>
10:27 pm - Tuesday August 16, 2022

የዶ/ር አብይ ጥርስ እየተሳለ ነው -  አድፍጦ መገዝገዝ ጀምሯል!!! (መሳይ መኮንን)

የዶ/ር አብይ ጥርስ እየተሳለ ነው –  አድፍጦ መገዝገዝ ጀምሯል!!!
መሳይ መኮንን
 
* ከህዝብ ልብ መግባት አቅቶት በቴሌቪዥን፣ በመከላከያና በደህንንነቱ እየተደገፈ ከቤተ-መንግስት የቆየው የህወሀት አገዛዝ የመጨረሻ መሸሸጊያዬ ያላት የመቀሌዋም ጉድጓድ እየተደፈነችበት ይገኛል!
 
የኢሳትና የሪፖርተር ዜናዎች አንዳች ነገር አመልካች ናቸው። በኢሳት የትላንት መረጃ መሰረት ከ160 በላይ ጄነራሎችና የጦር አዛዦች በጠ/ሚር አብይ ትዕዛዝ ከሰራዊቱ እንዲሰናበቱ ተደርገዋል። አብዛኞቹ የህወሀት ጄነራሎች ናቸው። ዛሬ ደግሞ ሪፖርተር ጋዜጣ ከ40 በላይ የሜቴክና የደህንነት አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የሚያትት ዜና ይዞ ወጥቷል።
 የጠ/ሚር አብይ ጥርስ እየተሳለ ነው።  አድፍጦ መገዝገዝ ጀምሯል። የህወሀትን የጥፋት እጆች ከየክልሉ በመቁረጥ የቀጠለው ህወሀትን የማፈራረስ እርምጃ ወደ ጡዘቱ የደረሰ መስሏል። መቀሌ የመሸጉት፡ ከአክሱም ሆቴል ውስኪ እየላፉ፡ ለህግ የበላይነት እጅ አንሰጥም ያሉት የህወሀት ባለሟሎች ቀን እየጨለመባቸው ስለመሆኑ የሚያረጋግጡ ምልክቶችን እያየን ነው።
የኢትዮጵያ ፖለቲካ ነጭና ጥቁር ሆኖ ሽግግሩን ተያይዞታል። ተስፋና ጽልመትን እያስተናገደ ነው። ጥላቻ የሚሰብኩ ከወዲህ፡ በፍቅር የሚያንበረክኩ ከወዲያ ሆነው በእኩል ድምጻቸው የሚሰማባት ሀገር ሆናለች ኢትዮጵያ። ነገን በብርሃን የሚመለከተው በአንድ ወገን ቆሟል፡ የሚሟረተውና ጨለማው ብቻ የሚታየውም መዳፉን በጉንጩ ላይ አድርጎ ነጋ ጠባ መርዶ ይናገራል። አንድነትን የሚዘምሩ በርክተዋል። ጎጥና ክልል የሚናፍቁትም በለስ ቀናን ብለው ጮቤ እየረገጡ ነው። ትንንሽ ጥያቄዎች አደባባይ አመጽ የሚያስነሱም መሆናቸውን እየታዘብን ነው። በምስራቁ በር ተገኘ የተባለው የጅምላ መቃብር ደግሞ ገና ያልተነካ፡ የልተገለጸ በደል አርግዘን እንዳለን የሚያሳብቅ ሆኗል። ብቻ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉራማይሌ መስሏል። ዥንጉርጉር።
ለእኔ ከጽልመቱ ይልቅ ተስፋው ቀልቤን ገዝቶታል። ችግሩን ስለለመድነው፡ ግጭቱን ስለኖርንበት የተለየ ቦታ የምሰጠው አልሆነም። ደግሞም ሽግግር ወቅት ላይ ነጻ አውጪው፡ አርበኛውና ፋኖው ስለሚበዛ እንዲህ ዓይነቱ ትኩሳት የሚጠበቅ ነው። ክህወሀት የጎሳ ፖለቲካ ሀንጎቨር ጋር መላቀቅ ያቃታቸው የመንደር ፖለቲከኞች ይህቺ ጊዜ አታምልጠን ብለው የህዝብን ስሜት በመቀየር የፖለቲካውን የአየር በአየር ንግድ ለማጧጧፍ እያሟሟቁ እንዳለ እየሰማን ነው። ቀድመው የጀመሩትም በአንዳንድ አከባቢዎች ከተከሰቱ ግርግሮች ጀርባ ቆመው ትርፋቸውን በማስላቱ ላይ ተጠምደው እያየን ነው። የማይሰማ መንግስት በነበረ ጊዜ ለአመጽ ቀርቶ ለአቅመ ስብሰባ ያልበቁ ትንንሽ ጥያቄዎች ዘንድሮ ህዝባዊነት ካባ እንዲለብሱ እየተደረጉ የጎዳና ላይ አመጽ ፈጥረዋል። የሚሰማ መሪ ቤተመንግስት በገባ ጊዜ አመጹ የበረከተበት ምክንያት ግራ ያጋባል።
