>

በአባቱ ውድማ የተኛውን በሬ ... ነካክተው ቆስቁሰው አደረጉት አውሬ!!!

በአባቱ ውድማ የተኛውን በሬ 
ነካክተው ቆስቁሰው አደረጉት አውሬ!!!  
ዘመድኩን በቀለ
~ ነገ መላው ዐማራ በላሊበላ፣ በጣናና በፋሲል ግንብ ውድመት ዙሪያ ድምጹን ያሰማል። እግረመንገዱንም ለራያና ወልቃይት ድምፁን ያሰማል። ከዚያ በኋላ ምን ምላሽ እንደሚገኝ አብረን እናያለን።
~ በሕገ መንግሥት ያልተወሠደ ሀገር በሕገ መንግሥት ማዕቀፍ ሊመለስ አይችልም። ወልቃይትና ራያ የሚመለሡ ከሆነም በሄዱበት በተወሰዱበት መንገድ ብቻ ነው። ያም ከህግ ማዕቀፍ ውጭ ማለት ነው። በሕግ አግባብ ያልወሰድከውን ነገር በሕግ አግባብ አታስመልስም።
ለማንኛውም በመጨረሻ ጊዜም ቢሆን እውነታዎች እየወጡ ነው። አርቴፍሻሉን የኢትዮጵያ ክልል የፈጠሩት የክልል ፈጣሪዎቹ ህውሓቶች አሁን ላይ የመጨረሻ ኑዛዜአችውን እየተናዘዙ ነው።
“ዐማራ የሚባል ክልል አልነበረም። ዐማራም ሆነ ኦሮሚያ፣ አፋር፣ ቤኒሻንጉል ወዘተ የሚባሉት ክልሎች የተፈጠሩት በዚህ ሕገመንግሥት መሠረት ነው።” አራት ነጥብ ብለዋል አይተ ጌታቸው ረዳ።
እኔ በበኩሌ ከህውሓት ሰዎች መካከል እንደ አቶ ጌታቸው ረዳ የምወደው ሰው የለም። ጌች ማለት ግልጽ ሰው ነው። በተለይ ከቀማመሰ በቃ የዋሕነት ያበዛል። ቆንጀ ካየማ በቃ አለቀ የመጨረሻ ደግ ይሆናል አሉ። ሰውየው ብቸኛና የራያ ዐማራ ሆኖ በህውሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴም ውስጥ የተካተተ ዐማራ ነው። ልክ እን ኦባማ ቁጠሩት። እናም ጌቾ የራያ ዐማራም ስለሆነም ነው መሰለኝ ትግርኛውም ብዙ ውስብስብ አይደለም። በጣም ግልፅ አማርኛ የሚያወራ ነው የሚመስለው። በተለይ ትግሬዎቹ በትግርኛ ኢንተርቪ አድርገውት ጌቾ ትግርኛ ነው ብሎ ሲያወራ ስትሰሙት በፍፁም ትግርኛ እንደማይችል ትረዳላችሁ። ትግርኛ በአማርኛ የሚያወራ ሰው ቢኖር ጌቾ ብቻ ነው።
በነገራችን ላይ ህውሓት ከመለስ ዜናዊ ሞት በኋላ ተናጋሪ ሰው አልወጣላትም-
* አቶ አባይ ፀሐዬ እናስተነፍሳቸዋለን ብሎ ራሱ ተንፍሶ አረፈው።
* አቶ ስብሃት አክርካሪውን ሰብረነዋል ብሎ ራሳቸው ተሰብረው መቀሌ መሸጉ።
