>

ጩኸታችን ሰሚ አግኝቷል፤ ሂደቱ ግን ወጥነት እና  ግልጽነት የተላበሰ ይሁን! (ያሬድ ሀ/ማርያም)

ጩኸታችን ሰሚ አግኝቷል፤ ሂደቱ ግን ወጥነት እና  ግልጽነት የተላበሰ ይሁን!
ያሬድ ሀ/ማርያም
*  አብዛኛው የአገዛዙ ባለሥልጣናት በተለይም በፖሊስ፣ በመከላከያ እና በደህንነት ተቋማት ውስጥ ያገለገሉ ሰዎች በተፈጸሙት የመብት ጥሰት ተሳትፎ የነበራቸው ናቸው። ስለዚህ በወንጀል የሚጠየቁትን ሰዎች መንግስት የሚለይበት መስፈርቱ ምንድን ነው? የማይጠየቁስ ካሉ ለምን? የመለያ ደረጃው ምንድን ነው?  
—-
መንግስት የመብት ጥሰት ወንጀል የፈጸሙ ሰዎችን ለፍርት የሚያቀርብበት መንገድ ግልጽነት እና ወጥነት ያለው ሊሆን ይገባል።
ላለፉት ሃያ አመታት ሰብአዊ መብት የሚጥሱ አካላት ለፍርድ ይቅረቡ፣ በሕግ አግባብ ተጠያቂ ይሁኑ፣ ተበዳዮችም ይካሱ እያልን ስንጮኽ ኖረናል። መንግስት አሳሪ፣ ገዳይ፣ አፋኝ፣ አሳዳጅ ብቻ ሳይሆን ከሳሽ አቃቢ ሕግ እና ፈራጅ ዳኛም እራሱ ስለነበር ጩኸታችን ሰሚ አልነበረውም።
የዚህ ለውጥ አንዱ ቱርፋት እነኚህን በጉያው የነበሩትን እና የከፋ የመብት ጥሰት ወንጀል በመፈጸም አለም ያወቃቸውን ሰዎች ለፍርድ ማቅረብ መጀመሩ ነው። የዶ/ር አብይ አመራር እየወሰደ ያለውን እርምጃ ማድነቅ ብቻውን በቂ አይሆንም። ሁላችንም፤ በምንችለው መጠን ለመንግስት ድጋፍ ማድረግ ይገባል ብዮ አምናለሁ።
– የመብት ተሟጋቾች፣ ጋዜጠኞችና በሰብአዊ መብቶች ዙሪያ ጥናት እና ምርምር ያደረጉ ሰዎች አሁንም ውትወታቸውን መቀጠል አለባቸው፤
– የመብት ጥሰት የደረሰባቸው ሰዎች በተለይም የማሰቃየት ተግባር የተፈጸመባቸው ሰዎች የት፣ መቼ፣ በማን እና በምን ሁኔታ ድርጊቱ እንደተፈጸመባቸው ያላቸውን ማስረጃ ለመንግስት ቢሰጡ ጥሩ ነው፤
– መንግስትም ዜጎች ጥቆማ ሊያቀርቡ እና መረጃ ሊሰጡ የሚችሉበትን ሁኔታ ቢያመቻች ጥሩ ነው።
እስካሁን በሕግ ጥላ ስር እንዲውሉ ከተደረጉት ጥቂት ከፍተኛ አመራሮች ባልተናነሰ የከፋ የመብት ጥሰት ሲፈጽሙ የኖሩ ሰዎች አሁንም የመንግስት ደሞዝ እየተከፈላቸው በተለያዩ ተቋማት ውስጥ ተሰግስገው ይገኛሉ። እነኚህ ሰዎች ከጥፋታቸው እንዲማሩ እና ለሌላውም መቀጣጫ እንዲሆን ምርመራ ሊካሔድባቸው እና ለፍርድም ሊቀርቡ ይገባል።
