>
4:02 am - Friday July 1, 2022

"ለኦሮሞ የሚጠቅመው ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር አገሩን የተሻለች ማድረግ ነው!!!" (ዶ/ር መረራ ጉዲና)

“ለኦሮሞ የሚጠቅመው ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር አገሩን የተሻለች ማድረግ ነው!!!”

 

ዶ/ር መረራ ጉዲና
 
* የዶ/ር መረራ ፖለቲካዊ ምልከታ ፣ ግምገማና ተስፋ!
መደመር መቀነስ እያልን ጊዜያችንን ስናጠፋ፣ ጊዜው እንዳይመሽብንም እሰጋለሁ!
  *  ሁሉም የሚጋጩ ህልሞቹን ይዞ ነው ወደ ፖለቲካ ሜዳው የገባው!
     *  የፖለቲካ ልሂቃኑ ከጠባብ ህልም መውጣት አለባቸው!
*  የመገንጠል አጀንዳን ለማንሳት የሚያበቃ ምክንያት የለንም!
በአገሪቱ የፖለቲካ መልክአ ምድር ላይ የተለያዩ አስደማሚ ለውጦች እየታዩ ባሉበት በአሁኑ ወቅት፤ አስጊና ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎችም እየተከሰቱ ነው፡፡ በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ አገር ቤት መግባታቸውን ተከትሎም የተለያዩ ችግሮችና ውዝግቦች እየተፈጠሩ ነው፡፡ አንጋፋው ፖለቲከኛና የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና ለዚህ ምክንያቱ፣ ሁሉም የሚጋጩ ህልሞቹን ይዞ ወደ ፖለቲካው ሜዳ በመግባቱ ነው ይላሉ፡፡ በለውጡ ሂደቱ፣ በኦፌኮ እና ኦነግ ግንኙነት፣ በአዲስ አበባ ጉዳይና ሌሎች አገራዊ አጀንዳዎች ላይ አንጋፋው ፖለቲከኛ ምልከታቸውን፣ ግምገማቸውን እንዲሁም ተስፋና ስጋታቸውን ለአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ እንደሚከተለው አጋርተውታል፡፡

     በጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አመራር የመጡ ለውጦችን በተመለከተ ምን አስተያየት አለዎት?
በአጠቃላይ ተስፋ የሚሰጡ እርምጃዎች ተወስደዋል፤ ነገር ግን መሰረታዊ የሆኑ ያልተሰሩ ብዙ ጉዳዮች አሉ፡፡ በተለይ መንግስት እና ተቃዋሚ፤ ተቃዋሚ እና ተቃዋሚ ውይይት አልጀመሩም፡፡ የዲሞክራሲ ስርአትን ለማምጣት ወይም ለውጡን የተሳካ ለማድረግ እስካሁን ስምምነት የተደረገበት ፍኖተ ካርታ የለም፡፡ ብሔራዊ ስምምነት አስፈላጊ ቢሆንም እስካሁን አልተደረገም፡፡ ስለዚህ ጥንቃቄ የተሞላበት ተስፋ ነው የማደርገው፡፡ ያልተፈቱ ብዙ መሰረታዊ ጉዳዮች አሁንም አሉ፡፡
ምንድን ናቸው እነዚህ ያልተፈቱ መሰረታዊ ጉዳዮች?