በረከትም እንደዚያው ጠፋ፣ ደብረ ጽዮን እንደምታዩት ነው ንግግር ፀጋው አይደለም። አቶ ስዩም አንደበቱ ተዘግቷል። ኬሪያ እንኳ ሲያቅለበልባት ተናግራ በደብዳቤ ንግግሬን አስተካክሉልኝ ብላ እስከማስፈራራት ደርሳ እያየናት ነው። በአጠቃላይ በእውነት ስለእውነት እንነጋገር ከተባለ አቶ መለስ ዜናዊ የህውሓትን ምላስ ጭምር ይዞ ነው መቃብር የገባው። መለስ ማለት ችግር ፈጥሮ ችግሩን ራሱ በምላሱ ይፈታ የነበረ ሰው ነው። ነገር ግን አንድም ሰው ሳያበቃና ሳይተካ ላይመለስ ሄደ። ጨረቃ ላይ እኮ ነው የጣላቸው።
ጋሽ ጌታቸው ማለት ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል የሚባልለት ፎልፏላና ቦዥቧዧ ዓይነት ሰውም ነው። ለምን እንደሆን አላውቅም ጋሽ ጌታቸው መድረክ አግኝቶ ሚድያ ላይ ከወጣና እሱ የሚቃወመው አጀንዳ ካለና በዚያ ጉዳይ ላይ መግለጫ ከሰጠ ያ ጋሽ ጌታቸው የሚቃወመው ጉዳይ ብዙም ሳይቆይ መቋጫ ያገኛል።
ማሳያ ~ ፩
የኦሮሚያ ወጣቶች ለተቃውሞ ይወጣሉ። የወጣቶቹ ቁጣ እያየለ ይመጣል። ህውሓት ደግሞ ተቃውሞውን ለመቀልበስ ቀን በቀን መግደልን ሥራዬ ብላ ትይዛለች። በዚህን ግዜ የህዝብ ግኑኝነት ኃላፊ የነበረውን ሰው ጉዳዩን አርግቦ መግለጫ ለጋዜጠኞች እንዲሰጥ ጋሽ ጌችን ከፊት ወንበር አምጥታ ትሰይመዋለች። ጌች ሆዬ በዛ ያለ የጋዜጠኞች ማይክራፎን ከጠረጴዛው ላይ ሲያይ አይወበራ መሰላችሁ? ” ሰይጣናም፣ አጋንንታም ” ብሎ በጅምላ ታቃዋሚውን ኦሮሞ ሁሉ ሙልጭ አድርጎ አይሰድብ መሰላችሁ። ያን ጊዜ ነው በትንሽ አካባቢዎች ብቻ ተወስኖ የነበረው የኦሮሞዎች ተቃውሞ እንደ አብዮት ፈንድቶ መላውን አሮሚያን አጥለቅልቆት አረፈው። ተቃዋሚዎቹ እነ ጀዋርም የጌችን ስድብ ህዝቡን ለመቀስቀሻነት በደንብ ተጠቀሙበት። ይሄ የሆነው እንግዲህ በጌቾ ከመስመር የወጣ ድንፋታ ምክንያት ነው።
ማሳያ ~ ፪
ጎንደሮች ሰላማዊ ሰልፍ ያደርጋሉ። በሰላማዊ ሰልፉ ላይም መፈክር ይዘው ይወጣሉ። መፈክሩ ደግሞ ትንቢታዊ መፈክር ነበር። ህውሓት እንደሚፈርስ፣ አቦይ ስብሐት ድራሽ አባታቸው እንደሚጠፋና ሌሎችም መፈክሮች ተይዘው ነበር ወደ አደባባይ የወጡት። ነገር ግን ህውሓትን ያበሳጨው መፈከር ” በኦሮሚያ ምድር የሚፈሰው የኦሮሞዎች ደም የእኛም ደም ነው ” የሚለው ነበር። ይሄን መፈክር ስትሰማ  ህውሓት ነዘራት። ወባ እንደያዘውም ሰው አንቀጠቀጣት።
የሆነ ጊዜ የህውሓት የነፍስ አባቷና ፈጣሪዋ የነበረው አይተ መለስ ዜናዊ አስቀድሞ ” ኦሮሞና ዐማራ የተስማማ ዕለት ያን ጊዜ የህውሓት ነገር እንዳበቃ ቁጠሩት ” ብሎ ነግሯቸው ነበርና ደነገጡ። ደንግጠውም አልቀሩ ይሄንኑ ሆድ ያባው ብቅል ያወጣዋል የሆነ አይተ ጋሽ ጌታቸው ረዳ የተባለውን ሆደ ቡቡ ሰው እንዲያስፈራራ ወደ ራዲዮ ፋና አንደርድረው ይልኩታል።
