>
4:31 pm - Tuesday July 5, 2022

ቤተክህነቱም ቤተመንግሥቱም የታመሙባት አገር (ከይኄይስ እውነቱ)

ቤተክህነቱም ቤተመንግሥቱም የታመሙባት አገር

 

ከይኄይስ እውነቱ

 

ያሳለፍነውን 27 ዓመታት ጨምሮ ይህ ያለንበት ጊዜ በምን መልክ ትገልጸዋለህ ብባል የዕብደትና የድንቁርና ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በቤተክህነቱም በቤተመንግሥቱም መደማመጥ የጠፋበት፤ መዘላለፍና መናናቅ የነገሠበት፤ ቅንነትና መንፈሳዊነት የጠፋበት፡፡ የሀገር ሉዐላዊነትና አንድነት፣ መንፈሳዊና ሥጋዊ ሀብትና ቅርስ፣ ባህላዊና ትውፊታዊ እሴቶች፣ ክብርና ኩራት ወዘተ ጭርሱኑ እንዲጠፋ 24/7 ሲዶለት÷ሲሴር÷ግብረ ዲያቢሎስ ሲፈጸምበት ተከርሟል፡፡

ቤተመንግሥቱ

ባንድ ወገን አእምሯቸው በዘረኝነትና በድንቁርና የናወዘባቸው ወያኔ ትግሬዎች (ሕውሓቶች) ከምንይልክ ቤተመንግሥት በአካል ቢለዩም፣ የ27 ዓመታቱ ግፍና በደልም አልበቃ ብሏቸው ከሕዝብ በዘረፉት ሀብትና የአገዛዛቸውን ህልውና ለማስጠበቅ ባዋቀሩት የፀጥታና ሠራዊት ኃይላት እንዲሁም ሌሎች የመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ ያሉ አሸባሪዎቻቸውን በመጠቀም መቐለ መሽገው ሽብር ላኪና አከፋፋይ የሆኑበት ፤ በሌላ ወገን ሕዝብ በከፈለው መሥዋዕትነት በተገኘ አንፃራዊ ነፃነት አማካይነት በአገር ጉዳይ እኩል ተካፋይ እንዲሆኑ ተጋብዘው ወደአገር ቤት ከገቡት የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ዓላማ ቢስ የሆነው ኦነግ እና ከጀርባ ሆነው ጥቂት የኦሮሞ ወጣቶችን በመንጋ ተከታይነት ይዘው ሥርዓተ አልበኝነት እንዲነግሥ፣ ራሳቸውን በማንአለብኝነት (‹በመንግሥትነት› በመሰየም) ቀን ከሌት ለሽብር የሚጣደፉት ኦነጋውያን (ጀዋራውያን) በትክክለኛ ስማቸው ተረፈ-ወያኔዎች አገር ካልገነጠልኩ ወይም ተረኛ መንግሥት ካልሆንኩ ኢትዮጵያን እበትናታለሁ÷አፈርሳታለሁ እያሉ ኹከት በመፍጠር የተሠማሩበት፤ ባንፃሩም የመንግሥትን ሥልጣን የያዘውና በዐቢይ የሚመራው አገዛዝ በመጀመሪያዎቹ 3 ወራት ይበል የሚያሰኝ መንገድ ጠራጊ ርምጃዎችን በመውሰድ ባገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያኖችን ልብ ለመግዛት ቢችልም፤ ጅምር የለውጥ ሂደቱ ግለቱን ጠብቆ መሄድ ቀርቶ የማይላወስበት አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱን እያስተዋልን ነው፡፡ ከጅምር ለወጡ ደጋፊዎች መካከል አንዱ ብሆንም (ድጋፌም የተመረኮዘው በግለሰብ ሰብእና ላይ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህልውናና አንድነት ቀጣይነት፣ በሕዝቧ ፈቃድ የተመሠረተ የሕግ የበላይነት ፣ ማኅበራዊ ፍትሕና እኩልነት የሰፈነበት መንግሥት ማቆም እና ሕዝቧ ከተዋርዶ ወጥቶ የነፃነት፣ የዕውቀትና ብልጽግና ባለቤት መሆኑን ማረጋገጥ ላይ በመሆኑ) ሃሳቤን የማቀርበው እንደ ፖለቲከኞች ንግግር በማስታመም/በማድበስበስ ሳይሆን እንደ አንድ ያገሩ ጉዳይ በእጅጉ እንደሚያሳስበው (እንቅልፍ እንደሚነሳው) ዜጋ እውነቱን ተናግሮ የመሸበት ማደር የሚለውን ብሂል መሠረት አድርጌ በትችትና በወቀሳ ጭምር ነው፡፡  የዐቢይ መንግሥት ሕግና ሥርዓት ማስከበር አልቻለም፡፡ ይህ ማለት በሰላማዊ የአዲስ አበባ ወጣቶች ላይ ተኩስ ከፍቶ በመግደል እንደሚዘባነነው ጋጠ ወጥ ኃይልና ኃላፊዎቹ ዓይነት ርምጃ እንዲወሰድ አይደለም ጥያቄው፡፡ ባዲስ አበባ ወጣቶች እንደተፈጸመው ከሕግ ውጭ እስር ይፈጸም እያልኩም አይደለም፡፡ ያለንበት ጊዜም ከመደበኛው ወጣ ያለ እንግዳ ጊዜ መሆኑንም ዘንግቼው አይደለም፡፡ እስከ ሙሉ አቅማቸው መቐለ የመሸጉትን ነውረኞችም እያደረሱ ያሉትንና ሊያደረሱ የሚያስቡትንም ጥፋት ባለመገንዘብም አይደለም፡፡ ከወያኔ ትግሬ ጋር ባንድነት የፈጠሩትን የዘረኝነት አገዛዝ በወር ተረኝነት ለማስቀጠል በጥላቻ ስብከትና በኃይል ጭምር ለአርባ ዓመታት ያላሳኩትን ጭንጋፍ ዓላማ በአቋራጭ ለማሳካት የሚቃዡ፣ ሰላምና ዴሞክራሲን ከጠብመንጃ አፈሙዝ ፈልቅቀው ማውጣት የሚሹ ኋላ ቀሮችንም እንዳላየሁ ሁኜም አይደለም፡፡

