>

የፌዴራል ዓቃቢ ህግ መግለጫ ለምን ግርምትን ፈጠረብን? (ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ)

የፌዴራል ዓቃቢ ህግ መግለጫ ለምን ግርምትን ፈጠረብን?

ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ

ኮተቤ ሜትሮፖሊን ዩኒቨርስቲ

 

የፌዴራል ዓቃቢ ህግ አቶ ብርሀኑ ፀጋየ ህዳር 03/2011 ዓ.ም የሰጡትን መግለጫ ተከትሎ በርካታ ግርምትን ከብዙ ኢትዮጵያውያን በመስማቴ ተገረምሁ፡፡ አቶ ብርሀኑ ፀጋየ የዘረዘሩትን የወንጀል ድርጊቶች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ስለ ኢትዮጵያ ሲጮሁ ለነበሩ ዜጎች   እንግዳ አልነበረም፡፡

ለበርካታ ዓመታት ታማኝ የሆኑ፣ አለማቀፋዊ ተሰሚነት ያላቸው፣ ገለልተኛ ተsማት ሲዘግቡት የነበረ ክስተት ነው፡፡ ሂውማን ራይትስ ዎች፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ፣ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ  እና ሌሎችም ተsማት ሲጮሁበት የነበረ አሳዛኝ ታሪካችን ነው፡፡ ከእነዚህ አለማቀፋዊ የመረጃ ምንጮች ባሻገር የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴሌቪዠን (ኢሳት) የፌዴራል ዓቃቢ ህግ አቶ ብርሀኑ ፀጋየ ከዘረዘራቸው ድርጊቶች በላይ ሰፊና ጥልቅ መረጃ አቅርቧል፡፡ በተጨማሪም ለሆዳቸው ሳይሆን ለህሌናቸው የሚኖሩ ጋዜጠኞች እና ፀሀፊያን  በተለያዩ ፅሁፋቸው ሲሰራ የነበረውን ግፍ፣ ስርቆት እና በደል ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ከእስር-ቤት የወጡት ወንድም እና እህቶቻችን በተለያዩ ግዜያት የሰጡት ቃል ህያው ምስክር ነው፡፡

ታዲያ እነዚህ ሁሉ አስረጅዎች በዙሪያችን እያሉ፣ በፌዴራል ዓቃቢ ህጉ ዝርዝር ትንታኔ መገረማችን ከመረጃ ምን ያህል እንደራቅን የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያውያን  ወገኖቻችን ህመምን ህመማችን ስላላደረግነው በየእስር ቤቱ ሲካሄድ የነበረውን ሰቆቃ ማዳመጥ አለመቻላችንን የሚያሳይ ነው፡፡ በሀገር ጉዳይ ላይ የግዴለሽነት እና ‘ምን አገባኝ’ የሚል አባዜ ተጠናውቶን በሀገር ላይ ለሚሰነዘሩ የዘረፋ ጥቃቶች ፊታችንን አዙረን እንደነበር የሚያመለክት ማስረጃ ይመስለኛል፡፡ ስለሀገረ ኢትዮጵያ አንድነትና ጥቅም፣ ስለ ዜጎቿ መብት ሲታገሉ እና ሲያታግሉ ለነበሩ ኢትዮጵያውያን የአቶ ብርሀኑ ፀጋየ ሪፖርት አዲስ ሊሆንባቸው አይችልም፡፡

ህወሃት በኢትዮጵያ እና በዜጎቿ ላይ ለ27 ዓመታት የፈፀመው ወንጀል የፌዴራል ዓቃቢ ህግ አቶ ብርሀኑ ፀጋየ ከዘረዘሩት በላይ ነው፡፡ ለሰቆቃ ዘመናችን መርዘም ደግሞ ዋናው ምክንያት በህወሃት ትርክት መከፋፈላችን እና የወገኖቻችንን ቁስል ቁስላችን አለማድረጋችን ነው፡፡ ስለዚህ የጎሳ ፖለቲካን ከህወሃት ጋር በመቅበር እና በአንድንት በመቆም፤ በዜጎቻችን ላይ የሚደርሰውን ማንኛውንም የሰብዓዊ መብት ጥሰት፣ መፈናቀል እና ግፍ በራሳችን ላይ እንደደረሰ በማሰብ እና አምርረን በመቃወም የነገዋን ኢትዮጵያ የሰላም ምድር ልናደርጋት ይገባል፡፡

Filed in: Amharic