ጌቾ ሆዬ ከዛሬዋ ቆዳዋን ለውጣ የለውጥ አቀንቃኝ ተብላ ከመጣችው የሰላም ሚንስትር ተብዬዋ ወሮ ሙፈሪያት ከማል ጋ ሆኖ በፋናው ጋዜጠኛ ብሩክ እየታጀበ የድንፋታ መዓት ያወርደው ጀመር። ” እንዴት አለ ጋሽ ጌቾ ፤ እንዴት እሳትና ጭድ ያደረግናቸው ዐማራና ኦሮሞ ሊስማሙ ቻሉ?  20 ዓመት የተደከመበት የጥላቻ ግንብ እንዴት ጎንደር ላይ ሊናድ ቻለ?  ይሄ ነገር ትክክል አይደለም ብሎ አበደ ፣ አረፋ እየደፈቀ አጥብቆ ለፈለፈም ጮኸም፣ አንባረቀም ” ወዳጄ ፒፕሉ ይሄን የጌቾን ድንፋታ ሲመለከትና ሲሰማ ጊዜ ጭራሽ ባነና ከእንቅልፉ ነቃልሃ። ለካስ የሚያጣሉን፣ እሳትና ጭድ ያደረጉን፣ የሃሰት የጥላቻ ሃውልት አኖሌ ላይ የገነቡልን እነሱ ናቸው አለልህና የተቃውሞ ዙሩን አከረረው። ቄሮ ፋኖ፣ ኦሮማራ ወዘተ ብሎ ያካልባቸው ጀመር። በመጨረሻም የሆነው ሆነ። አሁን ጌቾም ከአዲስ አበባ ጠፋ። መቀሌም ከተመ።
አዲሱ የጌቾ ትንቢት ፦ 
ዛሬ ደግሞ አንድ የጌቾን ቪድዮ በዚሁ በማኅበራዊ ሚዲያ ሲመላለስ ዐየሁና ቢገርመኝ ጊዜ ጠየቅኩ። ጎበዝ ይሄ ነገር የድሮ ነው አዲስ ብዬም ጠየቅኩ። ኧረ አዲስ ነው አሉኝ። እንግዲያው ቆይ እንደዚያ ከሆነማ ይሄ ሆደ ቡቡ የሆነ ሰው በቅርቡ መፍትሄ የሚያመጣ ትንቢት መናገሩ አይቀርም አልኩና ጆሮ ሰጥቼ አዳመጥኩት። እውነትም የፈራሁት አልቀረም ጌች ሆዬ እውነታውን አውጥቶ ሲዘረግፍ አላየው መሰላችሁ።
★ ዐማራና ኦሮሚያ የሚባል ክልል የፈጠርነው እኛ ነን። እናም ወልቃይትና ራያም የትግራይ እንጂ የዐማራ አይደሉም ” አራት ነጥብ የሚል ቃና ያለው እንደድሮው በድንፋታ ሳይሆን የድንፋታ ታናሽ ወንድም በሚመስል ድምጽ ሲናገር ሰማሁት።
~ ሕገ መንግሥቱ የህውሓት መተደዳደሪያ ደንብ ነው። እናም ይሄ ሕገ መንግሥት በተጻፈና ለውይይት ቀርቦ በጸደቀም ጊዜ ደግሞ ዐማራው በሂደቱ ላይ አልተወከለም። ስለዚህ እኛ ዐማሮች ይህን ሕገ መንግሥት አንቀበለውም በማለት ላለፉት 27 ዓመታት ዐማሮቹ እሪሪሪሪ ሲሉ መክረማቸውን ሁላችንም ምሥክሮች ነን።
~ ህውሓት ሕገ መንግሥት ተብዬውን ከማጽደቋና የኢትዮጵያውያን መተዳደሪያ ከማድረጓ በፊት በ1984 ዓም