እኔ ደጋግሜ እንዳልኩት፤ ለዶ/ር ዐቢይ አሁንም ፈተና የሚሆንባቸው፣ ኢህአዴግን ለለውጥ ማዘጋጀት ነው፡፡ ይሄ አሁንም ገና ያልተፈታ ችግር ነው፡፡ “የኢትዮጵያ የታሪክ ፈተናዎች እና የሚጋጩ ህልሞች” በሚለው መፅሐፌ በግልፅ እንዳስቀመጥኩት፤ አሁንም ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች የሚጋጩ ህልሞቻቸውን ይዘው ነው ወደ ለውጡ የፖለቲካ ሜዳ የገቡት፡፡ ከሞላ ጎደል ይሄ ለውጥ የመጣው በወጣቶች በተለይም በኦሮሞ ወጣቶች ደም ነው፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ይሄን በወጣቶች ደም የመጣን ለውጥ በአግባቡ ማጣጣም እየቻሉ ያለ አይመስልም፡፡ ሁሉም የሚጋጭ ህልሙን ይዞ ነው ወደ ጨዋታው ሜዳ የገባው፡፡
“የሚጋጭ ህልም” ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
ለምሳሌ ኢትዮጵያ ወዴት ትሂድ? እንዴት ትሂድ? በሚለው ላይ ሁሉም የየራሱ ህልም ነው ያለው። የተቀራረበ አይደለም፡፡ ምርጫ እንዴት ይካሄድ? መሰረታዊ የሀገሪቱ ፖለቲካዊ ችግሮች እንዴት ይፈቱ? በሚሉት ላይም አንዱ ከአንዱ ያልተቀራረበ አጀንዳ ይዞ ነው የተቀመጠው፡፡ ወደ ሃገር ቤት የገቡ የፖለቲካ ኃይሎች ጭምር እንዴት በህግ አግባብ መንቀሳቀስ ይቻላል በሚለው ላይ እንኳ የመግባቢያ ውል የላቸውም፡፡ በመንግስትና በእነሱ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚወስን የህግ ስምምነት አልተደረገም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በነፃነት መንቀሳቀስ ትችላላችሁ ብሎ ቃል ገብቶላቸዋል እንጂ በመንግስት ደረጃ የተፈራረሙት ስምምነት ይኑር አይኑር እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ግን በመንግስትና በእነዚህ ተቃዋሚ ኃይሎች መካከል ከቃል ያለፈ፣ በሰነድ የታገዘ ስምምነት እንደሌለ እገምታለሁ፡፡
ከዚህ ቀደም “መድረክ” በቀጥታ ከመንግስት ጋር ድርድር ለማድረግ ያቀረበው ጥያቄ ምን ላይ ደረሰ?
መድረክ ከአራት ወር በፊት የድርድር ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡ አስራ ሰባት የመደራደሪያ ነጥቦቹን አቅርቦ ነበር፡፡ ምናልባት አንዳንዶቹ ተመልሰዋል፡፡ ለምሳሌ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተነስቷል፤ የፖለቲካ እስረኞች ከሞላ ጎደል ተፈትተዋል፡፡ በዚህም የተነሳ  የፖለቲካ ምህዳሩ ሰፍቶ ታይቷል፡፡ ነገር ግን ላቀረብናቸው መሰረታዊ የመደራደሪያ ነጥቦች መንግስት መልስ አልሰጠንም፡፡
መልስ ያልተሰጣቸው የመደራደሪያ ነጥቦቻችሁ ምንድን  ናቸው?
ለምሳሌ የሃገሪቱን ዲሞክራሲ ተስፋ ባለው መንገድ ወደፊት ሊያራምድ ይችላል ብለን ያቀረብነው፣ ቢያንስ ሰፊ የህዝብ ድጋፍ አላቸው የሚባሉ የፖለቲካ ኃይሎች ያሉበት የፖለቲካ ብሔራዊ መግባባት ስብሰባ ቢጠራ የሚለው ይገኝበታል፡፡ ያ የሚሰበሰበው የብሔራዊ መግባባት ጉባኤ በሚደርስበት ስምምነት መሰረት፣ ብሔራዊ የአንድነት መንግስት ቢቋቋም የሚል ነው፡፡
ብሔራዊ የአንድነት መንግስት እንዴት ነው እንዲመሰረት የምትፈልጉት?
