ቹቹ አለባቸው
” ወይ ባልዘፈንሽ: ከዘፈንሽም ባላሳፈርሽ” ይባላል
ይች ድንቅ አማራዊ አባባል:ልብ ላለዉና የሰወችን ሀሳብ ለማዳመጥ/ለመስማት ዝግጁ ለሆነ ሰዉ ሁሉ: እጅግ ጠቃሚ ናት። ማእከላዊ ነጥቧም: አንድን ነገር ዘለህ አትጀምር: ከጀመርከዉ ደግሞ ያለምንም ወለም ዘለም: በዉጤታማነት ከዉን ለማለት ነዉ። ስለሆነም: ልብ ያለዉ ልብ ይበል።
ሰሞኑን ደግሞ ወጉ ሁሉ: ስለ ሰላማዊ ሰልፍና የኦሮማራ ነገር ሁኗል። የአጀንዳችን መብዛቱ። ለሁሉም በነዚህ ሁለት አጀንዳወች ዙሪያ: ድጋፍም ሆነ መለስተኛ ተቃዉሞወችን እየሰማሁ ነዉ። ለጊዜዉና የነገሩን ስር / የተቃዉሞዉን ጭብጥ በደምብ እስክረዳዉ ድረስ: በኦሮማራ ዙሪያ የሚነሳዉን ነገር ዘልየ: በቀጣይ: የጽንሰ ሀሳቡን ደጋፊወቹንና ተቃዋሚወች: አመለካከት: የሚደግፉበትንና የሚቃወሙበትን ምክንያትና ተገቢነተት: የግሌን አስተያየት በማካተት በስፋት እመለስበታለሁ። ለዛ ሬው ሰሞኑን ሊካሄዱት ሰለታሰቡት ሰላማዊ ሰልፎች ብቻ፡ ሀሳቤን መሰጠት ፈልጊያለሁ፡፡
1. የሰልፎቻችን ነገር:-
ለዛሬዉ ማለት የፈለግኩት: ሰሞኑን በአማራ ክልል አንዳንድ ከተሞች: ስለተጠሩት ስላማዊ ሰልፎች ጉዳይ ነዉ። እስካሁን እንደተረዳሁት ከሆነ: ጠቅለል ብለዉ ሲታዩ: የሰልፎቹ አላማ ወጥና ተመሳሳይ ናቸዉ። ይሄዉም:-
1. በወልቃይት ጠገዴና ራያ አካባቢወች: በእብሪተኛዉ ህወሀት አማካኝነት:በአማራወች ላይ እየደረሰ ያለዉን: መፈናቀልና ግድያ ማዉገዝ: ለተጎጅ ወገኖቻችን አጋርነትን መግለጽ።
2. ሁለተኛዉና ከአንደኛዉ አላማ ጋር የሚተሳሰረዉ የሰልፉ አላማ ደግሞ: የወልቃይት ጠገዴና ራያ የአማራ ማንነት ጥያቄወች መልስ እንዲያገኙ መጠየቅ ነዉ። አሁን አሁን የራያ ጥያቄ: የነገሮች መደበላለቅ እሰማበታለሁ። ከባድ ጥንቃቄ ቢደረግ እላለሁ። አሁን በወጥ ግንዛቤ ጥያቄዉን ለማስመለስ በጋራ እንቁም: ወሳኙን ጥያቄ ካስመለስን በሁዋላ: እንደ ቤተሰብ የሚታይ ነገር ካለ: በቤተዘመድ ሽማግሌ የሚቋጭ ይሆናል።
3. በሶስተኛ አላማነት የሚታየዉ የሰልፎቻችን አላማ ደግሞ: በጣናና ሀይቅና ላሊበላ ቅርስ ላይ እየደረሰ ያለዉን ጥፋት: ለመንግስትና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሰማትና መፍትሄ እንዲሰጥ ለመጠየቅ ነዉ።
እንግዲህ በኔ ግንዛቤ መሰረት: የሰልፎቹ ዋና ዋና አላማወች ከላይ ጠቅለል አድርጌ ባስቀመጥኳቸዉ ጭብጦች ዙሪያ የሚታዩ ናቸዉ ብየ አምናለሁ። እኔ በግሌ: ስለነዚህ ስላማዊ ሰልፎች : አስፈላጊነትና ወቅታዊነት: እንዲሁም ሰልፎቹ ሊያስገኙት ስለሚችሉት ዉጤት: ምን ትላለህ ? ተብየ ብጠየቅ መልሴ የሚሆነዉ “ዝምታ ነዉ መልሴ” የሚል ይሆናል። ለአንድ ነገር የምትሰጠዉ ምላሽ ዝምታ ከሆነ: በጉዳዩ ዙሪያ አቋም ለመዉሰድ: ተቸግረሀል ማለት ነዉ። ስለሆነም: ነገሩን በዝምታ ታልፈዉና: ግን ደግሞ ስለ ነገሩ እየተብሰለሰልክ: የሚሆነዉን ነገር በአንክሮ ትከታተለዋለህ።
ይሁን እንጅ: እኔ ለጉዳዩ ያለኝ ምላሽ: ዝምታም ሆነ ሌላ:ሰልፎቹ ግን በተያዘላቸዉ ፕሮግራም መሰረት መከወናቸዉ የሚቀር አልመሰለኝም። ስለሆነም: ሰልፎቹ መካሄዳቸዉ ካልቀረ: የሚከተሉትን ጥያቄወች ላንሳና: የሰልፉ አሰተባባሪወች: የሚከተሉትን ጥያቄወች ግምት ዉስጥ አስገብታችሁ: እንድትንቀሳቀሱ እመክራለሁ።
2. ጥያቄ አለኝ?
