>
5:36 pm - Friday August 19, 2022

ስለ ዶክተር ዐቢይ መንግስት መናገር ያቆምኩት (አፈንዲ ሙተቂ)

ስለ ዶክተር ዐቢይ መንግስት መናገር ያቆምኩት
አፈንዲ ሙተቂ
ብዙዎች በውስጥ መስመር “ስለመንግስታችን መናገር አቁመሃል” ይሉኛል። አዎን! አቁሜአለሁ። አቁመናል። ምክንያቱም አፍ እንጂ ጆሮ ከሌለው መንግስት ጋር መዳረቅ ፋይዳ ስለሌለው ነው።
ይህ መንግስት እኛን አይሰማንም። ከእኛ በላይ ለእርሱ ቀረብ የሚሉት እነ ዶክተር ደረጄ ገረፋ ቱሉ የሚሰጡትንም ምክር አይሰማም። እስከ አሁን ድረስ በህዝብ ግንኙነት ስራ ብቻ ተጠምዷል። የሚሰራው በሙሉ በጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በፓርቲያቸው ዙሪያ personality cult ለመፍጠር ታልሞ የሚደረግ ነው የሚመስለው። እስቲ ተመልከቱት።
# አስር ሴት ሚኒስትሮች ተሾሙ። እልልልልል
# ሴት ፕሬዚዳንት ለመጀመሪያ ጊዜ ተመረጠች። እልልልልልል
# ሴት የፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ሆነች። እልልልልልል
# ሴት የኢንሳ ዳይሬክተር ሆነች። እልልልልልል
አሁንም ብርቱካን ሚደቅሳ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ልትሆን ነው ተብሏል። ባለፈው ሳምንት ለቀድሞው ፕሬዚዳንት መሸኛ ድል ያለ ድግስ ተደገሰና ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደለመዱት ጤፍ በሚቆላ ምላሳቸው የሰው ልብ ለመስረቅ ሞከሩ። ነገ ደግሞ ለኤርትራው ፕሬዚዳንት አቀባበል ልዩ ስርዓት በጎንደር ሲደረግ ከባልቴቶች እጅ ምሳቸውን ይጎርሱና በቲቪ ታይተው ይህንን ወፈ ሰማይ ህዝብ “አይ አቢይ! አይ እሱ እኮ! ሰው የማይንቅ! የሚተናሰስ!” ያሰኙት ይሆናል። ወይንም የአንዲት ቆሎ ሻጭ ልጅን ሽምብራ ዘግነው ይቀምሱትና “ፐ! ፐ! ፐ!” እንድንል ይጥሩ ይሆናል።
—-
እኔ የምለው! የዚህች ሀገር ችግር ይህ ነበር እንዴ? ከአንድ መሪ የሚጠበቀውስ የህዝብ ግንኙነት ስራዎች እንደዚህ እየደጋገሙ ሰውን ማሰልቸት ነው?