ዶ/ር ዐቢይ አህመድ የያዙት አመራርነት እንዳለ ሆኖ፣ ነገር ግን የአመራር መሰረቱ ይስፋ ነው የምንለው። ኢህአዴግ ብቻውን ይሄን አገር የማስተዳደር አቅም የለውም፡፡ ስለዚህ የለውጡን ተስፋ ከቅልበሳ ለማዳን፣ ሁሉም ህዝብ የኔ መንግስት ነው ብሎ ሊንቀሳቀስ በሚችልበት ደረጃ መሰረቱን ማስፋት የግድ ነው። በሌላ በኩል፤ ቀጣዩን ምርጫ በህዝብ የታመነ፣ ነፃና ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ፣ የሁሉንም ፍላጎቶች ባጣመረ መልኩ የሚመራ የፖለቲካ ኃይል ያስፈልጋል። አሁን ያለው ኢህአዴግ ብቻ ነው። ኢህአዴግ ለውጥ አመጣለሁ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩም እኔ አሸጋግራችኋለሁ ይላሉ፡፡ ይሄ አሁን ባለው የሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ የሚቻል አይደለም፡፡ አንድ ዐቢይ ከላይ ተቀምጦ፣ እርስ በእርሱ ያልተጣጣመው ኢህአዴግ ነው ከስር ያለው፤ ስለዚህ ሁሉን ያካተተ የብሔራዊ አንድነት መንግስት ተቋቁሞ፣ በቀጣይ ተአማኒ ምርጫ ማካሄድ የሚቻልበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡ ትናንት ምርጫ ሲሰርቁ ሲያሰርቁ ለነበሩ ግማሽ ሚሊዮን ያህል የምርጫ አስፈፃሚዎች፣ ዶ/ር ዐቢይ ሰብስቦ “ምርጫ መስረቅ ወንጀል ነው” ብሎ ስለመከራቸው ብቻ እጃቸውን ሰብስበው ይቀመጣሉ፤ በንፅህና ይሰራሉ ማለት አይቻልም፡፡ ስለዚህ ቀጣዩ ምርጫ የተሳካ ዲሞክራሲያዊ ስርአትን ማዋለጃ እንዲሆን፣ ምርጫ ቦርድን ጨምሮ የዲሞክራሲ ተቋማትን ሪፎርም ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ሪፎርም ደግሞ ኢህአዴግ ብቻውን እየመራ የተሳካ አይሆንም፡፡ ሪፎርሞቹ የተሳኩ እንዲሆኑ በተለይም የተሳካ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ፈጠራ ላይ ሁሉም ተሳታፊ እንዲሆን፣ ብሔራዊ የአንድነት መንግስት መቋቋሙ ወሳኝ ነው። አሁንም ያለነው በኢህአዴግ እና በእግዚአብሔር እጅ ነው። ከዚያ ያለፈ ስምምነት የለንም፡፡ ስለዚህ ለውጡን ከቅልበሳ ለማዳንና የተሳካ ለማድረግ ብሔራዊ የአንድነት መንግስት ያስፈልገናል፡፡ ዝም ብሎ ህጎች ተሻሽለዋል፤ ሪፎርም ተደርጓል መባሉ ብቻ መተማንን ፈጥሮ፣ የሀገሪቱን የፖለቲካ ችግር አይፈታውም፡፡ ለዚህ ነው “መድረክ” ለሀገሪቱ ፍኖተ ካርታ ያስፈልጋል የሚለው፡፡ ዛሬ በብዙ ቦታዎች ያለመረጋጋት ይታያል። ወጣቱ አሁንም የተለያዩ ጥያቄዎችን እየጠየቀ ነው። ትጥቅ ፍቱ አንፈታም የሚሉ ውዝግቦች ይሰማሉ፡፡ ምርጫ ደግሞ ማካሄድ የሚቻለው በተረጋጋ ሃገር እንጂ በተኩስ ቀጠና አይደለም፡፡ ስለዚህ ሃገሪቱ እንድትረጋጋ ከተፈለገ፣ የብሔራዊ አንድነት መንግስት መስርቶ፣ ሃገርን የማረጋጋት ስራ በመስራት፣ ፍኖተ ካርታ በማስቀመጥ፣ የወደፊቱን የሀገሪቱን ጉዞ መተለም ያስፈልጋል፡፡
የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር (ኦነግ) እና በእርስዎ የሚመራው ኦፌኮ የመሰረቱት ግንኙነት ምን ይመስላል?
እኛም የራሳችን፣ እነሱም የራሳቸው ፕሮግራም አላቸው፡፡ ከመሪዎቹ ጋር የተነጋገርነው ወጣቱ ወደ መከፋፈል፣ ወደ ሌላ ችግር እንዳይገባ በጋራ መስራትና የኦሮሞን ህዝብ ትግል ወደፊት በተሻለ መልኩ ለማስቀጠል የሚል ነው፡፡ ከዚህ ያለፈ አንድ ሁለት ብለን የተስማማነው ነገር ግን የለም፡፡ ህዝቡን በአንድነት ለነፃነቱ፣ ለመብቱ፣ ለክብሩ እንዲታገል ለማድረግ ነው የጋራ መግባባት ላይ የደረስነው፡፡ ከዚያ ያለፈ ግንኙነት የለንም፡፡
ኦነግ ወደ ሃገር ውስጥ ከገባ በኋላ እየተፈጠሩ ያሉ ውዝግቦች ምክንያታቸው ምንድን ነው ይላሉ?
