>
6:38 am - Tuesday December 6, 2022

አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ የአማራ ክልልን የሚጎበኝበት ምን የተለየ ምክንያት አለ???(አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው) 

አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ የአማራ ክልልን የሚጎበኝበት ምን የተለየ ምክንያት አለ???
አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ ወያኔ የአማራ ክልል ብሎ የከለለውን  ሊጎበኙ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ ለመሆኑ የሕዝባዊ ግንባር መሪ አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ የአማራ ክልልን የሚባለውን የሀገራችንን ክፍል የሚጎበኝበት የተለየ ምክንያት አለ ወይ??? እንደኔ እንደኔ አዎ በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ ይሁን እንጅ ይህ የአቶ ኢሳይያስ ጉብኝት እነኝህን ጉዳዮች የሚያይ፣ የሚደርስ፣ አሚዳስስ የሚሆን አይመስለኝም፡፡
ሸአቢያ ባሕረ ምድርን (ኤርትራን) ከኢትዮጵያ ለመገንጠል ባደረገው ትግል ቀንደኛ ጠላቱ አድርጎ ያየው የነበረው አማራውን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በረሃ እያለ ጀምሮ እስከ በቀደም ዕርቅ ተፈጸመ እስከተባለበት ዕለት ድረስና “ከዛሬ ጀምሮ በአማራ ላይ ጥላቻንና ጠላትነትን የሚሰብኩ ዘፈኖችና የተውኔት ሥራዎች አገልግሎት ላይ እንዳይውሉ!” የሚል ትዕዛዝ እስካወጡበት ቀን ድረስ ሲያቀነቅኗቸው የኖሯቸው የትግል ዘፈኖቻቸውና ሲተውኗቸው የኖሯቸው ተውኔቶቻቸው በሙሉ አማራን ጠላት አድርገው የሚሥሉ፣ አማራን ለማጥፋት የሚያነሣሱና በአማራ ላይ ጥላቻን የሚነዙ ናቸው፡፡ ሸአቢያ በዚህም ብቻ አልተወሰነም ኢትዮጵያ ውስት ያሉ ብሔረሰቦችንና ጎሳዎችን በአማራ ላይ በማነሣሣት የአማራ ጠላት እንዲሆኑ ብዙ ሠርቷል፡፡
በዚህ ምክንያት ነው ሸአቢያ ትግሮችን በጠባብ የጎሳ ፖለቲካ መርዞ አማራን በጠላትነት ፈርጀው በመመልከት ለማጥፋትና ከኢትዮጵያም ለመገንጠል የሚታገሉ ሕወሓት የተባለን የጥፋት ኃይል በእኛ ላይ ሊመሠርትብንና ሊያታግላቸው የቻለው፡፡ ዛሬ የሀገራችንን ህልውና አደጋ ላይ የጣለው ተገንጣይ ጠባብ የጎሳ ፖለቲካ በሀገራችን ሊስፋፋ የቻለው ሸአቢያ ተገንጣዩን ጠባብ የጎሳ ቡድን ሕወሓትን ፈጥሮ በማሠማራቱ ምክንያት ነው፡፡ ከሕወሓት መመሥረት ሁለት ዓመት በፊት በ1965ዓ.ም. የተመሠረተው ኦነግ እንኳ የመገንጠል ዓላማን ዓላማው አድርጎ የተንቀሳቀሰው ሕወሓት የመገንጠል ዓላማን አንግቦ መታገሉን ካየ በኋላ ነው፡፡
