>

ኮ/ል ጎሹ ወልዴ ከ32 አመታት ስደት በኋላ ወደ ሚወዷት ሃገራቸው ተመልሰዋል!

ኮ/ል ጎሹ ወልዴ ከ32 አመታት ስደት በኋላ ወደ ሚወዷት ሃገራቸው ተመልሰዋል!
ሙሉነህ ዮሀንስ
The Finest Ethiopian Diplomat Returns From 32 Years of Exile!
እኚህ  አንደበተ ርቱእ ሃገር ወዳድ ምሁር የ76 አመት አዛውንት ናቸው። ግማሽ ያክሉን በትክክል ሲሰላ 32 አመታት አሜሪካን ሃገር በስደት(በትግል ጭምር) ገፍተዋል። ዛሬ ሃገር ቤት መመለሳቸውን ስሰማ የተወሰኑ ነጥቦች ለማንሳት ፈለኩ። የተለያዩ ሰዎች በፖለቲካ አቋማቸው ምክንያት ሊተቿቸው ወይም ሊደግፏቸው ይችላሉ። ሆኖም የሚከተሉት ነጥቦች ትኩረት ይስባሉ።
ኮ/ል ጎሹ ወልዴ በኢሊባቦር ክፍለ ሃገር በጎሬ ከተማ ነው የተወለዱት። በ1950ዎቹ አጋማሽ በውትድርና መስክ ገብተው በትምህርትና ስልጠና ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የሜዳልያ ተሸላሚ ናቸው። አእምሯቸው ብሩ በመሆኑ ምናልባት ካልተሳሳትኩ ማትሪክን ሳይደፍኑ አይቀሩም። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ትምህርት ክፍል በከፍተኛ ነጥብና ብቃት ተመርቀዋል። አሜሪካን ሃገር ታዋቂው የል ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የህግ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል።
በስራ መስክም የኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስትር ሆነው ለአምስት አመታት አገልግለዋል። በወቅቱ ደርግ ስኬት ያገኘበትን የመሰረተ ትምህርት ዘመቻን አመራር ሰጥተዋል። ኮሎኔል ጎሹ ወልዴ ይበልጥ የሚታወቁት ግን በከፍተኛ ሃላፊነትና በሚኒስትርነት ደረጃ ለዘጠኝ አመታ ባገለገሉበት የውጭ ሚኒስቴር ተያይዞ ነው።
ሃገር ውስጥ ባለው ፖለቲካና የውጭ ሃይሎች ተፅእኖ ምክንያት ስራቸውን በፈለጉት መልኩ መቀጠል ሳይችሉ ሲቀሩ በገዛ ፈቃዳቸው በ1978 ዓ.ም. ገደማ የስራ መልቀቂያ ለፕሬዚዳንት መንግስቱ በመላክ ወደ አሜሪካን ሃገር ስደት ገቡ። በዚህ ዘመን ከምናዝንበት የመንግስት ባለስልጣናት ከፍተኛ ሙስና መዘፈቅ በተቃራኒው የቀድሞው የደርጉ ሹም ኮ/ል ጎሹ ወልዴ ግን አስገራሚ ውሳኔ ወሰኑ። ለስራ የተሰጣቸውን ሶስት ሽህ ሃምሳ ሰባት የአሜሪካን ዶላር የውሎ አበል እና መመለሻ የአውሮፕላን ቲኬት ለኢትዮጵያ መንግስት ተመላሽ አድርገዋል። በተጨማሪም ለምን ስልጣናቸውን እንደለቀቁ በዝርዝር ፅፈዋል።
ኮ/ል ጎሹ ወልዴ በስፋት ከሚታወቁበት ጉዳይ አንዱ ወያኔ፣ ሻቢያ እና ኦነግ የኢትዮጵያን ሕዝብ ባገለለ መልኩ ለንደን ላይ ያደረጉትን የተናጠል ድርድር እና ለሃገር ጠንቅ የሆነ አካሄድ በመቃወም በአሜሪካን ሴኔት ውስጥ በመገኘት ያሰሙት እጅግ አስደማሚ ንግግር ነበር። ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው እውቅ ዲፕሎማቶች ተርታ የሚመደቡት ኮ/ል ጎሹ በሃገራቸው ጉዳይ ብዙ ለፍተዋል። በስደት ዘመን መድህን የተባለ ፓርቲ መስርተው ነበር። ሌላም የትጥቅ ድርጅት ለማቋቋም ሞክረዋል። በዚህ መስክ ስራቸውን ለህዝብ በግልፅ አላቀረቡም ትግሉንም መርተው ዳርም አላደረሱም በሚል ትችት የሚሰነዝሩባቸው ሰዎች አጋጥመውኛል። ቢሆንም ለኢትዮጵያ ያላቸውን ፍቅር እና ያበረከቱትን አስተዋፆ ልንዘነጋው አንችልም።
ይልቅ ለትውልድ ትምህርት እንዲሆን የህይወት ተሞክሯቸውን ሲሆን እራሳቸው ካልሆነም ሌሎች ሊፅፉት ይገባል። አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ስላሉም ሚዲያ ተቋማት ከእኒህ አንጋፋ ምሁር ጋር ጥልቀት ያለው ውይይት ቢያደርጉ መልካም ነው። ሞያተኛ አግላዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ቁምነገር ያላቸው ሃላፊዎች ቢገኙ ኮ/ል ጎሹን እድሜ ሳይገድባቸው ልምዳቸውን መቅሰሚያ ሁኔታ ማመቻቸት ይገባ ነበር። (የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባልደረባ)
https://www.youtube.com/watch?v=orod3OU3jfM
Filed in: Amharic