>
5:13 pm - Thursday April 19, 3184

የእስር ውሳኔው ጥሩ ነው! ያም ሆኖ "ስጋት አለኝ"  (ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና)

የእስር ውሳኔው ጥሩ ነው! ያም ሆኖ “ስጋት አለኝ”
ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና
በእጸገነት አክሊሉ/አዲስ ዘመን ጋዜጣ፤ ህዳር 4 ቀን 2011 ዓም
ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና የመንግስትን የእስር ውሳኔና የጠቅላይ ዐቃቤ ህግን መግለጫ በተመለከተ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ በሰጡት አስተያየት ፤‹‹እርምጃው ጥሩ ነው፤ ሁላችንም ስንታገልለት የነበረ ነው›› ብለዋል።
ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና ፣ ‹‹የእኔ ስጋት ትላልቅ አሳዎቹ ይኑሩበት አይኑሩበት እርግጠኛ መሆን አልቻልኩም ፤ እንደ አስፈላጊ እርምጃ ግን በጥሩ ጎኑ የሚታይ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት እርምጃ አብዛኛውን ጊዜ ትኩረቱን የሚያደርገው ትናንሽ አሳዎች ላይ ነው የሚሉት ፕሮፌሰሩ፣ ‹‹ስለ ትልልቆቹ አሳዎች መረጃ ላይኖረኝ ይችላል፤ አልያም በሌላ ምክንያት ይታለፋሉ። አሁንም ይህ ሥራ እንደዚህ ላለመሆኑ እርግጠኛ ባንሆንም እርምጃው ግን በጣም የሚያስደስት ነው ሲሉ ያብራራሉ።
ፕሮፌሰር መራራ ጉዳዩ መነካካቱ ጥሩ መሆኑን ጠቅሰው፣ የአንድ ሰሞን ግርግር እንዳይሆን ግን ስጋቱ አለኝ ይላሉ፡፡መንግሥት የአንድ ሰሞን የግርግር በሽታን ትቶ ውጤታማ የፍትህ ስርዓት በዳይን የሚቀጣ ተበዳይን የሚክስ አካሄድ መከተል እንደሚጠበቅበት አስታውቀዋል፡፡
እንደ ፕሮፌሰር መራራ ማብራሪያ፤ ሰዎችን በማሰርና ለህግ በማቅረብ ብቻ የማንወጣቸው በርካታ ችግሮች ስላሉ ፣መንግሥት ብሔራዊ መግባባት ላይ ሰርቶ ተጠያቂነት ያለው አሰራርን ማስፈን ይገባዋል። ይህ ሲሆን ህዝቡም ሌብነትን መቆጣጠር ይቻለዋል፤ በመሆኑም በዚህ ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ይገባል።
Filed in: Amharic