እኛ ተግባር ነው የጠየቅነው!!  Action! Action! Action! ሴቶች በህግ ስርዓቱ ከበድ ያለ ከለላ እንዲደረግላቸው ነው የሚፈለገው። ይህ ሳይፈፀም ዋና ዳኛዋ ሴት ስለሆነች ብቻ የሴቶች መደፈርን ማስቆም አይቻልም።
—–
ይህንን በምጽፍበት ሰዓት ሀገሪቷ በአራቱም አቅጣጫ በጸጥታ ችግር ተሰንጋ ተይዛለች። በቀበሌና በወረዳ ደረጃ ያሉት መዋቅሮች በሚያሳዝን ሁኔታ እየፈራረሱ ነው። ህገ ወጥ የመሬት ሽያጭ እየተመለሰ ነው ይባላል። የህግ የበላይነትን ማስፈንና ማስከበር አስቸጋሪ ሆኗል። የኮንትሮባንድ ንግድ ጦፎበታል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢኮኖሚው እየሾቀ ነው። የኑሮ ውድነቱ በአስፈሪ ደረጃ እየናረ ነው። ከዓለም ባንክና ከዐረብ አሚሬቶች ዶላር መጣ ቢባልም የተቀየረ ነገር የለም። Diaspora Trust Fund በተጨባጭ ምን እየሰራ እንደሆነ አልታወቀም። በሚገርም መልኩ መንግስት ዓመታዊውን ግብር በተገቢው መንገድ አልሰበሰበም (ግብር ሳይሰበስብ ግብር የሚያበላ መንግስት!)። በየወረዳው ውሃ የማይቋጥሩ ሰበቦች እየተፈለጉ አድማ ማድረግ ተጀምሯል። ክልሎችን የሚያገናኙ ትልልቅ ጎዳናዎች እየተዘጉ ነው። በየአካባቢው የሚካሄደው የብሄረሰብ ግጭት ተባብሶ ቀጥሏል።
——
እኔ ከቤተ መንግስት ውጭ በህዝቡ መሃል ስለምኖር የእነዚህን ችግሮች መንስኤና ውጤቶቻቸውን እያየሁ ነው። በመሆኑም መንግስት መንግስትነቱን ሳይረሳ ችግሮቹን በአፋጣኝ መፍታት ይጠበቅበታል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ ጥሪ እና አመራር መስጠት ብቻ ነው የሚጠበቅበት። ህዝቡ ለመንግስት አመኔታ የሰጠ በመሆኑ “ቶሎ ድረሱልኝና እርዱኝ” ተብሎ ቢጠየቅ ያለምንም ማመንታት እንደሚተባበረው እርግጠኛ ነኝ።
አዎን! ህዝቡ ቅሬታውን ችሎ ነው መንግስትን እየደገፈ ያለው። ይህንንም ያደረገው መከፋፈሉ ያልተጠበቀ አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ስለተገነዘበ ነው።
—–
ታዲያ በመንግስት መሠራት ያለባቸውና በህዝብ እየተጠየቁ ያሉት ከላይ የተጠቀሱት ነጥቦች ብቻ አይደለም። ህዝቡ የታገለላቸው ዋነኛ ጥያቄዎች አስቸኳይ የስትራቴጂ ፕላን ተሰርቶላቸው መመለስ ያለባቸው ናቸው። እነዚህ ጥያቄዎች ካልተመለሱ የምንመኘው ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው እውን ሊሆን አይችልም። እስቲ ዛሬም እንደፈረደብኝ ልድገማቸው።
 ወዳጆች!
እስከ አሁኗ ደቂቃ ድረስ መንግስትና ፓርቲ አንድ ላይ በተቆላለፉበት ሀገር ውስጥ ነው ያለነው። እስከ አሁን ድረስ በኢህአዴግ እና በመንግስት መካከል ትክክለኛ መስመር አልተሰመረም። ሪፎርሙ ሐቀኛ መሆኑን በሙሉ ልባችን እንድንመሰክርላችሁ ካሻችሁ የፓርቲ ስራን ከመንግስት ስራ መለየት አለባችሁ። ምሳሌ እንስጣችሁ!!