ትልቁ ሥጋቴ ቃላት ማሽሞንሞኑና በዚህም የባዕዳኑ የሰብአዊ መብት ንቅናቄ መሪዎችን ለመምሰል ሙከራ ማድረጉ የግል ሰብእናን/ገጽታን ከመገንባት ባለፈ ብዙ አይጠቅመንም፡፡ ይህ አንገብጋቢ ወቅት የፆታ ካርድ መዘን የምንጫወትበትም አይደለም፡፡ ይህ ካርድ በካቢኔው አባላት ሹመትና  በጠ/ፍ/ቤት ላይ እንዲሠራ ሲደረግ የአዲስ አበባ ከንቲባነት ላይ ሲመጣ ወገቤን ያለበትም ምክንያት ምን እንደሆነ ሰያሚው ብቻ የሚያውቀው ነው፡፡ በእኔ እምነት ምናልባት ከአምባሳደር ሣኅለ ወርቅ በስተቀር (ይመጥናቸው የነበረው ቦታ ቀፎው ፕሬዚዳንትነት ሳይሆን ትርጕም ያለው ለውጥ ሊያመጡበት የሚችለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ነበር) የዐቢይ ባለሥልጣነትን ሹመት በሙሉ በወያኔ የጎሣና ታማኝነት መመዘኛ መሥፈርት የተመለመሉ በመሆናቸው ዐቢይ ላይ ቅር ከተሰኘሁባቸውና ተዐቅቦ እንዲኖረኝ ካደረጉኝ ውሳኔዎች መካከል አንዱ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡

የጥፋት ኃይሎቹ የውንብድና ተግባር ከዐቢይ መንግሥት እየቀደሙና እያሽመደመዱት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ቅንጦት እየሆነ የአገር አለመረጋጋት አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ መጥቷል፡፡ እንደሚታወቀው የለውጡ ሂደት ቀጣይነት የተንጠለጠለው በጥቂት ግለሰቦች በጎ ፈቃድ ላይ ነው፡፡ በተለምዶ የለማ ቡድን የሚባለው እኮ ሁለት ሦስት ሰዎች ጠርተን ሌሎችን መድገም የምንችል አይመስለኝም፡፡ ለአፍታ እነዚህን ጥቂት የለውጥ አመራር ግለሰቦች ከሥዕሉ ዞር ብናደርጋቸው የምንፋጠጠው መራር እውነት ርኵስ የሆነውና በርኵሰት ተግባሩ አቻ የማይገኝለት ወያኔ/ኢሕአዴግ ነው፡፡ የዚህ ነውረኛ ድርጅት መዋቅርን በ‹ፌዴራል› ደረጃ ብቻ አናስበው፡፡ በአገሪቱ ግዛቶች በሙሉ የተተበተበ ነው፡፡ ይህ ስሙን ለመጥራት የምጸየፈው ድርጅት ለወጡን ለመምራትና ለማሸጋገር የሚያስችለው ብቃትና ፍላጎትም እንደሌለው ጽኑ እምነቴ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ግዴላችሁም በእኔ ጣሉት ለእኔ ተዉት ምንም ሥጋት አይገባችሁ የሚለው የዐቢይ ተስፋ ቃል ከዝርው ቃልነት አያልፍም፡፡

እንደ ኢትዮጵያ ለዘመናት ሲንከባለሉ በመጡ መጠነ ሰፊና ዘርፈ ብዙ ችግሮችና ተግዳሮቶች የተተበተበች አገር በሕዝብ ሙሉ ተሳትፎና ትብብር ካልሆነ በቀር የፈለገው ጠቢብና ዐዋቂ÷ቅንና አስተዋይ ቢሆን በግለሰብ መሪ ከገባችበት ማጥ ልትወጣ አትችልም፡፡ ለላቀና ጠንካራ ምክንያት ውዳቂ የሆነውና ሕውሓትን አዝሎ የሚገኘው ‹ግንባር› ጥፋቷ እንጂ መድኅኗ እንደማይሆን ለአፍታ አልጠራጠርም፡፡ ጎበዝ! ‹የተለወጠው ወያኔ/ኢሕአዴግ› የሚለው ስብከት ደንጊያ ላይ ውኃ ከማፍሰስ ልዩነት የለውም፡፡ አይለወጥምም፡፡ ኢትዮጵያን በጭራሽ ሊታደግ አይችልም፡፡ በሽታው ራሱ ፈውስ መድኃኒት ይሆናል ብለው ከሚሟገቱ ገልቱዎች ጋር ራሴን መደምር አልፈልግም፡፡

