>
5:14 pm - Tuesday April 20, 6810

ሰው እና እርግብ (አሰፋ ሀይሉ)

ሰው እና እርግብ
አሰፋ ሀይሉ
እርግቦች በተፈጥbቸው እጅግ ኢምንት Brain Size የተሰጣቸው ፍጡራን ናቸው፡፡ እርግቦች በጭንቅላት እርከን ከእንስሳት መካከል ከውራዎቹ መሐል ናቸው፡፡ ብልጥ ከሚባሉት እንስሣት ከድመት፣ ከውሻ፣ ከአይጥ፣ ከቺምፓንዚ፣ ከዶልፊን፣ ከአሣነባሪ፣ ከካንጋሩ፣ እና ከመሣሠሉት ጋር ሲነፃፀሩ ራሱ – እርግቦች – በቃ የዋህ መባላቸው እውነት ነው፡፡ እዝጌሩ ለእርግቦች የዋህነትን እንጂ ጭንቅላትን አልፈጠረባቸውማ፡፡ 1.2 ኪሎ ግራም ከሚመዝነው የሰው ልጅ ምጡቅ አዕምሮ ጋር የእርግቦችን ሚጢጢ አዕምሮ ካነፃፀርን – በቃ እኛ ሰዎች – ለእርግቦች – እግዜራቸው ነን – ለማለት ይዳዳል፡፡
እርግቦች ጭንቅላት የላቸውም፡፡ ወይም ቴስታታቸው ኔፓ ነው፡፡ ግን ግን አንድ ነገር ልብ በል፡፡ በልጅነቱ እርገቦችን ያረባ፣ አሊያም የእርግቦችን ‹‹ኩኩ መለኮቴ›› ከጣራው ላይ እየሠማ ያደገ ማንም ሰው – የሚያውቀው አንድ ታላቅ የእርግቦች የተፈጥሮ ፀጋ አለ፡፡ የማፍቀር ፀጋ፡፡ እርግብ ሁሉ ያፈቅራል፡፡ አፍቃሪዎች ናቸው፡፡ ያለመሰልቸት ቀኑን ሙሉ አንዳቸው የሌላኛቸውን ላባ ሲያክኩ ይውላሉ፡፡ ወንዱ የሴቷን እንቁላል ይታቀፍላታል፡፡ አንዱ ገላውን ሲታጠብ ውሃ በሌላኛዋ ላይ ይረጫል – ለጨዋታ፡፡ አንዱ ምግብ ሲያገኝ በመንቁሩ እየነካካ ሌላውን ይጣራል፡፡ ወንድና ሴት እርግቦች ተሳስመው ውለው ቢያድሩ አይጠግቡም፡፡ በቃ እርግቦች የማፍቀር ፀጋ የተሰጣቸው – ዝም ብለው ለማፍቀር እና ለመፈቃቀር – ፍቅርን ለመስጠትና ለመቀበል ዝግጁ ሆነው የተፈጠሩ – የምድሪቱ ፍቅር እስከ መቃብር ፍጡራን ናቸው፡፡
ይሄ ሁሉ የሚያሣየን ምንድነው⁈ ይህ የሚያሳየን – ለማፍቀር ሥልጡን ሆኖ መገኘት አስፈላጊ አይደለም፡፡ ለማፍቀር ጭንቅላትህን በትምህርት መግራትም አስፈላጊ አይደለም፡፡ ለማፍቀር ዲግሪ መደርደር አያስፈልግህም፡፡ ለማፍቀር ቀንድ እስክታበቅል መጠበቅ የለብህም፡፡ ለማፍቀር ምራቅህን እስክትውጥ የግድ ጠብቅ የሚልህ የለም፡፡ በቃ የትኛውም ጭንቅላቱ ያልበሰለ ጮርቃ ኅፃን ልጅ ማፍቀር ይቻለዋል፡፡ ማሰብ እምብዛም የማይሆንላቸው እርግቦች በፍቅር አትምጣባቸው፡፡ ዝሆኑም ያፈቅራል፣ ተኩላውም፣ አንበሣውም፣ ወፉም፣ አራዊቱም፣ ሁሉም የማፍቀር ፀጋን በተፈጥሮው ታድሏል፡፡ ምክንያቱም ማፍቀር በሥልጣኔ የሚገኝ ፀጋ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ማፍቀር፣ መፈቃቀር በምርምር የሚገኝ ሥጦታ አይደለምና፡፡