# በኦሮሚያ ክልል እየተደጋገመ የሚነገር አንድ አስገራሚ ስልጣን አለ። ይህም “በምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ የድርጅት ጽ/ቤት ኃላፊ” የሚል ነው። ምን አይነት ቀልድ ነው? የድርጅቱ ጽ/ቤት ኃላፊ ሆኖ ለተሾመ ሰው የምክትል ፕሬዚዳንት ማዕረግ ሲሰጥ አይተንም ሰምተንም አናውቅም። ይህ በአስቸኳይ መታረም አለበት።
# የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ያካሄዱት ጉባኤ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በቀጥታ ሲተላለፍ ነበር። ኢህአዴግ በአዋሳ ያካሄደው ጉባኤም በቀጥታ ተላልፏል። ፓርቲዎቹ ይህንን ያደረጉት ለኢቲቪ ከፍለው ነው? ካልከፈሉ ህገ ወጥ ስራ ሰርተዋል። በህገ መንግስቱ መሠረት ኢቴቪ ሳይከፈለው የገዥውን ፓርቲ ጉባኤ ብቻ በቀጥታ ማስተላለፍ የለበትም። የገዠውን ፓርቲ ጉባኤ ካስተላለፈ ደግሞ የተቃዋሚ ፓርቲ ጉባኤዎችንም በቀጥታ የማስተላለፍ ግዴታ አለበት። ኢህአዴግ ጉባኤውን በቀጥታ ማስተላለፍ የሚችለው የራሱ ንብረት በሆኑት ዋልታ እና ፋና ቲቪ ነው እንጂ የሁላችንም ንብረት በሆነው ኢቲቪ አይደለም (ለክልል ጣቢያዎችም ቢሆን አሰራሩ ተመሳሳይ ነው)።
# በየትኛውም የሀገራችን ክልል ባሉት ወረዳዎች ከዞራችሁ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች እንደ ቢሮ የሚገለገሉባቸው ጽህፈት ቤቶች ከየወረዳዎቹ የአስተዳደር ጽ/ቤቶች ጋር በአንድ ግቢ ውስጥ የሚገኙ ሆነው ነው የምታዩዋቸው። ይህ ስህተት ብቻ ሳይሆን ህገ ወጥም ነው። ዲሞክራሲን እናራምዳለን በሚሉ ሀገሮች ውስጥ እንዲህ ዓይነት አሰራር በጭራሽ የለም።
እነዚህን ለመሳሰሉትና ከዲሞክራሲ መርህ ጋር ለሚጋጩት አሰራሮች ትኩረት ሳይሰጡ ሚኒስትሮችን መቀያየርና ሴቶችን በዛ አድርጎ መሾም ከፕሮፓጋንዳ ፍጆታ በስተቀር ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታው ጠቀሜታ የለውም።
—–
ለማጠቃለል ያህል የዶ/ር ዐብይ መንግስት የጀመረው ለውጥ ስር ሰዶ የምንሻውን ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እውን የማድረግ ቁርጠኝነቱ ካለው በመዋቅራዊ ጉዳዮች እና በዲሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ ላይ ማተኮር አለበት። ስለዚህ
# ፓርቲና መንግስት ይለያዩ!
# ፍርድ ቤቶች ከመንግስትና ከፓርቲ ቁጥጥርና ጣልቃ ገብነት ሙሉ በሙሉ ነፃ ይሁኑ!
# የፀረ ሽብር ህግን የመሳሰሉ አፋኝ ህጎች በቶሎ ይሻሩ!
# የመደራጀት ነፃነት ሙሉ በሙሉ ይረጋገጥ!
# ምርጫ ቦርድ ሙሉ በሙሉ ነፃ ይሁን! አደረጃጀቱም ዘመናዊ ይሁን!
# ሚዲያዎች ከፓርቲ ታማኝነት የፀዱ ይሁኑ!
# ከፓርቲ ቁጥጥር ነፃ የሆነ እምባ ጠባቂ ተቋም ይቋቋም!
# የነፃ ፕሬስ አዋጅ ይከለስ! በፕሬሶች ላይ የተቆለሉ ማነቆዎች ይነሱ!
# ከፓርቲ ጣልቃ ገብነት የፀዱ የሙያ ማኅበራት እንዲደራጁ ይፈቀድ!
—-
እኔ አቢይን የምደግፈው ለውጥና ተሐድሶው ለሀገሬ ጥሩ ነገር ያመጣል በሚል ነው። በተረፈ የዶ/ር አቢይና የኦቦ ለማ ፓርቲ የሆነው የኦዴፓ የፖለቲካ ፕሮግራም ደጋፊ አይደለሁም። አንዳንድ የኦዴፓ ካድሬዎች ታዲያ ከኦዴፓ የተለየ አቋም የሚያራምድ ሰው ሲገጥማቸው እንደ ጠላት የሚፈርጁበት አሰራር አላቸው። ይህ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት የሚጎዳ ነገር ነው። ስለዚህ ዶ/ር አቢይና ኦቦ ለማ ካድሬዎቻቸውን እንዲያሳርፉልን እንጠይቃቸዋለን።
Filed in: Amharic