ሸአቢያ ኢትዮጵያ ውስት ያሉ ብሔረሰቦችንና ጎሳዎችን በአማራ ላይ በማነሣሣት የአማራ ጠላት እንዲሆኑ በመፈለጉ ነው በደርግ ውድቀት ዋዜማ ላይ ለኦነግ ከፍተኛ ድጋፍ በሰጠበት በአሶሳው የኦነግና የደርግ ጦርነት ላይ በቦታው በነበረው ብዙ ቁጥር ባልነበረው የደርግ የጦር ክፍል ላይ ከፍተኛ ኃይል ይዘው በመዝመትና በመደምሰስ አሶሳ ከተማ ገብተው አማራ የሆኑ የከተማዋን ነዋሪ ሰብስበው ትምህርት ቤት የትምህርት መማሪያ ክፍሎች ውስጥ እየሞሉ በማጎር ትምህርት ቤቱን በከባድ መሣሪያ በመደብደብና እንዳለ በማቃጠል በንጹሐን ወገኖቻችን ላይ ዘግናኝና አረመኔያዊ ጭፍጨፋ በመፈጸም ሙሉ ለሙሉ ፈጅተው ኦነግን በአማራ እንዲጠላና በኦሮሞና በአማራ መሀከል ጠላትነት እንዲፈጠር ሸአቢያ አጋንንታዊ ሸፍጡን ሀ ብሎ የጀመረው፡፡
ይህ ዘግናኝና አረመኔያዊ ጭፍጨፋ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅች ሠራተኞች ለሰበነክ ሥራ አሶሳ በነበሩበት ወቅት የተፈጸመ በመሆኑ ይህ የተፈጸመው ግፍ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጭምር በሚገባ የሚታወቅ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ደርግ ከወደቀ በኋላም ኦነግ ሸአቢያ በቀደደለት መንገድ በመጓዝ በአማራ ላይ ምን እንደፈጸመ የምታውቁት ነው፡፡
ሸአቢያ ኤርትራን ከተቆጣጠረ በኋላም የአማራ ተወላጅ የሆኑ የደርግ ወታደር ምርኮኞች ላይ ዓለምአቀፍ የጦር ሕግን በመጣስ ዘግናኝ ጭፍጨፋ እንደፈጸመባቸው የሚታወቅ ጉዳይ ነው፡፡ ከጭፍጨፋ የተረፉትንም የገጠር መንገዶችንና የግብርና ሥራዎችን እያሠራ እስከዛሬም ድረስ በግዞት ይዟቸው ያሉ እንዳሉ ይሄም ይታወቃል፡፡
እነኝህ ሁሉ ሸአቢያ በአማራና በሀገሪቱ ላይ የፈጸማቸው እጅግ ከባባድ የጦር ወንጀሎች ከይቅርታ አቅም በላይ ቢሆኑም ሸአቢያ በይፋ ይቅርታ ሊጠይቅባቸው የሚገቡና በፍጹም በፍጹም ተድበስብሰው ሊታለፉ የማይገቡ የግፍ ተግባሮች ናቸው፡፡
በመሆኑም አቶ ኢሳይያስ ከዚህ ኩነኔያቸው ጋር ወደ መቃብር መውረድ ካልፈለጉና መተማመን ላይ የተመሠረተ ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር ከፈለጉ ለዚህ ሁሉ ግፍ ተንበርክከው ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባል፡፡ አቶ ኢሳይያስ ይሄንን ወርቃማ አጋጣሚ ለዚህ ወሳኝ ተግባር መጠቀም ካልቻሉና ካልፈለጉ በጣም የሚገርመኝ ነው የሚሆነው፡፡ የጉብኝቱ ዓላማም የሚገባኝ አይሆንም፡፡ ትርጉም አልባ ይሆናልና፡፡ ብቻም ሳይሆን አቶ ኢሳይያስ በዚህ ሁሉ ኩነኔያቸው ፈጽሞ እንዳልተጸጸቱና አሁንም ትኩረታቸው ኢፍትሐዊ ጥቅምን ከሀገራችን ለማግበስበስ የሚያልም ፍላጎትና ሐሳብ ላይ እንደተጠመዱና ይሄንን ፍላጎት ለማሳካት በማሰብ ብቻ የሚደረግ ጉብኝት መሆኑን ያረጋግጣል፡፡
ይሄ ፍላጎት ከባድ አደጋ አለው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ነውረኛ ጉብኝት ደግሞ ሕዝባችን አጥብቆ ማውገዝና መኮነን ይኖርበታል፡፡ አደራህን የጎንደርና የባሕርዳር ሕዝብ የበድኑን የቅጥረኛውን የብአዴንን ጥሪ ተቀብለህ ለደመኛህና ቀንደኛ ጠላትህ አቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ አቀባበል እንዳትወጣና በግፍ ሰለባ ወገኖችህ ደምና አጥንት ላይ ተሳልቀህ እንዳታዋርደን አደራየ ጥብቅ ነው፡፡