ያላለቁ ነገሮች ወይም ስምምነቶች ያሉ ይመስለኛል። ኦነግ አስመራ ላይ ከገዥው ፓርቲ ጋር ሲደራደር የተስማማባቸውን ነገሮች በግልፅ አላውቅም፤ ግን ያላለቁ ጉዳዮች ሊኖሩ ይችላሉ የሚል ግምት አለኝ። አሁን ችግር እየተፈጠረ ያለውም በእነዚህ ያላለቁ ጉዳዮች ይመስለኛል፡፡
በኦሮሞ ህዝብ ስም የተደራጁ በርካታ የፖለቲካ ኃይሎች አሉ፡፡ የድርጅታችሁ (ኦፌኮ) የትግል ዓላማ  ምንድን ነው?
የኛ ድርጅት ዓላማ፤ የኦሮሞ ህዝብ ከተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብና ፍላጎት ጋር ሳይጋጭ፣ በመከባበርና በመቻቻል ሁሉም በእኩልነት የሚኖርበት ኢትዮጵያ እንድትፈጠር ነው፡፡ ሁላችንንም በእኩልነት የምታስተናግድ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ መመስረት ነው የኛ ግብ፡፡ እኛ የመገንጠል አጀንዳ መጀመሪያውኑም የለንም፡፡ ነገም ከነገ ወዲያም የመገንጠል አጀንዳን ለማንሳት የሚያበቃን ምክንያት የለንም፡፡ ምክንያቱም የኦሮሞ ህዝብ ትልቁ የኢትዮጵያ ክልል ወይም የኢትዮጵያ እምብርት የሚባለውን አካባቢ የያዘ ህዝብ ነው፡፡ ለመገንጠል ፖለቲካ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጡም አመቺ አይደለም፡፡ ስለዚህ ለኦሮሞ የሚጠቅመው ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር ሃገሩን የተሻለች ማድረግ ነው፡፡ የኛ እምነት ይሄ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት በአንድ በኩል ጽንፈኛ የብሔር ፖለቲካ፣ በሌላ በኩል የዜግነት ፖለቲካ እየተቀነቀነ  ነው፡፡ ይሄ  በሀገሪቱ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ  ላይ ምን ተፅዕኖ ይኖረዋል?
በዋናነት ይህ ችግር ያለው ህዝቡ ዘንድ አይደለም። የፖለቲካ ልሂቃኑ ዘንድ ያለ ችግር ነው፡፡ ለምሳሌ የጎንደር አርሶ አደር፣ የሸዋን ወይም የሃረርን አርሶ አደር የመጉዳት ፍላጎት የለውም፡፡ የኦሮሞ አርሶ አደር ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር የመጋጨት ፍላጎት የለውም። ትልቁ ችግር ያለው ደጋግሞ እንዳልኩት፣ ልሂቃኑ የሚጋጩ ህልሞቻቸውን ገደብ ሳያበጁ እየተንቀሳቀሱ መሆኑ ላይ ነው፡፡ ያለ ገደብ የተቀመጡ ህልሞችን ይዘን የተሻለ ሰላምና መረጋጋት ለመፍጠር ያስቸግራል፡፡ ለዚህ ሃገር ወደፊት መቀጠል የመጀመሪያው የመፍትሄ እርምጃ መሆን ያለበት፣ የብሔራዊ መግባባት መድረከ ነው፡፡ ሃገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች የሚጋጩ ህልሞቻቸውን እንዴት ማስተናገድና