>

የተፈረደብን ቀን!!! (ውብሸት ታዬ)

የተፈረደብን ቀን!!!
ውብሸት ታዬ
የያዙን፣ የመረመሩን፣ የከሰሱንና የፈረዱብን ሰዎች ለመስማት በሚሰቀጥጡ ወንጀሎች ‘ተጠርጥረው’ በሕግ ቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው። ፍርድ የእግዚአብሔር ነው፤ ሕዝብም ይፈርዳል።
  ያሳለፍናቸው የእስር ጊዜዎችም በእጅጉ ከባድ ነበሩ። ሂሩት ክፍሌ አንደኛዋ አባርያችን ናት። በተፈታች በዓመት ከመንፈቋ ከእኛ ጋር ዳግም በመታሰሯ ቃሊቲ የገባን ቀን “መጨረሻሽ እዚሁ እንዲሆን ካልፈለግሽ አድበሽ ተቀመጭ” ተብላ ነበር። የተፈረደብን ቀን ለዳኞቹ እንዲህ አለች፦ “ይህ የሰው ፍርድ ነው፤ የእግዚአብሔርን እናያለን!”
ዘሪሁን ገ/እ/ር ሁለተኛው አባርያችን ነው። በተቃውሞ ፖለቲካው አቅሙ የፈቀደውን ሲያደርግ ቆይቷል። በእስር ቆይታው ‘አሻፈረኝ’ ባይነቱ ተጨምሮ ያልደረሰበት እንግልት አልነበረም። የተፈረደብን ቀን ለዳኞቹ እንዲህ አለ፦ “እውነት ታሸንፋለች!”
   ጋዜጠኛና መምህርት ርዕዮት ዓለሙ እንደፍትሕ ባሉ ሞጋች ጋዜጦች ላይ   በተባ ብዕሯ በምትጽፋቸው አንጀት አርስ(ለእነሱ አንጀት አጭስ)ጽሑፎቿ ነበር ለእስር የበቃችው። የተፈረደብን ቀን ለዳኞቹ እንዲህ አለች፦ “በአቋሜ ጸንቼ እቀጥላለሁ!” ቃሊቲ ደርሰን ስንለያይ ያለችውም አይረሳኝም። “አይዟችሁ ውቤ፤ የፈረዱት በራሳቸው ላይ ነው!” ያችን ጀግና እስከዛሬ በአካል አላገኘኋትም።
 ቅዱሱ መጽሐፍ “አትፍረዱ ይፈረድባችኋል” ይላል። እንግዲህ ፍትሕ ይበየን። ያለ አግባብ የሆነብን ሁሉ ይሁንባቸው አልልም። አያስፈልግም፤ አይጠቅምም። ለዚህ ያበቃን እግዚአብሔር ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብም ከጎናችን ነበር። እነሱስ የሚፈረድባቸው ቀን ለዳኞቹ ምን ይሉ ይሆን? ኑሩልን! Nuu jiraadha !
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ያስብ፤ ሕዝቧን ይባርክ!
Filed in: Amharic