>
5:13 pm - Saturday April 20, 0469

እባክህ የእኔ ወንድም ላስቸግርህ? (በፍቃዱ ሞረዳ)

እባክህ የእኔ ወንድም ላስቸግርህ?
በፍቃዱ ሞረዳ
ከዛሬ አሥራ አምስት ዓመት በፊት በሸገር ዉስጥ 18 ድብቅ እስር ቤቶች መኖራቸዉን ( ከእነቦታቸዉ ጭምር)፣ አምቡላንሶች ለአፈና ተግባር እየዋሉ መሆናቸዉን የፃፍንፍበትን ጦማር ጋዜጣ ከወመዘክርም ቢሆን ፈልገህ ከአቶ ብርሃኑ ፀጋዬ ቢሮ ታደርስልኝ? ወረታህን ስመጣ እከፍልሃለሁ፡፡
    ከቻልክም አሰፋ ማሩን ስለገደለዉ የመከላከያ ደህንነቱ ሰዉዬ ( ታጋይ መኮንን-በኋላም የመሬት ደላላ ስለሆነዉ)፣ ወንድሜን ተስፋዬ ታደሰን ስለገደሉት አረመኔዎች፣ ወንድሜን ኤቢሣ አዱኛን በአሰቃቂ ሁኔታ ስለገደሉት የመከላከያ ሽፍቶች ጉዳይ ትንሽ ማስታወሻ ጥለህልኝ ዉጣ፡፡
  ቦታና ሁኔታ ምቹ ከሆነም ‹‹ ባለፉት ሃያ ምንምን ዓመታት በሀገርና በዜጎች ላይ ለተፈፀመዉ በደልና ወንጀል ፣የተወሰኑ ግለሰቦችን የጦስ ዶሮ አድርጎ መስዋዕት በማቅረብ ማለፍ ሳይሆን፣ ‹‹ኢሕአዴግ›› የተሰኘዉ የወንጀል ቡድን እንደ ድርጅት ለፍርድ የሚቀርብበት ጊዜ መቼ እንደሆነም ጠይቅልኝ፡፡ ይህንን የመጨረሻ ጥያቄ ስታቀርብ ግን በትዕብትና በጀብዱ ከሆነ ሥራህ ያዉጣህ፡፡ ከአሥራ ስምንቱ ድብቅ እስር ቤቶች የተጋለጡት ሰባቱ ብቻ ናቸዉ፡፡
ሁለቱን እኔም ቀምሻቸዋለሁ፡፡ ፈረንሳይ ለጋሲዮን ራስ አሥራተ ካሳ ግቢ የነበረዉን አራት ኪሎ ዶርዜ ሃይዞ ፊት ለፊት ከላይ ከቅድስተማሪያም መጥቶ ወደፒያሳ በሚታጠፈዉ መንገድ ቀኝ ላይ ባለዉ ሕንፃ ዉስጥ የነበረዉን፡፡ ኡራዔል መስቀለኛዉ መንገድ ላይ ያለዉን ሟቹ ጓደኛዬ ተገርፎበታል፡፡ ባምቢስ ባለዉ የደህንነት ግቢ ዉስጥ ያለዉ ቤርሙዳ ሳንረሳ፡፡
እንግዲህ ሰባቱ ከተነገሩህ የተቀረዉ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል እንዳለ እንዲቆይ መደረጉን ማንም ሊነግርህ ስለማይችል አፍህን አታበላሽ፡፡
 ችግር ከደረሰብህ ግን ዘመድ ያሳዉቀኝ፡፡ ዋሽንግተን ሄጄ ዋይት ሀዉስ ፊት ለፊት ፣‹‹ Shame on you Abiy Ahmed!! ›› እንድል፡፡
Filed in: Amharic