ማቻቻል እንዳለባቸው በዚህ መድረክ የተሻለ ግንዛቤ ሊገኝ ይችላል፡፡ ከመጠፋፋት ይልቅ የተሻለ ትርፍ የሚያገኙበት አቅጣጫ ላይ መስማማታቸው አስፈላጊ ነው፡፡ ይሄ ካልሆነ ግን የሩዋዳ፣ የሶማሌ ወይም የሌሎች የፈረሱ ሃገራት እጣ ሊገጥመን ይችላል፡፡ አሁንም እኮ ዜጎች በግጭት እየሞቱ እየተፈናቀሉ ነው፡፡ ይሄ ቀልድ የሚመስል ነገር በኋላ ብዙ ዋጋ ያስከፍላል። ስለዚህ ልሂቃኑ ህልሞቻችንን በገደብ ካላደረግን በቀር በህልም አለም እየጋለቡ መኖር ነው የሚሆነው። የህልም አለም ግልቢያ ደግሞ የት እንደሚያደርስ አይታወቅም፡፡ የፖለቲካ ልሂቃኑ ከጠባብ ህልም መውጣት አለባቸው። ለዚህ ነው ደጋግሜ ብሔራዊ መግባባት መፈጠር አለበት የምለው፡፡ የዶ/ር ዐቢይ ትልቁ ፈተናም፤ ይሄ የብሔራዊ መግባባት ጉዳይ ነው፡፡ ይሄን ለመፍጠር መትጋት በጣም ወሳኝ ነው። ዳያስፖራውን በሰላም ሃገራችሁ ግቡ ማለቱ ጥሩ ነው፤ ነገር ግን የገባው ኃይል ሀገር ውስጥ ምን ይዞ ይንቀሳቀሳል? ፍኖተ ካርታችን ምንድን ነው? የሚለው በኢህአዴግ በጎ ፍቃድ ብቻ ሳይሆን ህዝባዊ መሰረትና ድጋፍ ያላቸው የፖለቲካ ኃይሎች ቁጭ ብለው በጋራ መክረው፣ አንድ ብሔራዊ ስምምነት ላይ መድረስ አለባቸው፡፡ ይሄ ካልሆነ በየቦታው የሚነሱት ግጭቶች የሚቀሩ አይመስለኝም፡፡ አጉል ተስፋ የያዘው ኃይልም እዚያም እዚህም የሚያደርጋቸው ንክሻዎች አላስፈላጊ ዋጋ ሊያስከፍሉን ይችላሉ፡፡
አሁን በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አገር ቤት ገብተዋል፡፡ ይህ በቀጣይ ምን ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል?
ይሄ ከባድ ነገር ነው፡፡ ለዚህ ነው ኢህአዴግ ብቻውን የ100 ሚሊዮን ህዝብ ፍላጎትን ሊያስተናግድ አይችልም፤ የብሔራዊ አንድነት መንግስት ያስፈልጋል የምለው፡፡ የፖለቲካ ኃይሎቹ ፍላጎታቸውን በህግና በስርአት ካልገሩ ወይም ህልማቸውን ካልገደቡ ፖለቲካችን በቀላሉ ወደ ጨረባ ተዝካር ሊለወጥ ይችላል፡፡ በዚህም አላስፈላጊ ዋጋ ልንከፍል እንችላለን። በዚህ ሁኔታ ምርጫ እናድርግ ከተባለም፣ ከ97 የበለጠ ፈተና ሊገጥመን ይችላል፡፡ መታወቅ ያለበት ዛሬም ብዙ ተዳፍነው ያሉ ቦንቦች አሉ፡፡ ስለዚህ በአጉል ተስፋ ብቻ ከመጓዝ፣ ከወዲሁ የጋራ ገዥ ህግና ስርአት ማበጀት ያስፈልጋል፡፡ ቀጣዩ ምርጫ የብሔራዊ መግባባት ውጤት መሆን አለበት፡፡ አሁን የኢትዮጵያ ፖለቲካ አልፋና ኦሜጋ ብሔራዊ መግባባት ብቻ ነው፡፡ ዶ/ር ዐቢይም ይሄን አርቀው ማየት አለባቸው፡፡
“የኢትዮጵያ ታሪክ ፈተናዎች እና የሚጋጩ ህልሞች” በሚለው መፅሐፍዎ፤ “የሀገሪቱን ፖለቲካ የበላው ቡዳ አልተገኘም” ብለዋል፡፡ አሁንስ ፖለቲካችንን የበላው ቡዳ አልተገኘም?
