አሰፋ ሀይሉ
━ Ancient Ethiopians’ “Axumite-Lalibelian” Architectural Mysteries Uncovered!
ከጥቂት ዓመታት በፊት በላሊበላ የደብረ አባ ሊባኖስ፣ ቤተ አማኑኤል፣ ቤተ መድኃኒዓለም፣ ቤተ ጊዮርጊስ እና ሌሎችም የዛሬ 1,000 ዓመት ገደማ በጥንታውያን ጥበበኛ አባቶቻችን ከአንድ ወጥ ድንጋይ የተፈለፈሉ ጥንታዊ ቤተመቅደሶች ላይ አንድ አስገራሚ ነገር ተመለከትኩ፡፡
ያም በላሊበላ ላይ ያየሁት ቅርፅ ከላሊበላ በፊት የዛሬ 1,600 ዓመታት ገደማ ላይ ከላሊበላ ውቅር ቤተመቅደሶች ቢያንስ ከ600 ዓመታት በፊት የተሠራውን የአክሱምን ኃውልት ቅርፅ ነው፡፡ የአክሱም ኃውልት ቅርጾች በላሊበላ በሮችና መስኮቶች ላይ ተሠርተዋል፡፡
በቤተ ደብረ ሊባኖስማ የመሸጋገሪያ ድልድዩ ግራና ቀኝ እንደመጠበቂያ ሆነው የተሠሩት የአክሱም ኃውልት ቅፅሮች ናቻ፡፡ እነዚያ የላሊበላና የአክሱም ዝምድናዎች ሁልጊዜ ያስገርሙኛል፡፡ በቅርብ በላሊበላና አክሱም መሠረታዊ ቅርፆች ላይ ባደረግኳቸው ቀጣይ ምርምሮች ደግሞ – ይበልጥ ይግረምህ፣ እርፍ በለው፣ ያውልህ እውነቱ ያለኝን ግኝት ደግሞ አገኘሁኝ፡፡
ያገኘሁት ነገር ምንድነው? በአክሱም ኃውልት ላይ «አራት ነጥብ» የሚመስሉ የተቀረፁ ምልክቶች አሉ፡፡ /በምስሉ ላይ ከታች በኩል መመልከት ይቻላል፡፡/ ይግረምህ ሲለኝ – እነዚህኑ በአክሱም ኃውልቶች ላይ ወደሠማይ የተቀሰቱትን አራት ነጥቦች – ድጋሚ ደግሞ – በላሊበላ አዕማዶች ላይም አገኘኋቸው፡፡ እንዴ! እነዚህ አራት ነጥቦች እዚህ ላሊበላ ላይ ምንድነው የሚያደርጉት? የላሊበላን ድንጋያት የፈለፈሉት ሰዎችስ – እንዴት እና ለምን ከእነርሱ 600 ዓመት በፉት ከተሠራው ከአክሱም ፍልፍል ኃውልቶች ላይ – አራት ነጥቦቹን መዋስ አስፈለጋቸው? – እነዚህ ጥያቄዎች በድግምግሞሽ በአዕምሮዬ ተመላለሱብኝ፡፡
ከዚያ ግን ምላሹን አገኘሁት፡፡ ለካንስ እነዚያ በአክሱም ላይ የምናገኛቸው አራት ነጥቦች የላሊበላ ቤተመቅደሶች አርኪቴክቸራል ዲዛይኖች ናቸው፡፡ እነዚያ የአክሱም አራት ነጥቦች – በቀላል ቋንቋ – የላሊበላ የግንባታ ዲዛይኖች ናቸው፡፡ የላሊበላ ቀያሾች፣ የንድፍ ባለሙያዎችና መሃንዲሶች ያደረጉት ነገር ምንድነው? – እነርሱ ያደረጉት – እነዚያን በአክሱም ኃውልት ላይ – በምስጢራዊ መልክ የተቀመጡላቸውን የአራት ነጥብ ንድፎች – በትክክል መርምረው ደረሱበት – እና የራሳቸውን ጥበብም አክለው – ወደ ላሊበላ መሬት አወረዱት!!
በምስሉ ላይ በቀኝ በኩል እንዳስቀመጥኩት – የላሊበላ መሃንዲሶች ያደረጉት ነገር – በአራቱ ነጥቦች አቅጣጫ በየአራቱም ማዕዘናት – ቁልቁል ተራሮቹን መፈልፈልን ነበረ የተያያዙት፡፡ እና አራቱም ማዕዘናት – በየአራት ነጥቦቹ ልክ ቁልቁል ሲቆፈሩ – መሐላቸው የምን ቅርፅ ይፈጠራል? – የመስቀል ቅርፅ፡፡ እናም በዚህ መንገድ – የላሊበላ ንድፈ-ጠበብት – የመስቀልን ቅርፅ የያዙትን የላሊበላ ውቅር አብያተ መቅደሶች – መሠረታዊ ንድፍ ያገኙት – ከአክሱም አራት ነጥቦች ላይ ነው፡፡
የሚገርመኝ – የእነዚያ የላሊበላ ጥንታውያን መሃንዲሶች ቀና እና ሃቀኛ አዕምሮ ነው፡፡ ከአክሱም ጋር ተወራራሽነት ያለውን ምሥጢራዊ ንድፈ-ጥበብ ማነፃቸውን መጪው ትውልድ እንዲያውቅላቸው ደግሞ – በቅዱስ4 ላሊበላ የተለያዩ ቤተመቅደሶች መስኮቶች፣ በሮች፣ የደወል ቤቶች፣ አዕማዶችና ቅስቶች ላይ – የአክሱምን ኃውልት ቅርፅ አኖሩበት!!!!!