ብዙው ሰው ግን ሲታይ – ገና ለገና የማሰብ ችሎታ አለኝ ብሎ – ራሱን እንደተራቀቀ ፍጡር እየተመለከተ ሲመጻደቅ ታየዋለህ፡፡ ብዙ የሰው ልጅ ጭንቅላት የፈጠራቸውን ነገሮችም ስታይ በሰው ልትደመም ይቃጣህ ይሆናል፡፡ ነገር ግን የሰውን ልጅ ከሠማያት ዳመኖች በላይ ያንሣፈፈ የሰው ልጅ ድንቅ ጭንቅላት – ባዶ ጭንቅላት ሊሆኑ የተቃረቡትን የዋሃን እርግቦች ጭንቅላት ያህል – ለማፍቀር ያልሆነለት – እርስበርሱ ሲነካከስ የሚኖር – አሣዛኝ ተሸናፊ ፍጡር አድርጎታል፡፡ ባጭሩ አምላክ በተፈጥሮ ለፍጡራኑ ያደለውን ማፍቀር እኛ ሰዎች በጭንቅላታችን አጥተነዋል፡፡
ማፍቀር በሁሉም ፍጥረት ዘንድ ያለ የተፈጥሮ ነፃ ሥጦታ ነው፡፡ ማፍቀር ምንም ቅድመ-ሁኔታ የለውም፡፡ ለማፍቀር ጭንቅላት ቢጠየቅ ኖሮ እርግቦች ሲፋቀሩ አናይም ነበር፡፡ እንደ እርግብ የዋህ እንሁን፡፡ ይሄን የነፃ ሥጦታ አንፍራው፡፡ የተፈጥሮ የማፍቀር ነፃ ፀጋችንን እንጠቀምበት፡፡ ጭንቅላታችን ፍቅርን የሚከለክለን ከሆነ – አውልቀን እንጣለው፡፡ ልባችንን ለፍቅር ሳንከፍት – ኦና ልባችንን ተሸመክመን ብንዞር – ምኑ ላይ ነው የኛ ሥልጡንነት⁇
እናማ … በቃ…. ልባችንን ለፍቅር እንክፈት፡፡ የሚያነታርከንን አጉል እውቀታችንን ከላያችን ገፍፈን እናሽቀንጥር – እና እጅ ለእጅ ተያይዘን – በፍቅር – አብረን እንዋኝ!! በፍቅር አብረን እንቅዘፍ!!!! ከእርግብ ከፍ ብለን በፍቅር እንብረር፡፡ በፍቅር አብረን እንክነፍ!! ለእርግብ የተቻለ – ለሰው ይቻላልና – ፍቅር አያቅተን፡፡ ፍቅርን እንድፈረው፡፡ ፍቅርን አንፍራው፡፡ መልካም ድፍረት!! ለፍቅር!!! ቻው፡፡
ፍቅር ፈራን “ፈራን” 
– ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን
‘ፍቅርን ፈራን መቀራረብ ፈራን
እንዳልተዛመድን እንዳልተዋለድን
ፈርተን መዋደድን ጉርብትናን ናድን
እኛነትን ትተን እኔነትን ለመድን
“ፈራን”
ፍቅርን ፈራን ጥላቻን ሰራን ብቸኝነት ጠራን
በጋራ ቤታችን አጥር ድንበር ሰራን
“ናቅን”
በልዩነት ደምቀን ያልኖርን ያህል አንድም ቀን
እልህ ተናነቅን
“ናቅን”
መቻቻልን ናቅን ለፀብ አሟሟቅን
ለአመፅ ስንነሳ ለሰላም ወደቅን
አገር ስትቃጠል ከዳር ሆነን ሞቅን
”ጠላን”
መወያየት ጠላን መነጋገር ጠላን
መደማመጥ ጠፍቶ መነቋቆር በዝቶ
መናናቅ በርክቶ
መመካከርን ስንረሳ መከባበርን ስንረሳ
እጃችን በወንድማችን ላይ ዱላ አነሳ
የቃየል ምቀኝነት በልባችን ላይ ነግሳ
“ራቅን”
የተስፋ ሻማችን ተለኩሶ
ወጋገኑ መታየት ሲጀምር አድማሱን ጥሶ
እኛ ግን ራቅን ብሩህ ነገን ራቅን
ዛሬን ተጣበቅን ትላንትን ናፈቅን
ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን
Filed in: Amharic