>

አማራ እና ትግሬይ!!! (አበበ ቶላ ፈይሳ)

አማራ እና ትግሬይ!!!
አበበ ቶላ ፈይሳ
በአሁኑ ሰዓት በሃገራችን አሳሳቢ ተብሎ ከሚቆጠሩ ነገሮች ውስጥ ለኔ ግንባር ቀደሙ አሳሳቢ ጉዳይ በአማራ እና በትግራይ ብሄርተኞች መካከል ያለው ፍጥጫ እና መተነኳኮስ ነው። ይሄ ጉዳይ በቄስ በሼክ በሽማግሌ ተብሎ እንዲለዝብ ካልተደረገ በህግ ብቻ የሚዳኝ አይመስልም።
ከሁለቱም ወገን ያሉ ብሄርተኛ አክቲቪስቶች በሶሻል ሚዲያ ላይ የሚያድርጉት የቃላት ልውውጥ በተለያዩ ታሪካዊ ጠብ ባላቸው ሃገራት መካከል የሚደረግ የቃላት ጦርነት እንጂ በአንድ ሃገር በአንድ መንግስት የሚተዳደሩ ሰዎች አይመስሉም። አክቲቪስቶቹን ተዉ ብለን ብንመክር ሁሉም ጉልበቱን ለማሳየት የቋመጠ ይመስል ‘ተዉ’ ማለትን ራሱ እንደ ስድብ እያዩት በጂ የሚል አልተገኘም።
ህዝቡን ግን እንመክራለን፤ አብዛኛውን አክቲቪስት ውጪ ሃገር ነው ያለው። ነገ ነገሮች ተካረው ህዝቡ ጦርነት ውስጥ ቢገባ የመሳሪያ መግዣ ገንዘብ ይልክልህ ይሆናል እንጂ የገፈቱ ቀማሽ መሬት ላይ ያለው ህዝብ ነው። እርግጥ ነው አበሻን ተው ትሞታለህ… ብሎ ካሰበው ነገር ማቆም እንደማይቻል የታወቀ ነው። ላመነበት ነገር መሞት ለአበሻ ክብሩ ነው። ቢሆንም ቅሉ ሃገራችንን ወደኋላ ያስቀራት በየግዜው በውሃ ቀጠነ ስናድርጋቸው የነበሩ ጦርነቶች መሆናቸውን መርሳት የለብንም። ዛሬም በእልህ እና ጀብደኝነት ወደ እርስ በርስ ጦርነት የገባን እንደሆነ ሌላ ብዙ አመት ወደኋላ ከመንከባለል ውጪ የምናመጣው በጎ ውጤት የለም።
ከቀልባችን ሆነን ካሰብነው፤ አሁን ላለው የቃላት ጦርነት እንደ ሰበብ ሆነው የሚታዩት ራያ እና ወልቃይት የአማራ ክልል አካል ተደርገው ቢወሰኑም የትግራይ ክልል አካል ተደርገው ቢወሰኑም በአንድ ሃገር ላለ ሰው ምንም የሚያመጣው ለውጥ የለም። በቦታው ላይ ያሉት ነዋሪዎች በየትኛውም ክልል ሆነው መብታቸው፣ ሰብዓዊ እና ማህበራዊ ክብራቸው እና ፍላጎታቸው ተጠብቆ ይኑሩ እንጂ እዛም ሆኑ እዚህ ሁሉም ኢትዮጵያ ነው!
በሃገራችን በተለያየ ግዜ የተለያየ አይነት የአስተዳደር ወሰን ኖሮን ያውቃል። ይሄንን ወሰን ለአስተዳደር ካለው አመቺነት አንጻር ብቻ ማየቱ ነው የሚያዋጣን። በአንድ ሃገር ውስጥ ማንም ከማንም ተለይቶ ድንበር ሊያበጅ አይችልም። ምንም የሚያመጣው ጠቀሜታም የለም።
እና ህዝቤ ሆይ… በተለይም አማራ እና ትግራይ ወዳጆቼ ወደ ጠብ እና ጦርነት ከሚያመሩ ቃላት እና ድርጊቶች ራሳችሁን ጠብቁ። ጦርነት ሲገቡበት ቀላል ይመስላል ይሆናል እንጂ ከገቡበት በኋላ ኪሳራው ብዙ ነው!!!
የአማራ እና ትግራይ ክልል መንግስታትም ህዝቡ ላነሳቸው ጥያቄዎች አጥጋቢ ምላሽ በመስጠት እንዲሁም እርስ በርስ በመነጋገር ህዝቡን ከአላስፈላጊ የርስ በርስ ግጭት ትታደጉት ዘንድ እንለምናችኋለን!
Filed in: Amharic