አስቀድማ ከሕገ መንግሥቱ መጽደቅ በፊት ከጎንደር ወልቃይትን፣ ጠገዴን፣ ከወሎ ራያን አላማጣና ኮረምን ሰርቃ በመውሰድ ዐማራውን ህዝብ በግድ ትግሬ ነህ ብላ ስታበቃ አሳሪውን ሕገ መንግሥት በ1987 ዓም አጽድቃ ከእንግዲህ ወዲህ ችግራችን የሚፈታው በዚህ ወረቀት ብቻ ነው ብላ ጉዳዩን ጠረቀመችው። ዐማሮቹም ችግራቸውን እንዳይጠይቁ በዐማሮቹ ላይ እነ በረከት ስምኦንን ሹማ ጠርንፋ አፋቸውን ለጎመችው።
~ ልብ በሉ ወልቃይቶች ዐማራ ነን ለማለት መጀመሪያ ዐማራ አይደላችሁም ያላቸው ትግሬ ጋር ሄደው ማመልከት አለባቸው። ዐማሮቹ ዐማራነታቸውን እንዲያረጋግጥላቸው መጀመሪያ ደጅ የሚጠኑት ዐማራነታቸውን በጉልበት ቀምቶ ትግሬ ናችሁ ያላቸውን የትግራይ መንግሥት ነው ማለት ነው።
~ ይቀጥሉና የትግራይ መንግሥት ዐማራነታችንን አልቀበልም ብሏል ብለው ዐማሮቹ የሚመጡት ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት ነው። በዚያ በትግራይ ያላቸውን ጣጣ ጨርሰው እዚህ አዲስ አበባ ሲመጡ ደግሞ እዚህም ዋና ሆና የምትጠብቃቸው የፌደሬሽን ምክርቤቱ ሰብሳቢ ዳኛ የሆነችው የህውሓቷ ዋና የሥራ እስፈጻሚ ኬሪያ የተባለች ነውጠኛ አክራሪ የህውሓት ፋኖ የሆነች ሴት ናት።
ከዚያ ከሳሽ ዐማራ ምን ይላል?
አባትየው ዳኛ
ልጅየው ቀማኛ
ዳኛውም ዝንጀሮ መፋረጃው ገደል፣
እምን ላይ ተቁሞ ይነገራል በደል፡፡
እያለ ይቆዝማል። ያንጎራጉራል። ቀን እስኪገጥም ጥርሱን ያፋጫል።
የእኔው ሆደ ቡቡ ጋሽ ጌቾ ዛሬ ይሄንኑ ነገር ነው ያጠናከሩት ። አፍረጠረጡት እኮ። በቀላል አማርኛ ጋሽ ጌቾ ዛሬ አስረግጦ የነገረን ነገር ቢኖር ” አሁን የሚታዩትን ክልሎች የፈጠርናቸው እኛ ህውሓቶች ነን፤ እናም እኛ የፈጠረነውን ክልል መቃወም ነውር ነው የሚል ነው።
ወዳጄ ጽዋው ሞልቷል። ህውሓት ቀስ በቀስ ከመላው ኢትዮጵያ ተጠርጋ መቀሌ ከትማለች። ከሱማሌ ተጠርጋ ወጥታለች። ከሁሉም ክልሎች ተጠርጋ አቅሟን አጥታለች። ችግሩ አንገቷ ስር ደርሷል። ራያና ወልቃይት መቀሌ አፍንጫ ስር ናቸው። ህውሓት ደግሞ አልተለወጠችም። በውይይትም አታምንም አሁንም እንደድሮው በመግደል ነው የምታምነው። መግደል ደግሞ ተቃዋሚ ያበዛል።
የህውሓት ታጋይ የነበረው ታጋይ ሓየሎም ዓርአያ እንዳለው ” ወደ ሕዝብ መተኮስ የጀመረ መንግሥት መውደቂያው ቀርቧል ማለት ነው ” እንዳለ ሁሉ ህውሓት ሳያበቃላት አይቀርም።
ለዚሁም ምልክቱ ነገ ዕሁድ በመላው ዐማራ በራያና በወልቃይት ጉዳይ ድብልቅልቅ ያለ ሰላማዊ ሰልፍ ተጠርቷል። ይሄ ማለት ለህውሓት ከባድ መልዕክት ነው የሚሆነው።
ሻሎም !  ሰላም !
Filed in: Amharic