>
5:13 pm - Friday April 19, 4740

የሰማዕቱ የአሰፋ  ማሩ ደም እንደ አቤል ደም ይጮሀል!  (አቻምየለህ ታምሩ)

የሰማዕቱ የአሰፋ  ማሩ ደም እንደ አቤል ደም ይጮሀል!  
አቻምየለህ ታምሩ
አቶ አሰፋ ማሩ በቀድሞው አጠራር በወሎ ጠቅላይ ግዛት በላስታ አውራጃ መቄት ወረዳ በ1951 ዓ.ም እንደተወለደ የሕይወት ታሪኩ ያስረዳል። አሰፋ ማሩ በመምህርነት ሙያ ከማገልገሉም ባሻገር በወያኔ ዘመን የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር የአመራር አባል በመሆን የመምህራንን መብትና ጥቅም ለማስከበርና የትምህርት ጥራት ለማስጠበቅ በሚደረገው ትግል ውስጥ ግንባር ቀደም በመሆን ሕይወቱ በፋሽስት ወያኔ ወታደሮች በጠራራ ፀሐይ እስከተቀጨበት ዕለት ድረስ በጽናት ሲታገል የኖረ የቀለም አርበኛ ነው። ከመምህራን ማኅበር በተጨማሪ ከመገደሉ በፊት በነበረው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤም በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በመሆን የፋሽስት ወያኔ አገዛዝ የሚፈጽመው ግፍና ግድያ በማጋለጥ የላቀ ድርሻም አበርክቷል።
ከዛሬ ሀያ ሁለት ዓመት ከስምንት ወር በፊት ሚያዚያ 30፣ 1989 ዓ.ም. የ37 ዓመት ጎልማሳና የሁለት ልጆች አባት የነበረው አሰፋ ማሩ ከቤቱ ወደ ሥራው በመጓዝ ላይ እንዳለ ልክ ከጠዋቱ 2፡20 ጉድ ሼፐርድ የቤተሰብና ጤና አገልግሎት ይባል በነበረው አካባቢ በትግራይ ወታደሮች በግፍ ተረሽኗል።
ጀግናው አሰፋ ማሩ እንዴት እንደተገደለ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ «Extra-Judicial Killing» በሚል ባወጣው Special Report No. 14 እና እ.ኤ.አ. May 13, 1997 ባሳተመው ሪፖርቱ የዓይን እማኞችን ጠቅሶ የአሰፋ ማሩን አገዳደል እንዲህ አቅርቦታል።
ጉድ ሼፐርድ አካባቢ አሰፋ ዳገቱን ወጥቶ ሊጨርስ አካባቢ አንዲት ፒክአፕ መኪና መጥታ ከፊቱ መንገዱን ዘግታበት ቆመች። የመገናኛ ሬድዮ የያዘውን ሰውዬ እና ሹፌሩን ሳይጨምር መኪናዋ ክላሽንኮቭ ጠብመንጃዎችንና የእጅ ቦምቦችን ወገባቸው ላይ የታጠቁ ስድስት «ፖሊሶችን» ይዛ ነበር። አሰፋ ማሩ ወደ ግንቡ ተጠግቶ መኪናዋን ለማለፍ ሞከረ። በዚህ ጊዜ አሰፋን ከቅርብ ርቀት ስትከተለው የነበረች ሌላ ኦፔል የፖሊስ መኪና የአደጋ ጥሪ እያሰማች ወደ እርሱ ቀረበች። ከኋላ ወንበር ላይ ተቀምጦ የነበረ ፖሊስም አውቶማቲክ መሣሪያ አውጥቶ አሰፋ ላይ አከታትሎ ተኮሰበት። አሰፋም ወዲያው ነፍሱ ከሥጋው ተለየች።
በፒክአፕ መኪና ላይ ከነበሩትም ሆነ በኦፔሏ ውስጥ የነበሩት ፖሊሶች አሰፋን እንዲቆም አላዘዙትም። የማጠንቀቂያ ተኩስ ወደ ሰማይም አልተኮሱም። ወይም ከመያዝ ለማምለጥ የሚሞክርን ሰው ከሩጫው ለመግታት እንደሚደረገው ወደ እግሮቹ አልተኮሱም። ይልቁንም የተተኮሱት ጥይቶች በሙሉ የታለሙት ወደ ጭንቅላቱና ወደ ደረቱ ነበር። አሰፋ ማሩ ሲወድቅ ኦፔሏ መኪና መንገዷን ሳታቋርጥ ወደፊት ቀጠለች። በፒክ አፕ መኪናዋ ላይ የነበሩት ስድስት ፖሊሶች ግን ከፒካፓቸው ላይ ወርደው መንገዱን ከላይም ከታችም ዘጉት። ከእነርሱ መካከል የተወሰኑት የአቶ አሰፋን አስከሬን ኪሶች በረበሩ፤ የእጅ ቦርሳውንም ወሰዱ። ከዚህ በኋላ ተጨማሪ አራት ፖሊሶች በላንድሮቨር የፖሊስ መኪና ተጭነው መጡ። መኪናውም እነርሱን አራግፎ ተመለሰ።