ጠ/ሚር አብይ አህመድ ከሰሞኑ እየወሰዷቸው ያሉት እርምጃዎች የመንግስታቸውን ቁመና እያሳመረው እንዲሄድ አድርጎታል። ቀደም ብለው በደህንነት መስሪያ ቤቱ ውስጥ ያለውን የህውሀት የበላይነት መስበር የቻሉት ጠ/ሚሩ ወደ መከላከያው ፊታቸውን አዙረው ስር ነቀል ለውጥ ጀምረዋል። ከህዝብ ልብ መግባት ያቃተውና፡ በቴሌቪዝን፡ በመከላከያና በደህንንነቱ እየተደገፈ ከቤተመንግስት የቆየው የህወሀት አገዛዝ የመጨረሻው መደበቂያው እየተደፈነበት ይገኛል። በቅርቡ የተሞከረው መፈንቅለ መንግስት ለዶ/ር አብይ እርምጃ መፍጠን አስተዋጽኦ አድርጓል። ህወሀትና ኦነግ ጥምረት የፈጠሩባቸው የሁለት ጊዜያት የግድያ ሙከራዎች ዶ/ር አብይ በአፋጣኝ ደህንነቱንና መከላከያ ውስጥ የተከመረውን ቆሻሻ እንዲያስወገዱ ገፋፍቶአቸዋል።
ባለፉት ሁለት ቀናት በመከላከያ ውስጥ የተወሰደው እርምጃ የለውጥ ሂደቱ ከተጀመረ ወዲህ ካየናቸውና ከሰማናቸው አጀብ ካሰኙን የዶ/ር አብይ ውሳኔዎች አንዱና ዋናው ነው ማለት ይቻላል። እሳቸውም የመከላከያ አዛዦችን ሰብስበው በተናገሩ ጊዜ ያሉት ይሄንኑ ነው። ”በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጡ ከመጣበት ካለፉት 7 ወራት ወዲህ ትርጉም ያለውና መሬት የረገጠ ስራ የተሰራው በሃገር መከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ ነው” ብለዋል ጠ/ሚሩ።
ልክም ናቸው። አቅም ያለው መከላከያ ውስጥ ነው። ሰራዊቱን ያልያዘ መንግስት የቱን ያህል ህዝባዊ ተቀባይነት ቢኖረውም እንደጸጉራም በግ ውጭው እያማረ ከውስጥ እየሞተ ሊመጣ የሚችል አይነት ነው። ህወሀት በዘርና ጎሳ ያዋቀረውና በፍጹም የበላይነት ቀፍድዶ የያዘውን መከላከያ መቆጣጠር ደግሞ የድሎች ሁሉ ድል ነው ማለት ይቻላል። ከመነሻው ስጋቴ የነበረው መከላከያን ከህወሀት እጅ ፈልቅቆ ለመውሰድ የጠ/ሚር አብይ መንግስት እንዴት ይቻለዋል? የሚል ነበር። አሁን የማየው ስጋቴን የሚቀርፍ ነው።
በመከላከያው ላይ የተወሰደው እርምጃ ህውሀት ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ መረዳት የሚቻል ነው። መከላከያው የበላይ አመራሩ በአንድ መንደር ልጆች የተያዘ ሆኖ ቆይቷል። ሰባቱም የመከላከያ ስታፍ መምሪይያዎች በህወሀት ሰዎች የተያዘበት፡ ኤታ ማዦር ሹምነቱን በርስትነት የተቆጣጠሩበት፡ ቁልፍ የሆኑ የመከላከያ መዋቅሮችን የትግራይ ተወላጆች ብቻ እንዲይዙት ከፈጣሪ ጭምር ትዕዛዝ የተሰጠ እስኪመስል የደረሰበትን ታሪክ ጠ/ሚር አብይ ግልብጠውት አረፉት።
 ከ160 በላይ ጄነራሎችና የጦር አዛዦች የተሰናበቱበት የሰሞኑ እርምጃቸው በዋናነት ይሄንኑ የህወሀትን የበላይነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማጥፋት መሆኑን የውስጥ የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል።  ከክፍለጦር አዛዥነት እስከ እዝ ኣዛዥነት በአንድ ስፍራ ከአንድ በላይ የተመሳሳይ ብሔረሰብ ተወላጆች እንዳይኖሩ ተደርጓል ብለዋል ጠ/ሚሩ። ይህ እንግዲህ ጠ/ሚር አብይ የህግ የበላይነትን አሰፍናለሁ ብለው በተደጋጋሚ ለሚገቡት ቃል ማስፈጸሚያ የሚሆናቸው ትልቅ አቅም የሚፈጥር እርምጃ ነው።