አልተገኘም፡፡ ሁሉም ሌላውን ይከሳል እንጂ ቡዳው አልተገኘም፡፡ ቡዳው ግን አሁንም አለ፡፡ ወይም ሁላችንም በተለያየ ደረጃ ቡዳዎች ነን ወይም ቡዳው ኢህአዴግ ነው፡፡ ቡዳው አሁንም ተለይቶ አልወጣም። በፖለቲካችን ውስጥ አለ፡፡ ይሄ ቡዳ እስካልወጣ ድረስ የምናደርጋቸው ጥረቶች ውጤት አያመጡም፡፡ መደመር መቀነስ እያልን ጊዜያችንን ስናጠፋ፣ ጊዜው እንዳይመሽብንም እሰጋለሁ፡፡
ለእርስዎ ኢትዮጵያዊነት ምንድን ነው?
እስከ ዛሬ ገዥው መደብና የፖለቲካ ልሂቃን ኢትዮጵያዊነትን በማይሆን መንገድ ለመጠቀም ሲሰሩ ኖረዋል፡፡ እንደውም የኢትዮጵያዊነት ሰርተፍኬት ሰጪና ከልካይ እኔ ነኝ ብለው ራሳቸውን የሾሙ አሉ፡፡ በአንድ በኩል ይሄ ችግር አለ፡፡ በሌላ በኩል፤ ለራሳቸው ህዝብ እንኳ ያልሆኑ መንግስታት ባጠፉት ጥፋት፣ ህዝብ ባልሆነ መንገድ የሚፈርጁ አሉ፡፡ እነዚህ ሁለት ፅንፎች ይታያሉ፡፡ ሰርተፍኬት ሰጪ እኔ ነኝ የሚሉት በአንድ ፅንፍ፣ “አይ እኔ በዚህ አልኖርም” የሚለውና ልገንጠል የሚለው በሌላ ፅንፍ አለ፡፡ ዋናው የዚህ ችግር መንስኤ ደግሞ ህዝቡ ሳይሆን ልሂቁ ነው፡፡ በታሪክ አጋጣሚ ሁላችንም ኢትዮጵያ የምትባል ሃገር ውስጥ እንድንኖር ተደርጓል፡፡ ምናልባት በተለያየ ደረጃ፣ በፍላጎትና ያለ ፍላጎት የገቡ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ብዙ ሃገሮች በዚህ ሂደት ነው የተፈጠሩት፡፡ ስለዚህ ለኔ ኢትዮጵያዊነት የማንነት መገለጫ ነው፡፡ ኦሮሞነትና ኢትዮጵያዊነት አይጋጩብኝም፡፡ የግድ ይጋጩ ካልተባለ በስተቀር፣ ሁሉም አብሮ የማይኖርበት ምክንያት የለም፡፡ በተቻለ መጠን ግን ከላይ የገለፅኳቸውን ሁለቱን ፅንፎች ወደ መሃል አምጥተን በመግባባት ላይ የተመሰረተች ሃገርን መፍጠር አለብን፡፡ እንጣላ ከተባለ ወንድምና ወንድምም ይጣላል፡፡ መጣላት ከተፈለገ ቀላል ነው ነው፡፡ መግባባትም ከተፈለገ ቀላል ነው፡፡ እኔ ከዚህ አንፃር አብዛኛው ህይወቴን መሃል መንገደኛ ነኝ። ከመኢሶን ጀምሮ መሃል መንገደኛ ነኝ፤ መንገዱም በተሻለ ሁኔታ ተመችቶኛል፡፡
በቅርቡ አዲስ አበባ የውዝግብ መነሻ ሆና እንደነበር ይታወቃል፡፡ ኦፌኮ በአዲስ አበባ ላይ ያለው አቋም ምንድን ነው?