ጥቂት ቆይቶም አስከሬን ለመጫን የሚያገለግል የፖሊስ መኪና መጥቶ የሟቹን አስከሬን አነሣ፤ በተፈሪ መኮነን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት [ የዛሬው እንጦጦ ቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ኮሌጅ] በስተጀርባ አድርጎ ወደ ስድስት ኪሎ በረረ። አስሩ ፖሊሶችም በቶዮታ ፒክ አፕ መኪናዋ ላይ ተጭነው የአስከሬን መኪናውን ተከተሉት። አሰፋ ከተገደለ ከ25 ደቂቃዎች በኋላ (2፡45) የመገናኛ ሬድዮዎችን የያዙ፣ አውቶማቲክ መሣሪያዎችንና የእጅ ቦምቦችን የታጠቁ «ፖሊሶች» አሰፋ ቤት በመሄድ የፍርድ ቤት የብርበራ ማዘዣ በማቅረብ የሟቹን ቤት በረበሩ። በቤቱ ውስጥ ግን ከካሴቶች፣ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤና ከኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ሰነዶች ውጪ አንድም ያገኙት የጦር መሣሪያ አልነበረም።
በብርበራ ያገኗቸውን ወረቀቶቹንና ካሴቶቹን በሙሉ ወሰዷቸው። በተመሳሳይ ሰዓት በኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ጽሕፈት ቤት 12 ፖሊሶች ደርሰው ነበር። እነዚህ ፖሊሶች ግን የፍርድ ቤት የብርበራ ማዘዣ አልነበራቸውም። ይህ ግን የማኅበሩን ሠራተኞች ጨምሮ 34 ሰዎችን ከማሰርና አሰፋ ማሩ ምክትላቸው የነበሩትን የመምህራን ማኅበሩን ፕሬዝደትን የዶ/ር ታዬ ወልደ ሰማያትን ቢሮ ከመበርበር አልከለከላቸውም።
ከረፋዱ 4፡00 ሰዓት ገደማ የማይታወቅ የትግርኛ አማርኛ የሚናገር ሰው ወደ ኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ ቢሮ ስልክ በመደወል «አሰፋ ማሩ ለሚባል ሰው ታውቁታላችሁ? ለእናንተ አባል ነው?» ሲል በትግርኛ አማርኛ ጠየቀ። አዎንታዊ ምላሽ ሲያገኝም «አሰፋ በመኪና አደጋ ስላረፈ አስከሬኑን ከምኒልክ ሆስፒታል መጥታችሁ ውሰዱ።» ሲል የአሰፋን ማለፍ እንደቀላል ተናገረ። የማይታወቀው ታጋይ አሰፋ የትና መቼ እንደሞተ እንዲናገር ሲጠየቅ ለመናገር ፈቃደኛ አልነበረም፤ ይልቁንም «ትፈልጉ እንደሆነ፣ አስከሬኑን ውሰዱና ቅበሩት ፤ ካልፈለጋችሁ የራሳችሁ ጉዳይ » በሚል ዐረፍተ ነገር ንግግሩን ቋጨው። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ አባላት ወዲያው ወደ ምኒልክ ሆስፒታል በፍጥነት ሄዱ። ያገኙት ግን በመኪና የተገጨ ሰው ሳይኾን ጭንቅላቱና ደረቱ በጥይት የተበሳሱ ፊቱ በደም አበላ የተሸፈነ፣ የሸሚዙ ደረት በደም የተነከረ የአሰፋ ማሩን አስከሬን ነበር።
እኩለ ቀን ላይ የፌደራል ፖሊስ አገዛዙ የሜዲያ ልሳኖች ሁሉ አሰፋ ማሩ «የአርበኞች አንድነት ግንባር» የሚባል «ፀረ-ሰላም ታጣቂ ቡድን» አባል እንደነበርና «አልያዝም ብሎ በማስቸገሩ» እርምጃ እንደተወሰደበት አወጀ። አሰፋ ግን የተባለው ቡድን አባል መሆኑን የሚያረጋግጥ አንድም መረጃ አልቀረበም።
ፋሽስት ወያኔ አሰፋ ማሩን ለምን ገደለው?
