>

ግልፅ ደብዳቤ - ለአቶ ለማ መገርሳ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር

ግልፅ ደብዳቤ – ለአቶ ለማ መገርሳ
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር
ሀብታሙ አያሌ
” በታሪክ በቅርስ እና በሃይማኖት ስርአት ላይ አደጋ ስለተደቀነበት ስለ አሰቦት ገዳም በጭንቅ መውደቅ እለምንዎታለሁ
በ13ኛው መቶ ክፍለዘመን በአቡነ ሳሙዔል የተመሰረተው በቀድሞ ሐረርጌ ክፍለ ሀገር በአሁኑ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሀረርጌ ሚኢሶ ወረዳ የሚገኘው የአሰቦት ገዳም መነኮሳት የድረሱልን ጥሪ እያሰሙ መሆኑ ተደጋግሞ ቢነገርም እርስዎና መንግስትዎ ዝምታን የመምረጣችሁ ምክንያት ፈፅሞ ግልፅ አይደለም ።
ዛሬ በአገራችን ከፍተኛውን የፖለቲካ ስልጣን እና የፀጥታ ተቋማት የተቆጣጠረው በእርስዎ ስም እየተጠራ ያለው “ቲም ለማ ” የተሰኘው ቡድን መሆኑ በሁሉ ዘንድ የታወቀ ነው። በተለይም እርስዎ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዘዳንት ብቻ ሳይሆኑ እራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በይፋ እንደተናገሩት በቤተ መንግስቱም ተፅኖ ፈጣሪና አመራር ሰጪ ነዎት።
በተለይም በሁሉ ዘንድ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ህዝብ ህወሓትን የታገለበት ምክንያት መልክ ቀይሮ እየተደገመ መሆኑን በግልፅ በሚያሳይ ሁኔታ እርስዎ በሚመሩት ድርጅት የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) በኩል ስልጣን ወደ አንድ ወገን (የአንድ ብሔረሰብ ተወካይ ነን በሚሉ) አካለት እጅ ተከማችቶ ሳለ በክልልዎ ስርዓት አልበኝነት መንገሱ ምክንያቱን መረዳት ተስኖናል።
የሐረር ህዝብ በተደራጁ ወንበዴዎች እጅ ወድቆ በውሃ ጥም ሲቀጣ የሚያስጥለው አልተገኘም። በወለጋ የታጠቁ ኃይሎች ህዝቡን አስገድደው እየዘረፉ እና መሳሪያ እየነጠቁ ወታደራዊ ስልጠና ጭምር ሲሰጥ መንግስትዎ ፀጥታን በማስከበር ለዜጎች ዋስትና ሲሰጥ ማየት አልተቻለም።
በተለይ ከድሬዳዋ ሐረር በጭራሽ በሰላም ወጥቶ መግባት የማይቻልበት ደረጃ ተደርሷል። ይህው በዚህ ሁሉ የህዝብ ጭንቀት ውስጥ አሁን ደግሞ በክልልዎ የአሰቦት ገዳምና መነኮሳት ለአደጋ እየተጋለጡ ነው።
የአሰቦት ገዳም መነኮሳት በታጣቂዎች ተከብበናል፤ ይሄን የዘመናት ታሪክ ያለው ገዳም ለቅቀን እንድንወጣ እየተገደድን ነው፤ የድረሱልን ጥሪያችን ሰሚ አጥቷል በማለት የጭንቅ ጥሪያቸውን ለኢትዮጵያ ህዝብ ለማቅረብ ተገድደዋል። ይህው ከጥቅምት ሰባት ቀን ጀምሮ ገዳሙ ባልታወቁ ሽፍቶች እንደተከበበ ነው።
ከሁሉ በላይ የሚያስገርመው በእርስዎ አመራር ስር ያሉት የሜኤሶ ወረዳ አስተዳዳሪዎች ከታጣቂዎቹ ጎን በመሆን ገዳሙን ለቀው እንዲወጡ መነኮሳቱ ላይ ጫና እየፈጠሩ መሆኑምን መነኮሳቱ ጥልቅ በሆነ ሐዘን እየገለፁ ነው። ቤተክህነትም የእርስዎ መንግስትም ይደርሱላቸዋል የሚለው ተስፋ እየተሟጠጠ ከዛሬ ነገ ምን ይፈጠራል የሚለው ለሁላችንም ጭንቅ ሆኗል።
መቼም ለዚህ ችግር የህወሓትን አኩራፊ ኃይል መጠርጠር በራሱ የነውር ሁሉ ነውር ይመስለኛል። እርስዎ እና ድርጅትዎ የክልሉ መንግስት ነዎት። ሁለት መንግስት አለ ባዮቹንም ሁለተኛ የተባለውን መንግስትም የኢትዬጵያ ህዝብ አያውቀውም። ለማንኛውም አደጋ ተጠያቂው እርስዎና መንግስትዎ እንጂ በህግ ስልጣን መያዝዎ ከሚታወቀው ከእርስዎ ውጪ ያለ ኃይል አይደለም። ከህግ ውጪ አለሁ የሚልን እንዳይኖር ማድረግ የእርስዎ ኃላፊነት እንደሆነም አያከራክርም። እባክዎ ታሪክ እና ቅርስ ሳይወድም መነኮሳት በመሰዊያው ስር እንደ ጧፍ ሳይነዱ ፈጥነው እንዲደርሱ “ሱስ ነው” ባሉት በኢትዬጵያ አምላክ ስም እማፀንዎታለሁ።
Filed in: Amharic