በታሪክ አጋጣሚ የአዲስ አበባ ከተማ፣ የኦሮሞ ህዝብም የኢትዮጵያ ህዝብም አምብርት ሆናለች። አዲስ አበባን ወደ ፍጭትና ግጭት ከማስገባት ይልቅ ሁለቱም ህዝቦች የጋራ ጥቅም አላቸው ማለቱ ይበጃል። ለምሳሌ፡- የአዲስ አበባ ህዝብ ውሃ፣ ኃይል፣ የቆሻሻ ማስወገድ አገልግሎት የሚያገኘው ከኦሮሚያ ነው። የሚበሉ ነገሮች በብዛት የሚመጡት ከኦሮሚያ ነው፡፡ ወደ ሌላው የኢትዮጵያ ክፍል መውጫው ኦሮሚያ ነው፡፡ ስለዚህ የአዲስ አበባ ህዝብ ከኦሮሞ ህዝብ የሚጣላበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ የኦሮሞ ተወላጆችም ከዘመናዊው አለም ጋር የሚገናኙት በአዲስ አበባ በኩል ነው፡፡ ዘመናዊ የሚባሉ ምርቶችን የሚያገኙት ከአዲስ አበባ ነው፡፡ ስለዚህ ሁለቱን በግድ ካላጣላናቸው በስተቀር የሚጣሉበት ምንም ምክንያት የላቸውም፡፡ ልሂቁ ግን ለማጣላት ከፈለገ ብዙ የማጣያ አማራጭ አለው፡፡ በዚያው ልክ ጥልን ማስወገጃም ብዙ አማራጭ አለው፡፡ የምርጫ ጉዳይ ነው፡፡ ዋናው የሚያስፈልገው፣ ምክክርና ውይይት ማድረግ ነው። ከዚህ ንትርክ ይልቅ እንዴት አካባቢውን እናልማ ማለቱ ነው የሚጠቅመው፡፡ ዛሬ አብዛኛው የአዲስ አበባ ሰራተኛ የሚኖረው፣ በዙሪያዋ ባሉ የኦሮሚያ ከተሞች ነው፡፡ አዲስ አበባ ብቻዋን ተለይታ ደሴት መሆን አትችልም፡፡ መልክ ባለው መንገድ ሁለቱ እየተጠቃቀሙ እንዲኖሩ ማስማማት ይቻላል፡፡ ከተማዋ በታሪክ አጋጣሚ የኢትዮጵያም የኦሮሞም እምብርት ሆና ተፈጥራለች፡፡ አስፈላጊ ከሆነ እና ጭቅጥቁ የሚበረታ ከሆነ፣ አዲስ አበባን ትቶ ሌላ የተሻለ ቦታ ዋና ከተማ ማድረግ ይቻላል፡፡ ታንዛኒያ፣ ናይጄሪያ … እንዲህ አድርገዋል፡፡ በታሪክ አጋጣሚ አዲስ አበባ የአፍሪካም መዲና ሆናለች፡፡
ለዚህ ዓይነቱ ንትርክ ተጠያቂው ማነው ይላሉ?
ኢህአዴግ ነው፡፡ ደስ ያለው ጊዜ “አዲስ አበባ ላይ ኦሮሞ ምን ጉዳይ አለው? ሂዱና ሌላ ከተማ ፍጠሩ” ብሎ ወደ አዳማ አባረራቸው፡፡ ቅንጅት አዲስ አበባን ሲያሸንፍ ደግሞ “እናንተ ናችሁ የመሬቱ ባለቤቶች” ብሎ ኦህዴድን ከአዳማ ወደ አዲስ አበባ መልሶ ቢሮ እንዲመሰርት አደረገ፡፡ አዲስ አበባ አካባቢ ልዩ ከተሞች መፈጠር አለባቸው ብሎ በሁሉም አቅጣጫ አዲስ አበባን አጠራት፡፡ በዚህ ሰፊ የሆነ የመሬት ንግድና ትርፍ ነው የተፈጠረው፡፡ ያቺ ትርፍ የብዙ ባለስልጣናትን ቀልብ ሳበችና በኦህዴድና በኢህአዴግ መካከል ግጭት ተፈጠረበት፡፡ የኦሮሞ ተቃውሞ አንዱ ምንጭ ይሄ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ነገሮች ለፖለቲካ ስልጣንና ፍላጎት ተብለው የሚደረጉ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ለግጭት ቀላል ነው፡፡ የአዲስ አበባን ፖለቲካ፣ የሁለቱን ህዝቦች ተጠቃሚነት ያማከለ አድርጎ አቅጣጫ ማስያዝ ያስፈልጋል፡፡ ዞሮ ዞሮ የተፈጥሮና የታሪክ አጋጣሚ የፈጠራቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ አዲስ አድማስ

Filed in: Amharic