አሰፋ ከጅምሩ በወያኔ ጥርስ የተነከሰበት የአንጋፋው የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ምክትል ሊቀ መንበር ነበር (ዋና ሊቀ መንበሩ ዶ/ር ታዬ ወልደ ሰማያት ነበሩ)። ይህ ማኅበር ደግሞ የተማሩና የሀገራቸው ዕጣ ፈንታ የሚያሳስባቸው ሰዎች የተሰባሰቡበት ተቋም ስለነበር ወያኔ እንደልቡ ሊያዝዘው፣ ሊጠመዝዘው የሚችል ማኅበር አልነበረም። በተጨማሪም ወያኔ ገና አዲስ አበባ ከመግባቱ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 42 መምህራንን ማባረሩን ልብ ይሏል። ከእነዚህ ተባራሪ መምህራን አንዱ የኢመማ ሊቀመንበር የነበረው ዶ/ር ታዬ ወልደ ሰማያት ነበሩ።
ከዚህም በተጨማሪ፣ አሰፋ ማሩ በየጊዜው በአገዛዙ ኃይሎች የሚፈጸሙትን አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች የሚያጋልጠው የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ሥራ አስፈጻሚ አባል ነበር። የጉባኤው ሥራ አስፈጻሚ ለመሆን አንዱ መስፈርት ደግሞ የምንም ዓይነት የፖለቲካ ድርጅት አባል አለመሆን ነበር። እንኳን ብረት ያነሣ ቡድን አባል ይቅርና ሰላማዊ ትግልን የመረጠ የፖለቲካ ፓርቲ አባል የሆነ ሰው እንኳ ለሥራ አስፈጻሚነት መመረጥ አይችልም ነበር። አሰፋም ማሩ በጉባኤው ለሥራ አስፈጻሚነት ሲመረጥ የምንም ዓይነት የፖለቲካ ድርጅት አባል አለመሆኑን አስረድቷል፤ ጉባኤውም ተቀብሎታል።
አሰፋ ንቁና የሀገሬ ጉዳይ ያገባኛል ባይ ሰው ነበር። ጨካኙ መለስ ዜናዊና የወንጀል ግብረ አበሮቹ ደግሞ ይህቺ የአሰፋ የህሊና ሰው መሆን አልተመቻቸውም። እናም በጠራራ ጸሀይ እረሸኑት። የአሰፋ ማሩ ደም በግፍ የፈሰሰ የአቤል ደም ነው!
በትግራይ ወታደሮች በጠራራ ፀሐይ የተረሸነው የአሰፋ ባለቤት በአገር ውስጥ መኖር ባለመቻሏ መከራዋን በውስጧ፤ ሕጻናት ልጆቿን ደግሞ በጀርባዋ አዝላ ተሰደደች። ከአመታት ውጣ ውረድ በኋላ ዛሬ ላይ ከሀገሯ በብዙ ሺህ ኪሎ ሜትሮችን ርቃ የፍትሕን ቀን እየናፈቀች በካናዳ ትኖራለች። ውድ ባለቤቷና የልጆቿን አባት ለምን እንደገደሉት የማወቅ ረሀብ እየቦረቦራት፣ ልቧ በሐዘን ተሰብሮ የሰቆቃ ኑሮ እየገፋች ትኖራለች። የአሰፋ ማሩ ባለቤትና ልጆች ፍትሕ ይሻሉ! አሰፋን የገደሉት አውሬዎች በአስቸኳይ ለፍርድ ይቅረቡ ዘንድ ይሻሉ!!!ፍትህ በመለስ ዜናዊ ትዕዛዝ በትግራይ ወታደሮች በጭካኔ ለተረሸነው ለሰማዕቱ አሰፋ ማሩ! ፍትህ ፋሽስት ወያኔ በግፍ ለረሸናቸው ኢትዮጵውያን ሁሉ!
አሰፋ ማሩ —እግዚያብሔር ነፍሱን በገነት ያኑራት! እኛ ወንድሞችህ አልረሳንህም! ልጆችህን ያላሳዳጊ ያስቀሩትን፤ ቤተሰብህን የበተኑትን፤ ባለቤትህን ያንገላቱትንና ውድ ሕይወትህን በለጋው የቀጠፉትን ጨካኞቹን ገዳዮችህ አገርና መንግሥት ሲኖረን ለፍርድ ሳናቀርብ እንቅልፍ ባይናችን አይዞርም!
Filed in: Amharic