>

የአማራ ብሔርተኛ መሆን ለኢትዮጵያ ጸጋ እንጅ አደጋ አይሆንም!!!  (አቶ ገዱ አንዳርጋቸው)

የአማራ ብሔርተኛ መሆን ለኢትዮጵያ ጸጋ እንጅ አደጋ አይሆንም!!! 
አቶ ገዱ አንዳርጋቸው
☞ለብዙ ዓመታት አማራ ኢትዮጵያን ሲገዛ ኖረ ፣ ነገር ግን ለአማራ ህዝብ የሰጠው የተለየ ጥቅም ምንድን ነው ?
☞ አማራ ሲበዛ ሱሰኛ ሕዝብ ነው ፡፡ ሲበዛም ከሱስ ለመላቀቅ ይከብደዋል ፡፡ አማራን የተጠናዎተው ሱሰኝነት በቀላሉ የሚወገድ አይደለም ፡፡ ይህም ሱሰኝነቱ ኢትዮጵዊነት ነው፡፡ የአማራን ብሔርተኝነት አማራ አልፈጠረውም ፡፡>> “የአማራ ብሔርተኝነት ለኢትዮጵያ ፀጋ እንጅ አደጋ አይሆንም”
አቶ ገዱ ይቀጥላሉ
አማራ ራስ ወዳድ ቢሆን ኖሮ ዘመናዊ ትምህርትን ከአብራኩ በወጡት መሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያመጣ ትምህርት ቤቱን ሰሜን ሸዋ ላይ ፣ ጎጃም ላይ ፣ ወሎ ላይ ወልቃይት ጸገዴ ላይ ፣ ራያና ኮረም ላይ ፣ ጎንደር ላይ ፣ ባስተከለ ነበር። ለዘመናት የአማራ ምስኪን እናቶች በድንጋይ ወፍጮ ባልፈጩ ነበር ፤ ለዘመናት ቅጥቅጥ ድግጣ እንጨት እያበራ በጨለማ ውስጥ ባልኖረ ነበር ፣ ለዘመናት በትንሹ ትራኮማና ጉንፋን በሽታ እየተጠቃ ባልሞተ ነበር ፣ በትራንስፖርት እጦት በባዶ እግሩ ረዥም ኪሎሜትሮችን እያቆራረጠ እሾህና ድንጋይ ባላንገላታው ነበር ፤ ለአመታት በባህላዊ መገናኛ ዘዴዎች ባልተጠቀመ ነበር ፣ ወሰኑን አልፎ አብዛኛውን የሀገሪቱን ክፍል የእኔ ነው ባለ ነበር ፤ ወሰኑንም አሳልፎ ባልሰጠ ነበር….ስንቱን ላንሳላችሁ፡፡
☞ አማራ በኢትዮጵዊነቱና በኢትዮጵያዊያን ላይ ያለው አቋም ከነገስታቱ እስከ መኳንንቱ ጊዜ ድረስ አንድና ያው ነበር ፡፡ ታዲያ አሁን አማራን ማን ዘረኛ አደረገው ? የአማራን ብሔርተኝነት የፈጠረውና የወለደው ለ27 ዓመት የተሰበከው ዘረኝነትና ለ27 አመት በአማራ ህዝብ ላይ የተጫነው ጭቆና ነው፡፡
ይህ የዘረኝነት ስብከት አማራን ያለስሙ ስም ያለግብሩ ግብር ያለ ስራው ስራ ሲያሰጠው ኑሯል ፡፡
እውነታው ግን ይህ አልነበረም፡፡ አማራ ለሀገሩ የኑሮ ሁኔታውን አያስብም፡፡ አማራ በሀገሩ አይደራደርም ፡፡ ዳሩ ግን አማራ ጨቋኝ ፣ አሳዳጅና አፈናቃይ ተደርጎ ተዘመረ፡፡ የአማራ ህዝብ እንደቀበሮ እየታደነ ከየአቅጣጫው ተፈናቀለ ፡፡ አቅፎ ባኖራት ኢትዮጵያ እንዲሰደድ እንዲፈናቀልና እንዲገደል ተደረገ ፡፡
☞ የአማራ ውለታ ግን ይህ አልነበረም፡፡ እውነቱ ግን አማራ የመሸበትን ሀገር ጎህ ብርሃን የሚቀድ ፣ የተራበን ጾም አድሮ የሚያበላ፣ እብሪተኛን የሚያስታግስ ዘመን ሳይሰለጥን ቀድሞ የሰለጠነ ነገር ግን ከስልጣኔ ያልተጠቀመ ምስኪን ህዝብ ነው፡፡
☞ የአማራ ብሄርተኝነት እውነት የኢትዮጵዊነት አደጋ ወይስ ጸጋ ? የአማራ ብሄርተኝነት መስፋፋት ሁለት መልኮች አሉት ፡፡
↝ አንደኛው መልክ አማራ በኢትዮጵያዊነቱ ብዙ መስዋዕትነትን የከፈለ ታላቅ ህዝብ በመሆኑና በፍትህና በእኩልነት የሚያምን ለሃቁና ለማተቡ ሟች ህዝብ በመሆኑ ምክንያት ለኢትዮጵያዊነት አደጋ ሊሆን የማይችልበት ሲሆን ፡፡
↝ ሌላኛው መልኩ ደግሞ አማራነት እንደ ወንጀል አማራነት ሃፍረት ተደርጎ በተሰበከበት ባሳለፍነው ሃያ ሰባት አመት በተፈጠሩ አንድ አንድ ያልተገቡ ስራዎች ለምሳሌ የወልቃይት ጸገዴ ፣ ኮረም ፣ ራያ እንዲሆም ሌሎች መተከልን ጨምሮ የተሰሩ የሀሰትና የፈጠራ ታሪኮች ካልተስተካከሉ የአማራ ብሄርተኝነት ከኢትዮጵዊነት ጋር ላይስማማ ይችላል፡፡
ያም ሆኖ ግን አማራ በእነ በላይ ዘለቀ እውነተኛ ኢትዮጵዊነት ፣ በእነ አጼ ምኒሊክ ርዕይ ፣ በእነ አፄ ቴዎድሮስ የአንድነት ጥሪ ሀገሩን እስከሞት እንዲወድ ተደርጎ ያደገ እና አሁንም ያ የህዝብና የሀገር ፍቅሩ ያልቀቀው ህዝብ በመሆኑ ምክንያት ከአደጋው የበለጠ ፍትሃዊነቱ ስለሚያመዝን የአማራ ብሔርተኛ መሆን ለኢትዮጵያ ጸጋ እንጅ አደጋ አይሆንም፡፡ (ከወጣቶች ጋር በነበራቸው መድረክ ከተናገሩት)
Filed in: Amharic