>

ወደ ምስራቅ ተመልከቱ!!! (መስከረም አበራ)

ወደ ምስራቅ ተመልከቱ!!!
መስከረም አበራ
በህወሃት የእስር ግዛት በነበርንበት ዘመን ሁላችንም አሳር መከራ ውስጥ የነበርን ብንሆንም የሱማሌ ክልል አበሳ ግን ትንሽ ባስ ይል ነበር፡፡ አብዲ ኢሌ የሚባል እብድ መለስ የሚባል ሰይጣንን ተልዕኮ ተሸክሞ ህዝቡን አሳር መከራ ሲያሳይ ኖሯል፡፡
በተለይ ኢሳት በአንድ ወቅት ያሳየው ህዝቡን የዘመዱን ሬሳ የማሳፈስ አረመኔያዊ ሥራ ያየ ሰው “የሶማሌ ክልልን ህዝብ ፈጣሪ ያስበው!” ማለቱ አይቀርም፡፡ እንደተባለው ፈጣሪ  እነዚህን ሰዎች አስቧቸው ሙስጠፋ መሃመድ ዑመርን የመሰለ አስተዋይ መሪ አምጥቶላቸዋል፡፡
 ሙስጠፋ በተባበሩት መንግስታት ስር የሰራ ሰው ነው፡፡ ከአውስትራሊያው SBS ሬዲዮ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ እጅግ ወድጄዋለሁ፡፡ ምክንያታዊነቱ፣ ህልሙ፣የሃገራችንን ወቅታዊ ፖለቲካዊ መንፈስ የተረዳበት መንገድ እጅግ ግሩም ነው፡፡ ብስለቱ ደንቆኛል፤ርቱዕ አንደበቱ በጣም መሳጭ ነው፡፡
 በሶማሌ ክልል ያለውን ጎሰኝነት እና ምስቅልቅል ወደ ተጠናከረ የኢትዮጵያዊነት ማንነት ለማምጣት የሚቻለው በጉልበት እና በፕሮፖጋንዳ ሳይሆን ተጨባጭ ነገሮችን ብቻ በመስራት እንደሆነ አምኖ በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥሩ ስራዎችን እየሰራ ያለ ሰው ነው፡፡
የጎሳ ፖለቲካ ወዴትም እንደማያደርሰን በደንብ ተረድቷል፡፡ በአስተሳሰብ ተዋረድ ውስጥም ጎሰኝነት የመጨረሻው መሰላል ላይ እንደተቀመጠ በማራኪ መንገድ አስቀምጦታል፡፡ በኢትዮጵያ የዜግነት ፖለቲካ እና የመብትጥያቄ የጎሳ ፖለቲካን እና የተበድየ ተረክን ተክቶ እንዲበቅል ይመኛል፡፡
 ከ18ኛው ደቂቃ በኋላ ያስቀመጠው ነጥብ ወቅታዊ የኢትዮጵያ ችግር ከነመፍትሄው ቁልጭ አድረጎ ያስቀመጠ ፍልስፍና ሆኖ አግኝቸዋለሁ፤ ተገርሜያለሁም፡፡ እውነት ለመናገር ይህን ሰው ለሃገራዊ ቁንጮ ስልጣን ሳይቀር ለመመኘት ከጅሎኛል! ያሰበው እንዲሳካለት ምኞቴ ነው……
Filed in: Amharic