በሪፖርተር ዘገባ መሰረት ደግሞ ከ40 በላይ የሜቴክና የደህህነት አባላት ታስረዋል። የ160 ጄነራሎች መሰናበትን ተከትሎ ይህ ዜና መሰማቱ የነገሮችን ፍጥነት አስደማሚ ያደርገዋል። የኢሳት ምንጮች ከሰሞኑ ቱባ ወታደራዊና ሲቪል ባልስልጣናት ከርቸሌ ሊገቡ እንደሚችሉ ፍንጭ ነግረውን ነበር። የሪፖርተር መረጃ የምንጮቻችን ጥቆማ የሚያጠናክር ይመስላል። እነዚህ 40ዎቹ የሜቴክና የደህንነት ሰዎች እነማን እንደሆኑ ባይታወቅም ህወሀቶች መሆናቸውን ግን ከጥርጣሬም በላይ መገመት ይቻላል።
ሜቴክ በአቶ መለስ ዜናዊ አማካኝነት ለህወሀት ጄነራሎች ጡረታ መደጎሚያ ተብሎ የተመሰረተ፡ የኢትዮጵያን ሀብት በቁም በመጋጥ የደለበ የግፍ ተቋም ነው። ይህ ተቋም በይፋ ፈርሶ አይን ያወጣ ዘረፋ ላይ የተሰማሩ የህወሀት ጄነራሎች በህግ ሊጠየቁ ይገባል የሚል የህዝብ ድምጽ አለ። ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ጄነራል ክንፈ ዳኘው እስርን ፍራቻ ከመቀሌ መውጣት አልቻሉም። እንግዲህ ገርጂ ላይ በስብሰባ ላይ እንዳሉ ተለቅመው የታሰሩት የሜቴክ ሰዎች እነማን እንደሆኑ ከሰሞኑ እንሰማለን። ብ/ጄነራል ክንፈ ዳኘው ባይኖሩበት እንኳን እርምጃው የእሳቸውም መጨረሻ ሌላውን ሲያሰቃዩ ከነበረበት የቃሊቲ እስር ቤት ሊሆን እንደሚችል ያመላከተ እርምጃ ነው።
የዶ/ር አብይ አመራር ጥርስ ካወጣ አይቀር ሶማሌ ክልልን የሚያምሱትን የህወሀት ሁለቱን ጄነራሎችንም አደብ ማስገዛት አለበት። ከሶማሌላንድ እስከ ደቡብ ሱዳን ጁባ የተዘረጋውን የኮንትሮባንድ ንግድ የሚቆጣጠሩት ጄነራል አበረሃም ወልደማርያም ኳርተርና ጄነራል ገብሬ ዲላ ሰሞኑን የጥፋት እጃቸውን ዘርግተዋል። ጂግጂጋን ውጠረት ውስጥ ከከተታት ያለፈው ሳምንት ግጭት ጀርባ እነዚህ ሁለቱ የህውሀት ጄነራሎች እንደሚገኙ የሶማሌ ክልሉ ፕሬዝዳንት ነግረውናል። ታዲያ በህውሀት የንግስና ዘመን እንዳሻቸው ሲፈነጩ ለነበሩት ለእነዚህ ነጋዴ ጄነራሎች ዘንድሮም የማርያም መንገድ ተሰጥቷቸው በደም የደለበ ንግዳቸውን እንዲቀጥሉበት መደረጉ ተገቢ አይደለም። ማሰር ባይቻል ከጥፋት መንገዳቸው ማስቆም ግን ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አይደለም።
በተረፈ ተስፋው ደምቆ ይታየኛል። ሊነጋ ሲል ጨለማው እንደሚበረታ፡ በሽታ ሊለቅ ሲል ህመሙ እንደሚጸና ሁሉ ኢትዮጵያን የተጣቧት ችግሮች ሊፋቷት በዋዜማው ላይ በመሆናቸው አቅማቸው የፈረጠመ መስሏል። ግን ጊዜያዊ ናቸው። የዶ/ር አብይ መንግስት በመከላከያው ላይ የጀመረውን ስር ነቀል ለውጥ ካጠናቀቀ በኋላ ነገሮች መልክ መያዛቸው አይቀርም።
ቸር ወሬ እንደሰማን ለከርሞውም እንደዚያው ያዝልቀን!
Filed in: Amharic