ምናልባት ዐቢይን እናግዘው ያንተ አስተዋጽዖ ምኑ ላይ ነው የሚል ጥያቄ ይነሳ ይሆናል፡፡ ለዚህ የምሰጠው መልስ ለጊዜውም ቢሆን በተፈጠረው አንፃራዊ ነፃነት የምናምንበትንና ላገር ይበጃል የምንለውን ሃሳብ ከማካፈል አልዘለለም፡፡ አስተዋጾአችን የበለጠ ትርጕም እንዲኖረው ከተፈለገ ዐቢይ ከድርጅቱ ሳጥን ወጥቶ በአገር ማረጋጋቱም ሆነ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እኛ ተራ ዜጎች የምንሳተፍበትን መንገድ ማመቻቸት አለበት፡፡ ዛሬም እኮ ያለው ድርጅታዊ አሠራር ነው፡፡ ለዐቢይም ሆነ ለኢሕአዴግ እነርሱ በመረጡት መንገድ ብቻ እንዲሄዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ በይፋ የሰጣቸው ሥልጣን (mandate) የለም፡፡ ጆሮን ጭው የሚያደርግ ዘግናኝ ወንጀለኞችን የፈጸሙ ‹አውሬዎች› እንደፈለጉ ሲፈነጩ ማየት፣ ባንድ ሉዐላዊት አገር ውስጥ ሌላ አገር-አከል ግዛት ፈጥረውና ተሸሽገው ከሕግ በላይ ሲሆኑ ማየት፣ እነዚሁ ሽብርተኞች አገርን እገዛለሁ በሚል ድርጅት ውስጥ በሥራ አስፈጻሚነት ፈላጭ ቆራጭ ሆነው ማየት፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ በዘረፉት አንጡራ ሀብት ሽብርን ሲያስፋፉ ማየት፣ ከውሸት ፓርላማው እስከ ካቢኔው፣ ከፀጥታው መ/ቤት እስከ መከላከያው÷ ከመንግሥት አስተዳደር (ሲቪል ሰርቪስ) መ/ቤት እስከ ልማት ድርጅት፣ ከዲፕሎማቲክ ሚሲዮኑ (ለመሆኑ በኢትዮጵያ የተነሱ አገዛዞች እስከ መቼ ይሆን ይህንን ታላቅ ተግባር የአኩራፊዎችና የሥልጣን ተቀናቃኞች ማራቂያ እና ማጽናኛ፤ የጡረታ ማሳለፊያ፤ የድርጅት አባላት መጠቃቀሚያ፤ የደናቁርት መሸሸጊያ ወዘተ የሚያደርጉት?) እስከ መንግሥታዊ ያልሆኑ  ድርጅቶች ኃላፊነትና ተቀጣሪነት ወዘተ ከለላና ጥግ አግኝተው ማየት፤ በጭራሽ በጭራሽ በጭራሽ የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት አይደለም፡፡ እነዚህ የአገር ጉዶች እና ‹ባለ ጊዜ/ተረኞች› ነን ባዮች የዐቢይን መንግሥት ከለላ አድርገው ባሉበት ሁኔታ፤ የድርጅት አሠራር በቀጠለበት ሁኔታ ቢያንስ በመንግሥት መ/ቤት ውስጥ እንዴት አገልግሎት መስጠት ይቻላል? ለመሆኑ የመንግሥት ሠራተኛ በየሥራ መስኩ አገራዊ ፖሊሲ አቀራረፅ ላይ ተሳታፊ ሆኖ ያውቃል? ሃሳብ እንዲያዋጣ ተጠይቆ ያውቃል? እንደ ተአምር ሆኖ ቢሳተፍ እንኳን ሃሳቡ ምንም ያህል ጠቃሚ ቢሆን እንደ ግብአት ተወስዶ ያውቃል? አዎንታዊ መልስ አናገኝም፡፡

ወደ ቀደመ ነገሬ ልመለስና የዐቢይ መንግሥት አገር በማረጋጋት በጅምር የቀረውን የለውጥ ሂደት ለማስቀጠል ተደጋግሞ በዚህ አስተያየት አቅራቢም ሆነ የኢትዮጵያ ነባራዊና መፃኢ ሁኔታ የሚያስጨንቃቸው ዜጎች እንዳሳሰቡት ብሔራዊ የመግባቢያ ጉባኤ/የመመካከሪያ መድረክ ማካሄዱ ይዋል ይደር የማይባል ቀዳሚ አጀንዳ ነው፡፡ የዜጎች እገዛም ከሚገለጽባቸው ዓይነተኛ መንገዶች አንዱና ዋናው በዚህ አገራዊ ጉባኤ በሚወሰኑ ብሔራዊ አጀንዳዎች ላይ የሚመሠረት ይሆናል፡፡

ይህ ወቅት በጭራሽ ስለ ምርጫ የምንነጋገርበት አይደለም፡፡ በጉባኤው/በመድረኩ ሥልጣን ላይ ያለውን የዐቢይ መንግሥት ጨምሮ የተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ባገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ምሁራን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተወካዮች፣ የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮች፣ የማኅበረሰብ ተቋማት ተወካዮች፣ የወጣቶች ተወካዮች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የባህላዊ ድርጅቶች መሪዎችና የአገር ሽማግሌዎች፣ ባጠቃላይ ኹሉንም የኅብረተሰብ ክፍሎች የሚወክሉ ዜጎች (ከድርጅታዊ አሠራር በፀዳ መልኩ) መሳተፋቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ጉባኤው እንደ አስፈላጊነቱ የሕግ ማዕቀፍ ኖሮት ሥልጣንና ተግባሩ በሕግ ይወሰናል፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ብሔራዊ መግባባት የሚያሻቸው አንኳር አገራዊ ጉዳዮችን ይለያል (የአገር ማረጋጋት፤ ባላፉት 27 ዓመታት በአገርና በሕዝብ ላይ በአገዛዙ በጋራና በግለሰብ ኃላፊዎችና አባላት የተፈጸሙ ወንጀሎችን በፍርድና በዕርቅ/ይቅርታ ሥርዓት የሚታዩበት አግባብ፤ እና  ከኢትዮጵያ ሕዝብ የተዘረፉትን ሀብቶች ባገር ውስጥም በውጭ የሸሸውን ጨምሮ)፤ ጥናት ለሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ብቃት ያላቸው ግብረ ኃይሎችን ያደራጃል፤ውሳኔዎችን ያስተላልፋል፤ ተግባራዊነታቸውን ይከታተላል፡፡ ይህ የብሔራዊ መግባባት ምክክር ጉባኤ በእጅጉ ሊታሰብበት ይገባል፡፡

