>
5:14 pm - Friday April 20, 9201

የታከለ ዑማ ጊዜያዊ ም/ከንቲባነት ሹመትና ያስከተለው ተቃውሞ (አበጋዝ ወንድሙ)

የታከለ ዑማ ጊዜያዊ ም/ከንቲባነት ሹመትና ያስከተለው ተቃውሞ

 

 አበጋዝ ወንድሙ

 

ባለፉት 27 አመታት ውስጥ የአዲስ አበባ ከንቲባ በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩት የኢህአዴግ ሹመኞች አንዳቸውም አዲስ አበቤዎች አልነበሩም። አዲስ አበቤ ካለመሆንም በላይ ሆን ተብሎ ጥርስ እንዳይኖረው ተደርጎ አዲስ አበባ ባለ አደራ ከንቲባ ከነበረው ብርሃነ ዴሬሳ ውጭ ሁሉም ለማለት ይቻላል ከተሜዎች እንኳን ነበሩ ለማለት አያስደፍሩም ።

ታከለ ዑማ፣ ከተሜ  ብቻ ሳይሆን  የሸገርን ውሃ እንደ አንድ  አላፊ መንገደኛ  የተጎነጨ ብቻ ሳይሆን፣ ከተማሪነት ጊዜው ጀምሮ  በሥራ አለምም ላይ በቆየበት ወቅት ውሃዋን በሰፊው እየጠጣ የኖረባት አዲስ አበቤ ሆኖ ሳለ፣(የደሪባ አስተዳደር ጊዜውን የጨረሰ የነበረ መሆኑንና ፣ የአዲስ አበባ ምርጫ መራዘምን  ታሳቢ በማድረግ የጊዜያዊ ሹመቱ ህጋዊነት ላይ የተነሳው ውሃ የማይቋጥር ስለሆነ ) የሱ ምክትል ከንቲባ ሆኖ መሾም ለምን ይሄን ያህል አቧራ ሊያስነሳ እንደቻለ እንቆቅልሽ ሆኖብኛል

ታከለ የኢህአዴግ አባል በመሆኑ ነው እንዳይባል ባለፉት 27 ዓመታት የነበሩት በሙሉ (ከብርሃነ ዴሬሳ በቀር) ኢህአዴጎች ነበሩ፣ ኦህዴድ አባል ስለሆነ እንዳይባልም በነዚህ 27 ዓመታትም ከነበሩ ከንቲባዎች ውስጥ ሶስቱ የኦህዴድ አባላት ነበሩ። ይሄን በማየትም ነው እንግዲህ ታከለ ላይ የተነሳው ተቃውሞ እንቆቅልሽ ሆኖብኛል የምለውና ምናልባትም ከተቃውሞው ጀርባ ሌላ ነገር ይኖር ይሆን ብሎ የሚያሳስበኝና፣ ጠርጥር ገንፎም ውስጥ… እንድል የሚያደርገኝ ።

እርግጥ ታከለ ወደ ምክትል ከንቲባነት ከመሾሙ በፊት የነበረው  የፖለቲካ ሰበዕናና ተሳትፎን አስመልክቶ ባንዳንድ ሰዎች ላይ የተወሰነ ስጋት ቢኖር አስገራሚ ባይሆንም ፣ ምናልባት ይሄን ስጋት በመጠቀም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደውን ለውጥ ማደናቀፍ የሚፈልጉ ሃይሎች የበለጠ እያራገቡት ነው ብሎ መጠርጠር ግን ተገቢ ይመስለኛል።

ለማናቸውም ድንገት ከአብይ ጠቅላይ ምንስቴር መሆን ጋር  ያልሆነ ግርታ ተፈጥሮ ልዩ ነገር ተጠብቆ ካልሆነ በቀር፣ አብይም ጠቅላይ ሚንስቴር የሆነው በኢህአዴግ ሊቀመንበርነቱ እንደሆነ፣ ሀገሪቱንም ሆነ ዋና ከተማዋን አዲስ አበባን አሁንም የሚያስተዳድራት ኢህአዴግ በጥቅሉ፣ በተለይ ደግሞ የአዲስ አበባ የኢህአዴግ የፓርቲ ኮሚቴ እንደሆነ፣ ታከለም ቢሆን የኢህአዴግ ሹመኛ እንጂ በሕዝብ ምርጫ የመጣ አለመሆኑን ልንዘነጋ አይገባም።

ይሄም በመሆኑ ታከለን አስመልክቶ ሊኖረው የሚችለው ድጋፍ ወይንም ተቃውሞ ከሱ በፊት ከነበሩት ከንቲባዎች ከሰሩት ወይንም መስራት ይገባቸው ነበር  ብለን ከምናምናቸው  ጉዳዮች አንጻር መሆን ይኖርበታል እንጂ፣ ለእሱ ብቻ የሚሆን የሚያገለግል  መስፈርት ፈጥሮ መቃወሙ ምክንያታዊ ሊሆን አይችልም ብቻ ሳይሆን አሉታዊና አጠቃላይ ለውጡን አደናቃፊም ጭምር ነው።።

በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ከተመለከትነው እንግዲህ፣ታከለ በአንዳንድ ጉዳዮች  የተወሰነ ድክመቶች ቢኖሩበትም፣ ስራውን በተረከበ በአጭር ጊዜ ውስጥ የአዲስ አበባ አስተዳደርን አስመልክቶ ትርጉም ያለው ለውጥ ያሳየና ተገቢ ድጋፍና ትብብር ካገኘም ብዙ መልካም ስራዎች ለመስራት ተነሳሽነት ያለው ወጣት መሪ ሆኖ ይታየኛል።

የከንቲባነት ሹመቱን ካገኘ በዃላ የወሰዳቸውን አንዳንድ እርምጃዎች ስንመለከትም ይሄንን አስተያየት የሚያጠናክሩ ሆነው አናገኛቸዋለን። ለምሳሌ ከመንግስት ጋር ብርቱ ቁርኝትና የተለየ ግንኙነት የነበራቸው ግለሰቦች ወይንም ኩባንያዎች በከተማው መሃል ሰፋፊ መሬት ወስደው፣ለአመታት ያለምንም ልማት አጥረው ሙጃ ሲበቅልባቸው የነበሩትንና፣ ከንቲባ ከንቲባ ምክንያት በመደርደር አይነኬ የነበሩትን ስፍራዎች ባጭር ጊዜ ውስጥ ወደ መንግስት ንብረትነት በማዞር ለቀጣይ ልማት በማዘጋጀት ተጨባጭ አስተዋጽኦ አድርጓል።

በአዲስ አበባ መስተዳደር ውስጥ በህገ ወጥ መንገድ ያሉ ይዞታዎችን ለማጣራት እየተደረገ  ያለው ተስፋ ሰጪ  ክትትል፣ ውስንም ቢሆን በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ ቤቶችን በማስለቀቅ ቤት ለሌላቸው የከተማው ነዋሪዎች እንዲሰጥ ማድረጉ፣  የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን የኑሮ ፈተና በቅርብ ለመገንዘብ የተለያዩ ሰፈሮችን በአካል በመገኘትና ከነዋሪዎች ጋር ውይይት በመጀመር የወሰዳቸው እርምጃዎች ከአውቶቡስ እስከ ባቡር እንደ አንድ አዲስ አበቤ ተሳፋሪ በመሆን ከተሳፋሪዎች ጋር ውይይት በማድረግ ችግሮችን በቅርበት ለማየት ያደረገው ጥረት፣ ለረጅም ጊዜ የከተማ መታወቂያ ላይ ብሄር የሚለው መኖር የለበትም የሚለውን የዜጎች ጩሀት አዳምጦ፣ አዲስ የሚወጡ መታወቂያዎች የከተማው ነዋሪነትን ብቻ የሚያሳዩ ማስደረጉ …. ወ.ዘ.ተ. ሊያስመሰግኑት የሚገባና የበለጠም እንዲሰራ በርታ፣ ቀጥል የሚያስብለው እንጂ የሚያስወቅሰው ሆኖ አይሰማኝም ።  

ከዚህና መሰል የከንቲባው ተግባሮች በመነሳት ጭፍንና መሰረት የሌላቸውን ተቃውሞ ወደ ጎን በማድረግ በተጨባጭ ለምሳሌ የአዲስ አበባ ወጣቶችን የፖሊስ አፈሳና እስር አስመልክቶ የሰጠውን ሀሰተኛና ያልተገባ አስተያየት፣ ሌሎች ግልጽነት የጎደላቸው አሰራሮችን የሚባሉ ለምሳሌ ተደረገ የተባለ ለወጣቶች የመሬት እደላ፣ በእርግጥም ተደርጎ ከሆነ…  ወ.ዘ.ተ. መውቀስና እንዲያስተካክል መጠየቅ አግባብና ገንቢም ስለሚሆን ትኩረት ብንቸረው የተሻለው መንገድ ነው የሚል እምነት አለኝ።

ከዚህ በተረፈ አጠቃላይ የስራ ትጋቱና ከተማዋን የሚያስተዳድርበት መንገድ የተሳሳተ ነው ብለን ካመንን ደግሞ፣ አግባብ ባለው መንገድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን አሳምኖ በሚቀጥለው ምርጫ የተሻለ ሰው ለመምረጥ እንቅስቃሴ ማድረግ ከፊታችን ያለው ብቸኛ አማራጭ ነው።

Filed in: Amharic