>
7:10 am - Tuesday December 6, 2022

"የእነዚህ አቤቱታ አትስሟቸው" ባይዋ ካድሬ አቤቱታ ማቅረቧን ሰማሁ!  (ጌታቸው ሽፈራው)

“የእነዚህ አቤቱታ አትስሟቸው” ባይዋ ካድሬ አቤቱታ ማቅረቧን ሰማሁ! 
ጌታቸው ሽፈራው
* የትህነግ/ህወሓትን ስም አንስተን ስንተች  ሰማይ የተገለበጠ የሚመስላት ሴት ዛሬ የትህነግ ፀሀይ መጥለቋን ስታይ ምን ተሰምቷት ይሆን?
ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ “የሽብር ወንጀል” ምርመራ ከሚደረግባቸው ቢሮዎች አንዱ  ቁ 27 ነው። በዚህ ቢሮ በአብዛኛው ምርመራ የሚደረገው በአርበኞች ግንቦት 7 የተጠረጠረ ሰው ሲሆን አልፎ አልፎ በኦነግ የተጠረጠረም  ይመረመርበታል። በዚህ ምርመራ ቢሮ ውስጥ በርከት ያሉ መርማሪዎች የነበሩ ሲሆን ኃላፊያቸው እቴነሽ አረፈአይኔ የተባለች የትህነግ/ህወሓት ቀንደኛ ካድሬ  ነበረች። በምርመራ ወቅት ስለ ህወሓት አምባገነንነት ሲነገር እንደ እብድ ያደርጋታል።
እቴነሽ በተለይ ከክፍለ ሀገር የሚመጡ  ወጣቶችን ታሰቃይ ነበር። በሴትነቷ አማልላ በጓደኞቹ ላይ ያስመሰከረችው ወጣት ነበር። በዚሁ እርኩስ ፀባዩዋ ምክንያት አባብላው እንቅልፍ የሚያጣ ሰው ነበር። በተመሳሳይ እንደሚፈታ ነግራው፣ በተለመደው ርክስናዋ አባብላው የተከሰሰ ወጣት ነበር። ወጣቱ የአካል ጉዳት ስለነበረበት ይህ ጉዳቱ እንደሚያሳስባት፣ ለልጁ መድረስ እንዳለበት በመግለፅ እንደምትፈታው እየነገረችው  የምትሰራውን ሰራችበት።  በመጨረሻም አስከሰሰችው። እቴነሽ  የወጣላት አረመኔ ነች። ጥላቻዋ አይጣል ነው። በአማራና ኦሮሞ ሕዝብ ላይ ጥላቻ ከነገሰባቸው መርማሪዎች መካከል አንዷ ናት።
ከዚህ አለፍ ሲል እቴነሽ ወንድ ላይ እንደምትሸና  ብዘዎች ይናገራሉ። ዛሬ እሷም ለዛ እስር ቤት ታሳሪ ነች።  በፈፀመችው የሰብአዊ መብት ጥሰት ለእስር ተዳርጋለች። ፍርድ ቤት ቀርባ አቤቱታ ማቅረቧንም ሰማሁ። ያች ሰውን እንደሰው የማትቆጥር አረመኔ “የ6 ወር ህፃን አለኝ” ብላ አቤቱታ ማቅረቧን ሰማሁ። እውነቷን ከሆነ ህፃኑ ያሳዝናል። ከምንም ከእሷ መፈጠሩ ያሳዝናል።
 ማዕከላዊ የታሰረ አንድ ወታደር ነበር።  በመጠኑም ቢሆን ማንበብ መፃፍ የሚችል ቢሆንም “ማንበብ መፃፍ አልችልም” ብሎ ይክዳል። ቢቀጠቅጡት ሊያምንላቸው አልቻለም። በመጀመርያዎቹ የምርመራ ጊዜያት የቅርብ ቤተሰብ ከተፈቀደለት መጠየቅ የሚችለው በቢሮ በኩል ነው። አንድ ቀን የወታደሩ እህት እንድትጠይቀው  ይፈቀድላታል። ወንድሟን ልትጠይቅ ሄዳ የገጠማት ግን የሚያሳዝን ነው።  መርማሪቹ የወታደሩ እህት እያለች ምርመራ ጀመሩ። እሱ “አነባለሁ። እፅፋለሁ” እንዲላቸው እህቱን በጥፊ መቷት። ወለል ላይ ወደቀች። ከዛ በኋላ ወደማዕከላዊ ቀርቶ ቂሊንጦ መጥታ ጠይቃው አታውቅም።
 ይህን የመሰለና ከዚህ የባሰ ጭካኔ የሚሰሩት እነ እቴነሽ ዛሬ ለእስር ተዳርገው አቤቱታ ሲያቀርቡ ይገርማል። ጊዜ ደግ ነው ማለት ይሻላል።    ፍርድ ቤት በድፍረት አቤቱታ የምናቀርብን ሰዎች የሚያዩበት ሁኔታ የሚገርም ነበር። ጓደኞቻችን ጠርተው “እነዛን አትስሟቸው” እያሉ ጣት ይቀስሩ የነበሩ ሰዎች ዛሬ አቤቱታ ማቅረቢያ ሰዓቱ የእነሱ ሆኗል። የትህነግ/ህወሓትን ስም አንስተን ስንተች  ሰማይ የተገለበጠ የሚመስላት ሴት ዛሬ የትህነግ ፀሀይ ስትከለል ምን ይሰማት ይሆን?
Filed in: Amharic