 

ቤተክህነቱ

 

የዐቢይ መንግሥት ከሚወደስበት ተግባር አንዱ ተደርጎ የሚቆጠረው በኢኦተቤ/ክ ባገር ውስጥና በውጭ በሚገኙ ‹አባቶች› መካከል የነበረውን አለመግባባት በዕርቅ ቋጭቷል የሚለው ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር ቤተክርስቲያኒቱን የማዳከምና የማጥፋት፣ ለዚህም ዓላማ በቤተክህነቱ ጉዳይ ውስጥ በግልጽ ጣልቃ በመግባት ክፍፍሉን ያመጣው የወያኔ ትግሬ አገዛዝ መሆኑ የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ ለዚህም በመሣሪያነት በዘረኝነት የታወሩ ‹አገልጋዮችን› እና አሠረ ክህነት የሌላቸው ወንበዴዎችን በማሠማራት ቤ/ክርስቲያኒቷን አምሷታል፤ የወንበዴዎችና የዘራፊዎች ዋሻ አድርጓታል፡፡ ዐቢይ በዚህ ‹የማስታረቅ ሚና› የፖለቲካ ጥሪት ያገኘበት ቢሆንም፣ በዚህ ጉዳይ ላይ በወቅቱ ባቀረብኹት አስተያየት ዕርቁ እውነት እንዳልሆነና ተድበስብሶ የታለፈ መሆኑን ገልጬአለሁ፡፡ እንደተነገረውም ‹ሁለት ሲኖዶሶች› አልነበሩም፡፡ ተፈጸመ ስለተባለው ‹ዕርቅ› በወቅቱ ያቀረብኹትን አስተያየት በሚከተለው አድራሻ ማየት ይቻላል፡፡