አቶ ኢሳይያስ ዝምድናችንን አስበው ይሄንን ዕድል ባያባክኑት መልካም ነው፡፡ ከዚህ ቀደም አቶ ኢሳይያስ ከኢሳት ጋር ቃለመጠይቅ ባደረጉበት ወቅት ያልኳቹህን ነገር ታስታውሳላቹህ? በዚያ ጽሑፍ ላይ ሐማሴኖች ጎንደሬዎች መሆናቸውን፣ ትግርኛቸው ለአማርኛ የቀረበ የሆነበት ምክንያትም ይሄ መሆኑን ገልጨላቹህ ነበር፡፡
ሐማሴኖች ስሞቻቸውን የጎንደር ነገሥታትን ስም እየወሰዱ ዓለም ሰገድ፣ አዲያም ሰገድ፣ ኢዮአስ፣ መሲሕ ሰገድ፣ ፋሲል፣ ቴዎድሮስ ወዘተረፈ. እያሉ ለራሳቸው ስም የሚያወጡበት ምክንያት የኋላ ታሪካቸውን ስለሚያውቁ መሆኑን ዐፄ ሠርፀድንግል ቱርኮች ምፅዋን በመውረራቸውና ሹማቸው የነበረው ባሕረነጋሽ ይስሐቅም ከድቷቸው ከቱርክ ወራሪ ጦር ጋር በመሰለፉ “ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት!” ብለው ከጎንደር ተነሥተው በመዝመት 1571ዓ.ም. እንቲጮ ላይ የከሐዲውን የባሕረ ነጋሽ ይስሐቅንና የቱርክን ጦር መደምሰሳቸውንና ሐማሴኖች ያን ጊዜ ለውጊያ ከጎንደር ዘምተው የነበሩና ለሀገር ጥበቃ እዚያው እንዲቀሩ የተደረጉ ጎንደሬዎች መሆናቸውንም ከዚህ ቀደም ጽፌ ነበረ፡፡
እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ እነኝህ ከጊዜ ብዛት ከሀገሬው ጋር ተዋልደው ተዋሕደው ትግሬነትን የተላበሱ ወገኖቻችን እዚያ እየቆዩ ሲሔዱ ከጣሊያን ያንን ምድር መርገጥ በኋላ የጣሊያንና የባሕሩ ጋኔን አደረባቸው መሰለኝ እነኛ ዘመዶቻችን የጥንት ጎንደሬዎቹ (ሐማሴኖችን ማለቴ ነው) የጎንደሬነት ወይም የአማራነት ማንነታቸውን በሚፃረር፣ በሚቃረንና በማይገልጽ መልኩ ፀረ ኢትዮጵያ ሆነው አረፉትና በፊት አውራሪነት በመታገል ባሕረ ምድርን (ኤርትራን) ገንጥለው አረፉት፡፡
ምን መገንጠል ብቻ ፈጽሞ የማይገባቸው እንደሆነ እያወቁ በአቶ መለስ ክህደት አሰብ ወደባችንን በስጦታ ሲሰጣቸው “ሀቃችን አይደለም አይገባንም!” ሳይሉ በመረከብ ሀገራችን የተቆለፈባት ምድር (Land locked) አድርገውብንም አረፉት እንጅ፡፡ ኧረ ምን ይሄ ብቻ ዋነኛ ፀረ አማራ የጥፋት ኃይል ሆነውም ቁጭ አሉ እንጅ፡፡ አያሳዝንም???
እነ አቶ ኢሳይያስ ግን እንዲያው እንደ ሰው ይሄ ሁሉ በደልና ግፍ ይታሰባቸው ይሆን??? ያውም እኮ ላይጠቀሙ እኮነው! ተገንጥለው አዩት በችጋር ከመማቀቅ በስተቀር ምን አገኙ??? ምንም!!! ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስስ አይለቅም እንዲሉ ይሄ ጋኔናቸው እንዲህ በቀላሉ የሚለቃቸው አይመስለኝምና ይሄ ሁሉ ግፍና በደል የሚሰማቸውና የሚጸጸቱ አይመስለኝም፡፡
በሉ እንግዲህ ወገኖቸ አደራ ያልኳቹህን ነገር አደራ እንዳትረሱ!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
Filed in: Amharic