>

የአማራ ሕዝብና አ.ብ.ዴ.ፓ ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ. . . !!! (አቻምየለህ ታምሩ)

የአማራ ሕዝብና አ.ብ.ዴ.ፓ ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ. . . !!!
አቻምየለህ ታምሩ
ድርጅት ማለት ሁለትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሰዎች ወይንም ስብስቦች የሕዝብ ችግር ለመፍታት በፍላጎታቸው ወይንም በዓላማቸው ወይንም በእምነታቸው ዙሪያ የሚሰባሰቡበት የሰዎች ማኅበር ወይንም የወል ማዕከል ነው። ድርጅት ኅልውና የሚኖረው የሕዝብ ችግር ለመፍታት ከሕዝብ ችግር ሲፈጠር ብቻ ነው። ብአዴን  እንደ  ድርጅት ላለፉት  ሀያ ሰባት ዓመታት  ሕይዎት ሳይኖረው በአማራ ሕዝብ ላይ ተጭኖ የኖረው  ከአማራ ችግር ጋር  ሳይገናኝና   ኅልው ሳይኖረው  የእንጀራ ፈላጊዎችና የባእድ ቅጥረኞች ስብስብ ሆኖ ነው። ባጭሩ ብአዴን የተፈጠረው አማራ አጎንብሶ የምትቆም የሕወሓት አገር ለመፍጠር ነበር።
ባለፈው ሰሞን ግን ታድሻለሁ ብሎን መለስ ዜናዊ ያወጣለትን  ብአዴን የሚለውን የትግርኛ ስሙን በመቀየር «የጎባጣ አሽከር ጎንበስ ብሎ ይሄዳል፤ ምነው ቢሉት ጌታዬን ለመምሰል» አለ እንደሚባለው ምክትል ያደረገውን ኦሕዴድን ለመምሰል ሲል አዴፓ የሚል  ከአማራ ሕዝብ ችግር ጋር የማይገናኝ ስም ቀይሮ ነበር። ያም ሆኖ  የአዴፓ መሠረት የሆነው ብአዴን  የተፈጠረው የአማራን ችግር ለመፍታት ስላልሆነ  አዴፓንም  መሠረት ብአዴን  እየሳበው  ከአማራ ሕዝብ የበለጠ እየራቀ በመሄድ ላይ  ይገኛል።
ከሰሞኑ የአማራ ሕዝብ  በነቂስ ወጥቶ በየአደባባዩ በትዕይንተ ሕዝብ እየጠየቃቸው ከሚገኙ ዋና ዋና ጥያቄዎች መካከል  ሕገ መንግሥት ተብዮው  ወያኔ  ለአማራ ያበጀው  የቁም መቃብር ተወግዶ  የሁሉንም ኢትዮጵያውያን ይሁንታ  ያገኘ  የኢትዮጵያ ሕዝብ ሕገ መንግሥት ባስቸኳይ ይዘጋጅ የሚለው ቀዳሚው ነው። የአማራ ሕዝብ አንድም ቦታ  ሕገ መንግሥት ተብዮው ይከበር ብሎ ያቀረበው ጥያቄ የለም።
የሕዝብ ጥያቄ ለመስማት ታድሻለሁ የሚለው ብአዴን ግን የአማራ ሕዝብ ሕገ መንግሥቱ ይከበር ብሎ ጠይቋም በማለት በቃል አቀባዩ በንጉሡ ጥላሁን አማካኝነት እየነገረን ይገኛል! የትና መቼ ነው የአማራ ሕዝብ ያልተወከለበት ሕገ መንግሥት ይከበርልኝ ብሎ የጠየቀው? ብአዴን መቼ ይሆን  የአማራ ፍዳና መከራ፣ ሕመም፣ ስቃይ፣ እስርና እንግልት ተሰምቶት የአማራን ችግር ችግሩ የሚያደርገው? ብአዴን የሕወሓት ፍጡር ስለሆነ የፈጣሪው ሕገ መንግሥት ተብዬ  ይመለከተው ይሆናል! የአማራ ሕዝብ ግን ሕገ መንግሥት ተብዮውን የት አውቆት ነው ይከበርልኝ ብሎ ትዕይንተ ሕዝብ የሚያደርገው?  መቼ ይሆን ድሀው የአማራ በሚከፍለው ግብር የሚተዳደሩት  ብአዴኖች  አማራን  ጥያቄ  የራሳቸው ጥያቄ አድርገው ሕዝቡ ያቀረበውን ጩኸት በማስተጋባት  አማራ  ቀና ብሎ  ሲሄድ  የምትቆም  የጋራ አገር ለመፍጠር   ትግል  የሚጀምሩት?
ሌላው ቢቀር ሕገ መንግሥት ተብዮው ለመጽደቁ በፊት የተወሰዱትን የጎጃም፣ የጎንደርና የወሎ መሬቶች እንዲመለሱ እንታገላለን የሚለውን የአዴፓን መግለጫ የት አድርጎት ነው ንጉሡ ጥላሁን ሕገ መንግሥት ተብዮው ሳይጸድቅ በወረራ የተወሰዱትን ወልቃይትን፣ ራያንና መተከልን በሕገ መንግሥቱ መሠረት እንዲመለሱ ሕዝብ ጠይወቋል በማለት  የሚቀጥፈው?
Filed in: Amharic