‹‹ተካክሎ መበደል (ከይኄይስ እውነቱ)›› https://www.ethioreference.com/archives/12945

የመንግሥት ግልጽ ጣልቃ ገብነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ባለፉት 27 ዓመታት ቤ/ክህነቱ ለደረሰበት ኹለንተናዊ ቀውስ መሠረቱ ከመንፈሳዊነቱ የተራቆቱ፤ ደሀ ተበደለ ፍርድ ተጓደለ ብለው ኃላፊነታቸውን በጥብዐት ለመወጣት የተሳናቸው፤ የእረኝነት ሥራቸውን ዘንግተው መንጋውን የበተኑ፤ አንዳንዶቹ በታላቅ መዓርግ የተቀመጡ ‹አገልጋዮች› በኦርቶዶክስ ካባ ተጀቡነው ውስጣቸው ነጣቂ ተኩላ (መናፍቃን) መሆናቸው፤ እንደ ጎሣ ፖለቲከኞቹ ሊጠብቁት አደራ የተቀበሉትን መንጋ በዘር ከፋፍለው ርስ በርሱ በጥላቻ እንዲተያይ ያደረጉ፤ በዓለማዊ ጥቅም የታወሩ፤ አንዳንዶቹ በአብነቱም ሆነ በአስኳላው ትምህርት ‹ጨዋዎች› መሆናቸው፤ ከዲቁና እስከ ጵጵስና ያሉ የቤተክርስቲያኒቱ አገልግሎቶች በገንዘብ የሚገዙ መሆናቸው (በዚህ መልኩ የተሰየሙትን ሐሳውያን አገልጋዮችን እና በእምነታቸው ኑፋቄ እንዳለባቸው የሚታወቁ ‹አባቶችን› ተገሥፀው እንዲመለሱ ወይም በአቋማቸው ከፀኑ ተወግዘው እንዲለዩ ሳይደረጉ በ‹ዕርቅ› ስም ይዞ ለመቀጠል መወሰኑ) ፤ ከጠ/ቤ/ክህነት እስከ አጥቢያ ቤ/ክርስቲያን (በተለይም በከተሞች የሚገኙ አድባራትና ገዳማት) ያሉ ዘራፊዎች ላይ (እንደ አግባቡ በፍርድም ሆነ በአስተዳደራዊ ርምጃ) ተገቢውን ውሳኔ ለመስጠት ድፍረቱ የሌላቸው መሆናቸው፤ የቤ/ክርስቲያኗን የሰው ኃይል፣ የፋይናንስ እና ቅርስ አስተዳደር ለማዘመን ብቃቱም ፍላጎቱም የሌላቸው መሆኑ፤ ወዘተ ይጠቀሳል፡፡ እስከ ቅርቡ የቡራዩ ጭፍጨፋ ላለቁት ሕፃናት፣ ወጣቶቸና እናቶች እንደ ፖለቲከኞች ከማውገዝ ባለፈ በጋራ የፍትሐት ሥርዓት አልፈጸመችም፡፡ ለዚህም ነው ቤ/ክህነቱ ከቃል ስብከት ባለፈ ከምእመኑ ለሚሰጠው ገንዘብ እንጂ  ለሕይወቱ እንደማይጨነቅ ባንድ አስተያየቴ ለማሳየት የሞከርኹት፡፡ ‹‹ያለሽ መስሎሻል ተበልተሽ አልቀሻል፤ ለመላው የኢትዮጵያ ቤ/ክ ምእመናን ወምእመናት አድባራት ወገዳማት [ከይኄይስ እውነቱ] ›› https://www.satenaw.com/amharic/archives/54532

 

ከሁሉ አስቀድማችሁ ለአገር ሰላም ጸልዩ ብላ የምታስተምር ቤ/ክርስቲያን አገራችን ባራቱም ማዕዝናት በተወጠረችበት ወቅት ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ በምእመናን ብትጎተጎትም ምሕላ ለማወጅ ዳተኝነትን ስታሳይ ቆይታለች፡፡ ይህ አስተያየት አቅራቢ የቅርቡን ለማስታወስ በአዲሱ ዓመት ሁለተኛው ወር መባቻ ላይ የምሕላ ጸሎት ጥሪውን ለቤ/ክህነቱ አቅርቦ ነበር፡፡ ሰሚ ጆሮ ባያገኝም፡፡ ‹‹የምሕላ ጥሪ (ከይኄይስ እውነቱ) ›› https://www.ethioreference.com/archives/14225