ከምንም በላይ ግን – ከዚህ መጠነኛ ምርምሬ ካገኘሁት ነገር እጅጉን ያስደመመኝ ነጥብ ምንድነው? – ምናልባትም – ምናልባት – በበርካታ ፀሐፊዎችና ተመራማሪዎች ቀደም ሲል – ቢያንስ ለ4 ተከታታይ ክፍለዘመናት ሲተረክልን የኖረውን (እና ሰፊ ተቀባይነትንም እስከማግኘት የደረሰውን) – የአክሱም ኃውልት አዕማዶች የታነፁት በጣዖቶች አምሣል ነው – የአክሱምም ኃውልት ራሶች – ሌላ ነገር ሣይሆኑ – ለልምላሜ አምላክ – God of Fertility – መታሰቢያነት የታነፁ የወንድ ብልት ቅርፆች (Phallus) ናቸው – እየተባለ ሲነገረን የኖረውን ትርክት – በበኩሌ – በትልቅ ጥያቄ ምልክት ውስጥ እንዳስገባው አስገድዶኛል፡፡
ምናልባትም – ይሄን የአረመኔ ጣዖታት ትርክት ከአክሱም አዕማዶች ጋር አገናኝተው በሠፊው የተረኩት ብዙ ፀሐፊያን – እነዚያ የአክሱም ኃውልቶች በገላቸው ላይ – በምሥጢራዊ መንገድ ያኖሩትን ረቂቅ የCruciforms ንድፍ – እንደ ቀደምቶቹ የላሊበላ ንድፈ-ጠቢባን በትክክል ተረድተው መተርጎም የተሣናቸው ፀሐፊያን ሊሆኑ ይችላሉ ባይ ነኝ!!!
ግን ግን – ግን ግን – ግን ለመሆኑ – አሁን – እነዚያ የአክሱም አዕማዶች ላይ፣ እና በላሊበላ ቤተመቅደሶች ላይ በሚያስገርም ቅለት (ሲምፕሊሲቲ) እና በሚያስገርም ረቂቅነት የተቀመጡትን እነዚህን የህንፃ ንድፍ አስገራሚ ዲዛይኖች – ይህ የእኔ ትውልድ ሁሉ አስተውሎ ቢያይ – እንዲህ እንደ አሁኑ – በትውልዶች ትሥሥሮሽና ቁርኝት ከጥንታውያን አባቶቻችን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን – የሰሜን ኢትዮጵያውያን ሕዝቦችን ታሪካዊ፣ ሣይንሣዊ፣ መንፈሣዊና ኪናዊ ዝምድና – እንዲህ አሁን በሐዘን እያየን እንዳለነው – ለመበጠስና በጥልና ጠላትነት ሊቀይረው ይነሣሣ ነበር ወይ? የሚል ሕሊናዊ ጥያቄ – ይሞግተኛል፡፡ መልሱን ለታላቁ ኢትዮጵያዊ ወገኔ – በአክብሮት እተወዋለሁ፡፡
አምላክ የጠቢባን መናገሻዋን እምዬ ኢትዮጵያን ለዘለዓለሙ ይባርክልን፡፡ የጥበብ ማህፀን – ሐረገ ወይን – የብርሃን ማደሪያ – የነገሥታት ማደሪያ – ግዮናዊት የጥበብ መፍለቂያ የሆነችውን – እናታቸንን ቅድስቲት ኢትዮጵያን – አምላካችን – ከዘለዓለም እስከዘለዓለም በጥበብ፣ በቸርነት፣ በሠላም፣ በፍቅር፣ በኅብረት፣ በብልፅግና ያኑርልን፡፡ የተደበቀብንን ቀደምት አባቶቻችንን ጥበብ ለትውልዳችን ይግለጥልን፡፡
በቸርነቱ ያቆየንና የሚያቆየን የነገሥታት ንጉሥ፣ የጌቶች ጌታ፣ የአማልክት ሁሉ አምላክ እግዚአብሔር ስሙ ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም በምድራችን ሁሉ የተመሠገነ ይሁን!!! አሜን፡፡
━ ለፎቶግራፎቹ ባለቤቶች ሁሉ የከበረ ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ /የምስሎቹ ቅንብር – የራሴ/፡፡