>
6:50 am - Wednesday December 7, 2022

ፖለቲከኞች ወደ ውስጥ... ጳጳሳት ወደ ውጭ (ዳንኤል ክብረት) 

ፖለቲከኞች ወደ ውስጥ . . . ጳጳሳት ወደ ውጭ
ዳንኤል ክብረት 
ከውጭ የመጡት ብጹአን አባቶች ኢትዮጵያ ውስጥ የመመደብ ፍላጎት ፈጽሞ የላቸውም
~
ባለፉት ሦስት ወራት አያሌ ፖለቲከኞች ወደ ኢትዮጵያ በመግባት በሀገር ውስጥ ባለው ፖለቲካ ለመሳተፍ እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተዘዋወሩም ድጋፍ እየሰበሰቡ ነው፡፡ በተቃራኒው ደግሞ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ፖለቲከኞቹ የለቀቋቸውን አሜሪካ፣ አውሮፓና አውስትራልያ ለማጥለቅለቅ ወደ ውጭ እያቀኑ ነው፡፡
በተለይም ከውጭ የመጡት ብጹአን አባቶች ኢትዮጵያ ውስጥ የመመደብ ፍላጎት ፈጽሞ የላቸውም፡፡ በዚህ ረገድ ከ18 ጳጳሳት ሁለት ብቻ ናቸው የተገኙት፡፡ ሌሎቹ ግን በአሜሪካና በአውሮፓ ካልመደባችሁን እንገነጠላለን ብለው የሚያስፈራሩ ሆነዋል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ መለመንና ማግባባት ሲያቅተው ጳጳሳቱን የደብር አስተዳዳሪዎች አድርጎ እስከ መመደብ ደርሷል፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን 99% በጎቿ የሚገኙት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፡፡ 99 በመቶ አሥራት ሰብስባ አገልግሎቷን የምትፈጽመውም ከገጠሯ ቤተ ክርስቲያን፣ ከድኻዋ መቀነት ነው፡፡ አሶሳ፣ ጅጅጋ፣ ጋምቤላ፣ ከሚሰበስቡት ዐሥራት ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ያወጣሉ፡፡ በውጭ ያሉት አብያተ ክርስቲያናት ከ16 በላይ ጳጳሳት ቢመደቡባቸውም አንድ በመቶውን የቤተ ክህነቱን ወጭ እንኳን አይሸፍኑም፡፡ በአንዳንዶቹ አህጉረ ስብከትም ከሁለት በላይ አጥቢያዎች አይገኙም፡፡ ጳጳሳቱ ግን መመደብ የሚፈልጉት ከጋምቤላ ይልቅ በሎንደን፣ ከሻሸመኔ ይልቅ በአውስትራልያ፣ ከመተከል ይልቅ በጣልያን፣ ከወለጋ ይልቅ በሎስ አንጀለስ ነው፡፡
ከግብጽ ቤተ ክርስቲያን ከባድ ፈተና የገጠመውን ዴር ሡልጣን፣ ከዘመኑ ጋር መራመድ ያቃተውን ቤተ ክህነት የማዘመን የምእመናን ጥያቄ፣ ከተሐድሶ እንቅስቃሴና በተለያዩ አካላት ጥቃት የደረሰባቸው አብያተ ክርስቲያናትን በተመለከተ ከባባድ አጀንዳዎች የነበሩት ቅዱስ ሲኖዶስ፤ ዋናውን ጊዜ የጨረሰው ግን በጳጳሳት ድልድል ነው፡፡ ጎንደርና ጎጃም፣ ወሎና ትግራይ፣ አዲስ አበባና ምሥራቅ ሸዋ፣ አዋሳና ድሬዳዋ ለመመደብ እንኳን ጳጳሳቱ ፈቃደኞች ባለመሆናቸው አህጉረ ስብከቱ ሲሞሉ ጳጳሳቱን በአድባራት የበላይ ጠባቂነት መመደብ ተጀመረ፡፡ የጎንደር አረጋውያን ‹ገና ጳጳስ ግብዝባና ይሾማል› የሚሉት ንግርት እየደረሰ ይመስላል፡፡
መንጋውን በትኖ ምኞቱን የሚከተል እረኛ ቅዱስ ሲኖዶስ ባይጠይቀውም ፈጣሪው ግን መጠየቁ አይቀርም፡፡  የቅዱስ ሲኖዶስ አንድነት ዓላማው እናት ቤተ ክርስቲያንን ለማጠናከር እንጂ አሜሪካንን በጳጳሳት ለመሙላት አልነበረም፡፡ ገጠሯን ቤተ ክርስቲያን አፍርሶ የኪራይ ቤተ ክርስቲያንን ለማብዛት አልነበረም፡፡ ገዳማትና አድባራትን ንቆ የግዥ አብያተ ክርስቲያንን ለማብዛት አልነበረም፡፡ የአንድ ሀገረ ስብከት ያህል አጥቢያና ሕዝብ ለሌላት አሜሪካ ከ13 በላይ ጳጳስ መመደብ የውጭ ዕድልን ለማስፋት እንጂ ለአገልግሎት እንዳልሆነ እሙን ነው፡፡ በሀገር ቤት ከ18 በላይ አህጉረ ስብከት አባት አልባ ሆነው ካህናቱና ምእመናኑ እግዚኦ እያሉ አሜሪካ ካልመደባችሁኝ እገነጠላለሁ የሚሉ አባቶችን እነ ዮሐንስ አፈወርቅና እነ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ፣ እነ አቡነ ጎርጎርዮስና እነ አባ እንየው ውቤ በዐጸደ ነፍስ ሆነው ሲመለከቱ ምን ይሉ ይሆን?
በዚህ ረገድ በሀገር ቤት በሚገኙት አህጉረ ስብከት ተመድበው ከድኻው መንጋ ጋር አገልግሎታቸውን ለመስጠት ኃላፊነት የተረከቡት አባቶቻችን ታሪክ በወርቅ ቀለም ስማችሁን እንደሚጽፈው አትዘንጉት፡፡ ኢትዮጵያውያን የግብጽ ጳጳሳት በኢትዮጵያ መመደባቸው አምርረው የተቃወሙት በዘራቸው ምክንያት አልነበረም፡፡ በጣልያን ወረራ ጊዜ የነበሩት የግብጽ ጳጳስ ሕዝቡን በትነው ካይሮ ገብተው መቀመጣቸውን በተመለከተ ጊዜ ነው፡፡ እንደ አቡነ ጴጥሮስ የሕዝብን መከራ የሚጎነጭ አባት የፈለገው በመከራው ጊዜ ጥሎት የሚሸሽ አባት ስላልፈለገ ነው፡፡ ዛሬ ግን አንዳንድ ጳጳሳት በሀገሪቱ ውስጥ አለ የሚሉትን መከራ ለመቋቋምና ከሕዝቡ ጋር ሆነው ለመጋደል ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ለዚህ ነው በሀገር ቤት ባለችው የገጠር ቤተ ክርስቲያን ለማገልገል ኃላፊነት የወሰዱትን አባቶች የምናመሰግነው፡፡
ታሪክ ቤተ ክርስቲያኒቱን ወደ አዲስ ምእራፍ እየወሰዳት ነው፡፡ አዲሱ ምእራፍ አዲስ ችግር ያመጣል፡፡ አዲሱ ችግርም አዳዲስ ጀግኖችን ይወልዳል፡፡ እነርሱም የመንፈስን ኃይል ታጥቀው ቤተ ክርስቲያንን ከምንደኞች ይገላግሏታል፡፡ ቤተ ክርስቲያን መክና አታውቅምና፡፡
Filed in: Amharic