ሰሞኑን ቤተክህነቱ ባደረገው መደበኛ ስብሰባ ቢዘገይም አንዳንድ በጎ ውሳኔዎችን እንዳሳለፈ ከመግለጫው ለመረዳት ችለናል፡፡ ለአብነት ያህል ጸሎተ ምሕላ እንዲያዝ መታወጁ፡፡ ከስብሰባው አጀንዳዎቹ አንዱ በውጭ የሚኖሩ ጳጳሳትና ሌሎች አገልጋዮችን ምደባ የሚመለከት ነበር፡፡ የቤ/ክርስቲያኒቱ ‹አገልጋዮች› መንፈሳዊ ሕይወት በምን ደረጃ እንደዘቀጠ በሚያሳይ መልኩ አብዛኞቹ ከውጭ ወደአገር ቤት መጥተው በስብሰባው የተካፈሉ ‹አገልጋዮች› የአገር ውስጥ ምደባን አንቀበልም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡ ይህ ካልተደረገ ‹እንገነጠላለን› እስከ ማለት የደረሱበት ተዐብዮ ጆርን ጭው የሚያደርግ ነው ብለን ብቻ የምናልፈው አይደለም፡፡ እነዚህ ግለሰቦች ‹ተገልጋዮች› እንጂ አገልጋዮች ባለመሆናቸው፤ ለዓለም ምዉት ነን ካሉ በኋላ (መነኰሳቱን ማለቴ ነው) 24 ሰዓት ስብሐተ እግዚአብሔር ከሚቀርብባቸው የኢትዮጵያ አድባራትና ገዳማት ይልቅ በማየትም በመስማትም ለመንፈሳዊ አገልጋይ እጅግ ፈታኝ በሆኑት ግብረ ሰዶምና ግብረ ጎሞራ በሰብአዊ መብት ሽፋን ባደባባይ በሚፈጸምባቸው ባዕዳን አገራት ካልተመደብን እንገነጠላለን (ከየት እንደሚገነጠሉም እግዚአብሔር ይወቀው አስቀድመው ከቤተክርስቲያን አንድነት ራሳቸውን ለይተዋልና) ማለታቸው ከመነሻውም የቤተክርስቲያኒቱ ገንዘቦች አለመሆናቸውን ያመለክታል፡፡ እንደነዚህ ያሉትን ‹ተገልጋዮች› ቤተክርስቲያናችን በምንም መልኩ ማስታመም የለባትም፡፡ ቢያንስ ከአገልግሎትና ኃላፊነታቸው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ማንሳት ያስፈልጋል፡፡ ቤ/ክርስቲያን እኮ የእነ አባ ማትያስና አባ መርቆሬዎስ ወይም የእነ ቀሲስና መምሬ እገሌ የግል ገንዘብ አይደለችም፡፡ ለዚህም ነው በቀደመ አስተያየቴ ተፈጸመ የተባለው ዕርቅ የውሸት ነው ለማለት የደፈርኩት፡፡ ቆብና ጥምጣሙን÷ ካባና መስቀሉን ለዓለማዊ ፍላጎታቸው ማሟያ ያደረጉ÷ሲመተ ክህነትን በገንዘብ የሸመቱ ‹ሲሞናውያን›÷ መንፈሳዊ ሕይወት ሳይገባቸው (ላልቶም ጠብቆም ሲነበብ በሚሰጠው ትርጕም) የተቀላቀሉ መንገደኞችን አስቀድሞ መለየት ይገባ ነበር፡፡

ቤተክርስቲያን እስከ ሙሉ መንፈሳዊ ሀብቷና ቅርሷ የምእመናን ነች፡፡ መዘባነኑ በማን ላይ ተቀምጦ ነው? አልፎ ተርፎም ቅርሶቿ የኢትዮጵያውያን በሙሉ ሀብቶች መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል፡፡ አሁንም እግዚአብሔር የሚያውቃችሁ እውነተኛ መንፈሳውያን አባቶች በቤተክርስቲያናችን አስተዳደር ላይ ካላችሁ ይዋል ይደር ሳትሉ ከሚመስሏችሁ ጋር በጋራ መክራችሁ በወያኔና ለርሱ ባደሩ ሐሳውያን ‹አገልጋዮች› መሣሪያነት በአድባራትና በገዳማት በልዩ ልዩ ኃላፊነት (አንዳንዶቹም ክህነቱም ሳይኖራቸው) የተቀመጡና ቤ/ክርስቲያኒቱን እያወኩ ካሉ መናፍቃን እና ዘራፊዎች ማፅዳት ይጠበቅባችኋል፡፡ አለበለዚያ ከትርፉ ሳይሆን ከዕለት ጉርሱ ነጥቆ ለቤተክርስቲያኒቱ መባዕ የሚያገባው ምእመን ገንዘቡን ለመናፍቃንና ለዘራፊዎች የሚሰጥበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ስለ ቤተክርስቲያናችን ዝም አንልም፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የሆኑ የቤተክርስቲያኑትን ልጆች በምግባር በሃይማኖት በማነፅ፣ በማስተባበር፣ በሌሎችም ዘርፈ ብዙ ተግባራት እያገዘ የሚገኘውንና የቤተክርስቲያናችን አለኝታነቱን ያረጋገጠውን ማኅበረ ቅዱሳንን በመናፍቃንና በዘራፊዎች ከመወንጀል/ማስወንጀል ይልቅ ይህን የቤተክርስቲያናችን አንድ አካል የሆነውን ማኅበር ዘርፈ ብዙና መጠነ ሰፊ ችግሮቻችንን ለመፍታት እንጠቀምበት ዘንድ እንደ አንድ ምእመን ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡

Filed in: Amharic