከውኃ ማጣሪያ ጣቢያ ሠራተኛው ቁልፉን ነጥቀው ወስደዋል። ሞተሮቹን አጥፍተዋል። ከዚህም አልፈው የውኃ መስመሩንም ሰብረው ውኃው በከንቱ እንዲፈስ እያደረጉ ነው።
የሚገርመው ነገር እስካሁን ድረስ የፌደራል መንግሥቱ በጉዳዩ ላይ ጣልቃ መግባትን አልፈቀደም። የምሰራቅ ኦሮሚያ የሥራ ኃላፊዎች፣ የአካባቢው አባገዳዎች፣ የሐይማኖት አባቶች እና ቄሮዎች ጋር ተደጋጋሚ የምክክር መድረክ ተፈጥሮ ውይይት ቢደረግም እስከ አሁን ምንም ዓይነት መፍትሄ አልተገኘም፡፡
የሐረሩ ሕገወጥ ተግባር መፍትሔ ካላገኘ ግን በቀጣይ ወራት የዚህ ዓይነት ጋጠወጥ ተመሳሳይ ድርጊቶች በመላ ሀገሪቱ እንደሚከሰት ለመናገር ነቢይ መሆንን አይጠይቅም። ተናግሪያለሁ።
የሚገርመው የሐረር ሕዝብ በችግርና በውኃ ጥም ክልሉን ለቅቆ ሲወጣ የሚለቀቁ ቤቶችን ታሳቢ በማድረግ ቄሮዎች የለቃቂዎችን ቤት ከአሁኑ የእኔ ቤት የእኔ ቤት እያሉ በመከፋፈል ላይ መሆናቸው እየተነገረም ነው። ጉዳዩን መንግሥት አያውቀውም ማለት አይቻልም። ካወቀው ደግሞ የጉዳዩ ተባባሪ ነው ማለት ነው። ይኸው ነው።
ሐረሮች ግን በጅምላ እናልቃታለን እንጂ ከተወለድንበት ከተማ ለቅቀን የትም መሄጃ ስለሌለን እዚሁ ሆነን የሚመጣውን ሁሉ በፀጋ ለመቀበል ወስነናል ነው የሚሉት።
★ ጌታ ሆይ የዚህ ነገር መጨረሻው ምን ይሆን ?
~ #ማስታወሻ | ~ ሌላኛው የኢትዮጵያው ቦካሐራም ከሐረር አልፎ አዲስ አበባ ግርጌ በሚገኘው የአሰቦት ገዳም ላይ የሞት ድግስ አዘጋጅቶ ምቹ ጊዜ በመጠበቅ ላይ እንደሆነ ተነግሯል። በጠቅላይ ሚንስትር ታምራት ላይኔ አይዞህ ባይነት በ1984 ዓም የገዳሙ መነኮሳትና የአካባቢው ምእመናንም እንደ በግ መታረዳቸው ይታወሳል። አሁንም ያው አራጅ ቡድን ገዳሙን ከብቦ ማታ ማታ ከገዳሙ ጥበቃዎች ጋር የተኩስ ልውውውጥ እያደረገ ሲሆን በአካባቢው ያለው የመከላከያ ሠራዊት የኦሮሚያ ክልል እስካልፈቀደልኝ ድረስ ምንም ልረዳችሁ አልችልም ማለቱም ተዘግቧል።
መፍትሄ እንዲሰጡ የተጠየቁት የአካባቢው አስተዳዳሪዎችም ” ቦታው የእናንተ ስላልሆነ ለምን ለቃችሁ አትወጡም ” በማለት ለገዳማውያኑ ቁርጥ ያለ መልስ እንደሰጧቸውም ተዘግቧል።
የጠሚዶኮ ዐቢይ አህመድ መንግሥት ሴቶችን በብዛት ወደ ሥልጣን መማምጣቱ ምን አልባት መፍትሄ ይሰጥ እንደሆን እናያለን የሚሉም በርክተዋል። ሕግና ሥርዓት በጠፋበት ሀገር ” ልጄ !  ልጄ  !  በጠባኸው የእናትህ ጡት ይዤሃለሁ እያሉ ሥርዓት አልበኞችን እጃቸውን እያርገበገቡ በእናትነት ልመና ወደ መሥመር እንዲያስገቡለት አስበው እንደሆንም እንደሆንም የሚገምቱም አሉ። ለማንኛውም ጊዜው ሲደርስ ሁሉንም አብረን የምናየው ይሆናል።
ሻሎም !  ሰላም 
ጥቅምት 15/2011 ዓም
ከራየን ወንዝ ዳር።
Filed in: Amharic