>

የችግሩ አካል አንተው ሆነህ ስለመፍትሄ ለመናገር የሞራል ብቃቱ ካለህ አስገራሚ ነው!!! (መሳይ መኮንን)

የችግሩ አካል አንተው ሆነህ ስለመፍትሄ ለመናገር የሞራል ብቃቱ ካለህ አስገራሚ ነው!!!
መሳይ መኮንን
 ህዝብ ከዳር እስከዳር ተስፋ ያደረገበትን የለውጥ ሂደት ለመቀልበስ ከሚሰሩ ሃይሎች አንዱና ዋናው ሆነህ ስታተራምስ ቆይተህ ”ሀገሪቱ አደጋ ውስጥ ናት” ብለህ የምታለቃቅስ ከሆነ ጥሩ ተዋናይ እንጂ ፖለቲከኛ አይደለህም። ለውጡ በተፈለገው ፍጥነት እንዳይሄድ እንቅፋቱ አንደኛው ነበርክ።
 ከለውጡ በፊትም አዲሱ አመራር ቤተመንግስት ሊገባ በተዘጋጀበት ሰሞን የጭቃ ጅራፍህን ስታስወነጭፍ የቆየህ፡ በይፋ የውግዘት መዓት ስታዥጎደጉድ የነበርክ፡ በኋላም በለውጡ ህዝቡ ውስጥ የገባውን ተስፋ ለማጨለም እንቅልፍ አጥተህ የምታደር ሆነህ፡ ቆየተህም በግልጽ በቴሌቪዥን መስኮት እየወጣህ ጥርጣሬን ስትረጭ፡ ስጋትን ስትበትን ኖረህ ድንገት እብስ ብለህ ደግሞ ”ሀገሪቱ ወደ ገደል እየሄደች ነው” የሚል ነጠላ ዜማ ስትለቅ በእርግጥ የሚያዳምጡህ አታጣም። ግን በእንዲህ ሁኔታ እስከመቼ? እድሜም ይሄዳል። ሽበት ይጀምራል።
በእርግጥ ለውጡ አዝጋሚ ለመሆኑ ክርክር አያሻውም። የሽግግር ጊዜው በቀውስ የተከበበ ለመሆኑ አይኑን የገለጠ ሁሉ የሚመለከተው ነው። እዚህም እዚያም አዳዲስ ጥያቄዎች እያቆጠቆጡ፡ የነበሩትም ከተዳፈኑበት እየተቀሰቀሱ ለግጭትና ለሰው ህይወት መጥፋት ሰበብ ምክንያት እየሆኑ እንዳለ እየታዘብን ነው። ግን ሂደት ነው። ሽግግር ነው። ደግሞስ ምን ምርጫ አለን? ጉድለቱን እየሞሉ ሂደቱ እንዲፈጥን በማድረግ ለሁላችንም የምትመች ሀገር እንድትሆን አወንታዊ አስተዋጽኦ ከማድረግ ባሻገር ምን የሚሻል አማራጭ ይኖር ይሆን?
ደቡብ አፍሪካ 5 ዓመታት ፈጅቶባታል። ቺሊ ከ8 ዓመት በላይ ወስዶባታል። ከጭቆና አገዛዝ ወደ ዲሞክራሲ የሚደረገው ሽግግር ከዚያም በላይ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ይታመናል። የተዘጋ ቤት ሲከፈት ጠረኑ በቀላሉ አይወጣም። ህወሀት ያጨማለቀውን ለማጥራት የሚወስደው ጊዜና የሚያስከፍለው መስዋዕትነት ገና አልተነካም። በ7 ወራት ተአምር መጠበቅ የዋህነት ነው። ደግሞ የችግሩ ዋናው አካል አንተው ሆነህ፡ ቀንና ማታ አጀንዳዎችን እየለወጥክ ስትረብሽ ከርመህ ”ለውጡ የታለ? አደጋ ውስጥ ገብተናል” ብለህ ስታሟርት ግን ጤንነትህን እጠራጠራለሁ።
Filed in: Amharic