1. እንዴዉ ለመሆኑ: ሰልፎቹ ማእከላዊ አመራር ያላቸዉ: በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ የሚመሩ ናቸዉ? ከሆነስ አመራሮቹ ይታወቃሉ? ነዉ ወይስ እንደ አካባቢዉ በመሰለኝና በተለምዶዉ መንገድ የሚካሄዱ ሰልፎች ናቸዉ?
2. የነዚህ ሰልፎች አላማ: ካሁን በፊት ከካሄድናቸዉ ሰልፎች አላማወች በምን ይለያል? What is New?
2. በሰልፉ የሚነሱት ጥያቄወች: ለማን ነዉ የሚቀርቡት? ለፌደራሉ? ወይስ ለክልሉ መንግስት? የትኞቹ ጥያቄወች:ለማን?
3. አነዚህ ጥያቄወች: በሚመለከታቸዉ አካላት ዘንድ: ወቅታዊና ተገቢ መልስ ባያገኙ: ቀጣዩ የሰላማዊ የትግል አግባብ ምን ይሆናል? ለመሆኑ በዚህ ልክ ታስቦበታል? ነዉ እንደተለመደዉ: ጩኸታችንን በአደባባይ አሰምተን ወደ ቤታችን ለመመለስ ነዉ ያሰብነዉ?
ብቻ እንግዲህ ነገሩ የማይቀር እስከሆነ ድረስ: እነዚህን ሰላማዊ ሰልፎች “ወይ ባልዘፈንሽ:ከዘፈንሽም ባላሳፈርሽ” የሚለዉን አባባል እንደ መርህ በመጠቀም : ልንከዉናቸዉ ይገባል። ጊዜና ጉልበት እንዲሁም ገንዘብ መፍሰሱ ካልቀረ: ሰላማዊ ሰልፎቹ: እጅግ ሰላማዊ: አማራዊ ባህልን የተላበሱ: ለአንዳንድ “ወፈፌወች” መጠቀምያ የማይሆኑ: ከመቸዉም ጊዜ በላይ ብስለትን የተላበሱ: በታቀደና በተደራጀ መልኩ የተመሩ: እንዲሁም: ለመንግስት ጠንካራና ግልጽ መልእክት የሚያስተላልፉ: ሰላማዊ ሰልፎች ሆነዉ እንዲጠናቀቁ መደረግ አለበት።
3. ጥሪ ለትግራይ ህዝቦች (በተለይም ወጣቱ ):-
በመጨረሻም: በሁሉም ሰልፎች ላይ: ወንድም ለሆነዉ ለትግራይ ህዝብ : በተለይም ለወጣቱ ክፍል:የሰላምና የእንተባበር ጥሪ ማቅረብ አለብን። ጠባችን ከ”ወንበዴዉ ” የህወሀት ቡድን ጋር እንጅ: ከትግራይ ህዝብ ጋር አለመሆኑን: ስለሆነም: የአማራ ህዝብ የዚህን ወንበዴ ትእቢት ለማስተንፈስ በሚያካሂደዉ: የሞት ሽረት ተግል ዉስጥ: የትግራይ ህዝብ: በተለይም ወጣቱ: ሲሆን- ሲሆን: ከአማራ ጎን ተሰልፎ ” ወንበዴዎቹን” እንዲታገላቸዉ: ካልሆነ ደግሞ: የአማራ ህዝብ ለነጻነቱ በሚያደርገዉ ተጋድሎ ላይ በእንቅፋትነት እንዳይቆም መጠየቅ ያስፈልጋል።
እናንተ የትግራይ ወጣቶች አንዴ ብቻ ስሙኝማ። ይሄ ክፉ ቀን ማለፉ አይቀርም። የህወሀትና የአማራ ህዝብ አብሮነት ጉዳይ ሞቶ ተቀብሯል። ነገር ግን የአማራና የትግራይ ህዝቦች ግንኙነት: እኛ ወደድነዉም ጠላነዉም: እንደገና መታደሱ አይቀርም። ይሄ እዉን እንዲሆንና በፍጥነት ወደ ወዳጅነታችን እንድንመለስ ካስፈለገ ደግሞ: ሳይንሳዊ ያልሆነዉን ” ህወሀትና የትግራይ ህዝብ አንድ ናቸዉ ” አሮጌ አባባል: ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ : ከትግራይ ወጣቶች ጭንቅላት ዉስጥ ማስወገድ ያስፈልጋል።
አንድ ነገር ግርም ይለኛል። ይሄዉም ” የትግራይ ህዝብና ህወሀት አንድ ናቸዉ” የሚለዉ ሀሳብ ሰባኪ የፖለቲካ ቄሶች: አርጅተዉና ገርጅፈዉ : ወደ አይቀሬዉ ቤታቸዉ እያመሩ ባሉበት ወቅት: የትግራይ ህዝብ በተለይም ወጣቱ ክፍል:እንዴት በ21ኛዉ ክ/ዘመን : አሮጌ ሀሳብ ተሸክሞ ሲንገላታ ይዉላል?