አሁን እየተካሄደ ያለው እስር በአንድ በኩል ከብርጋዴል ጀነራል እስከ ተራ ጋዜጠኛ ድረስ ይነካል። በሌላ መልኩ በመብት ጥሰት በታወቁ ተቋማት ውስጥ ቁልፍ ሚና ያለቸውን ሰዎች እና ሹማምንት ተደማሪ አርጎ ይጓዛል። ይህ አይነቱ ግልጽነት የማይታይበት፣ መስፈርቱ ተለይቶ የማይታወቅ እና በየትኛው የጥፋት ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎችን እንደሚያዳርስ ግልጽ ባልሆነበት ሁኔታ የከፋ ጥፋት የፈጸሙ ሰዎች ከተጠያቂነት ሊያመልጡ የሚችሉበትን እድል ይፈጥራል። በተቃራኒውም በይቅርታ ሊታለፉ የሚችሉ ጥፋተኞችንም ሰለባ ሊይደርግ ይችላል።
መንግስት ይህ የተጀመረውን አጥፊዎችን ለፍርድ የማቅረብ ተግባር ተነካክቶ እና የተወሰኑ ሰዎችን ብቻ ኢላማ አድርጎ አንዳይቆም ጉዳዩን በሁለት መልኩ ይዞ የሕዝቡን የፍትሕ ጥያቄ በአግባቡ ቢመልስ መልካም ነው።
፩ኛ/ ከፍተኛ የመብት ጥሰት ያደረሱ እና እጅግ ከፍተኛ ግምት ያለው የሃገር ሃብት የዘረፉ ወይም ያወደሙ ሰዎችን በበቂ ማስረጃ ተደግፎ ማሰሩ እና ለፍርድ የማቅረቡ ሥራ በተጀመረው አካሄድ እና ወጥነት ባለው መልኩ ማስቀጠል፤
፪ኛ/ በጥቅሉ በመብት ጥሰት ላይ በማናቸውም መልኩ በቀጥተኛም ይሁን በተዘዋዋሪ መልኩ ተሳትፎ የነበራቸው ሰዎች ላይ እና በአነስተኛ የሙስና ተግባር ላይ የተሰማሩ ሰዎችን ለይቶ በማውጣት፣ የጥፋተኝነት ድርሻቸውን በማስረጃ አስደግፎ እና ዘርዝሮ በመግለጽ በሌሎች አገራት፤ በደቡብ አፍሪቃ እና ሌሎች ተመሳሳይ ችግሩ የነበረባቸው አገሮች እንዳደረጉት አጥፊዎች በይፋ ሕዝብን ይቅርታ እንዲጠይቁ አድርጎ ጉዳዩን በይቅርታ መዝጋት።
አሁን በተጀመረው መልኩ የተወሰኑ ሰዎችን የማሰሩ እርምጃ እስከምን ድረስ ሊሄድ እንደሚችል ግልጽ የሆነ ነገር የለም። ያ ብቻም ሳይሆን ለተዛባ አሰራርም ክፍተትን ይፈጥራል። አብዛኛው የአገዛዙ ባለሥልጣናት በተለይም በፖሊስ፣ በመከላከያ እና በደህንነት ተቋማት ውስጥ ያገለገሉ ሰዎች በተፈጸሙት የመብት ጥሰት ወንጀሎች ላይ በአንድ ወይ በሌላ መልኩ ተሳትፎ የነበራቸው ናቸው። ስለዚህ በወንጀል የሚጠየቁትን ሰዎች መንግስት የሚለይበት መስፈርቱ ምንድን ነው? የማይጠየቁስ ካሉ ለምን? የመለያ ደረጃው ምንድን ነው?  እነዚህ ነገሮች በአግባቡ ተጠንተው እና መስፈርት ወቶላቸውም ከሆነ እየተካሄዱ ያሉት ይህ ለሕዝብ ይፋ ሊደረግ ይገባል። ይህ ካልሆነ በሰበር ዜና የሚደረጉ እወጃዎች ሕዝብን ግራ ያጋባል። ሂደቱን የተለየ መልክ ሊሰጡት ለሚፈልጉ ሰዎችም ቀዳዳ ይፈጥራል። በሂደቱ ውስጥ ግለሰቦችን ለማጥቃት ወይም መድልዖ ለመፈጸም ለሚፈልጉ ሰዎች በር ይከፍትላል። በሥራ ላይ ያሉ የመንግስት ተሿሚዎችም በሰቀቀን እንዲቆዩ ያደርጋል። ሂደቱን ግልጽ ማድረግ ግን የወደፊት መንገዳችንን የጠራ ያደርገዋል።
 ፍትሕ ለግፉአን! ብሔራዊ እርቅ ለአገር ዘላቂ ሰላም!
Filed in: Amharic