>
6:10 pm - Monday May 16, 2022

የሜቴክ ህክምና ፍላጎት!!! (አንሙት አብርሃም)

የሜቴክ ህክምና ፍላጎት!!!
አንሙት አብርሃም 
ለበርካታ አገራት ቀጣይ እድገት ምንጩ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍና ቴክኖሎጂ ልማት ላይ የፈጠሩት አገራዊ አቅም ነው፡፡ የጀመሩትን እድገት ወደፊት ይዞ ለመቀጠል የሚያስችል የቴክኖሎጂ ምርምርና ፈጠራ ላይ ክህሎት ያለው ወጣት በማፍራት ላይ የሠሩት ስራ ጠቅሟቸዋል፡፡ ወጣቶቻቸውን ወደ ፈጠራና ፍብሪኬሽን እንዲያዘነብሉ ለማድረግ የሚያግዝ የተቋምና ስርዓተ ትምህርት መሠረቶችንም አበጅተው ጠንክረው ሠርተውበታል፡፡ ብዙዎቹ developed and emerging economies የዚህ ውጤት ናቸው፡፡  ወጣቶቹ እውቀቱን ብቻ ሳይሆን ክህሎቱን አግኝተው የራሳቸውን ተቋም መስርተው አምራች እንዲሆኑ ለማድረግ መነሻ አገራዊ መሠረቶች ነበሯቸው፡፡ ይህንም የኢንዱስትሪና ፋብሪኬሽን ጅማሮ በወታደራዊ ተቋማት ውስጥ በጥብቅ ዲሲፕሊን እና መንግስታዊ ክትትል እንዲመራ በማድረግ ነው፡፡ ወጣቱ በነዚህ ተቋማት እየተሳተፈ አድጎ አምራች የፈጠራ ድርጅት ባለቤት እንዲሆን ምቹ መደላድል ፈጥረዋል፡፡  ይህ እንግዲህ በአውሮፓ ከተለኮሠው የኢንዱስትሪ አቢዬት ጀምሮ አንዱ ከሌላው ትምህርት እየወሠደ እያሻሻለና የራሱን ፈጠራ እየጨመረ የፈፀመው ነው፡፡ በአውሮፓ መቶ አመት የፈጀው ኢንዱስትራላይዜሽን በነኮርያና ጃፓን ሃምሳ፡ በነ ቻይናና ጥቂት የእስያ አገራት  ሠላሳ አመታትን ፈጅቶ ተሳክቷል፡፡ አንደኛው የሌላኛውን ቴክኖሎጂ በመለማመድ ፡ በመቅዳትና አዳዲስ በመፍጠር ጉዟቸውን እያቀለሉ ሄዱ፡፡

የኢንዱስትሪ ልማት መሠረቱ በወታደራዊ ተቋማት እንዲመራ ያስፈለገው፡ የማምረት አቅም ግንባታው የማይቆራረጥና ውጤታማ እንዲሆን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ጥብቅ ዲሲፕሊን፡ ታዛዥና መፈፀም የሚችል ፡  ሚስጥር ጠባቂ፡ ከራስ ይልቅ ለአገር ፍቅር ያለው፡ ወዘተ የሰው ኃይል ማሰማራት ይፈልጋል፡፡
ለዚህ ምቹ የሆነው ደግሞ የወታደራዊ ስነምግባር በመሆኑ ወታደራዊ የኢንዱስትሪ  ተቋማትን በመመስረት በሂደቱ የሲቪል ኢንዱስትሪ ልማት አቅም ምንጭ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል ፡፡ በሂደት የልማቱ እርሾ የሆኑት ወታደራዊ ተቋማት ( “አቅም ፈጣሪ አቅም ሆነው” ) በወታደራዊ ቴክኖሎጂ ላይ ስፔሻላይዝ ሲያደርጉ በሲቪል ዘርፉ ያሉቱ አገራዊ ተወዳዳሪነትን አሳደጉ፡፡ በወታደራዊ ተቋማት ውስጥ እጃቸውን ያፍታቱ ወጣቶች ቀስበቀስ ወደግል ስራ ዙረው አምራቾች ለመሆን ችለዋል፡፡ እንደ ወታደራዊ ተቋማት ሁሉ ሲቪሉም የፋብሪኬሽን ምርቶቹን ለዓለም ገበያ በመስራት ተቋማዊና አገራዊ ውድድሩን አጡዞታል፡፡
አሁን አሁን ደግሞ ከኢንዱስትሪው በተጨማሪ የ’ Cyber Development’ን  ተመሳሳይ ጥብቅ ወታደራዊ ባህል በማድረግ አገራት በVirtual world የሳይበር ሠራዊት እየገነቡ መወዳደር ይዘዋል፡፡ የአካዳሚክ መስኩ የምርምርና ፈጠራ ዘርፍ ላይ እያተኮረ መምጣት፡ የፈጠራና ግብይት ምንጭና መነሻ ወታደራዊ ተቋማት ብቻ የመሆናቸውን ታሪክና እድል እያጠበበው ቢመጣም፡ ዛሬም ድረስ ላለው Global Arms Race የወታደራዊ ኢንዱስትሪ አካዳሚዎች የላቀ ሚና አላቸው፡፡
➊☞ የMETEC እና INSA ምስረታ በአንድ በኩል ከዚህ አስተሳሰብ የመነጨ ነው፡፡
–*–
ዘመኑ ምህረት የለሽ ውድድር የሚታይበት፡ አምርቶ መወዳደር አሊያም መውደቅ ብቻ አማራጭ የሆነበት ነውና የሰው ምርት እየተቀለቡ መቀጠል ጭንቅ ነው፡፡
[እዚህ ላይ ትንሽ ቁምነገር እንጨምር]
በሉላዊው ዓለም የቴክኖሎጂ እና ኢንዱስትሪ ውጤቶች አምራችነት  ምርጫ አይደለም ፡ ማምረት ብቻውንም አይበቃም- ወይ ገቢ ምርትን መተካት አለበት ወይ ወደ ውጭ መላክ አለበት፡፡ ‘export መር’ ሲባል የምንሰማው ለዚያ ነው፡፡ መላክ ካልቻልክ የሚልኩልህን መቀበል ነው፡ ያውም ማምጣትና መግዛት ከቻልክ፡፡ እንደምንም ገበያ የሚፈልገውን ነገር ማቅረብ አለብህ፡፡ ግን መላክ ብቻውን አይበቃንም÷ ማንም ሊልክ ይችል ይሆናል፡፡ በምርት ጥራትና ዋጋ መወዳደር የግድ ነው፡፡ በዓለም ገበያ ከመሠሎችህ ምርት ጋር መወዳደር ብትችል እንኳ ስራው አላለቀም፡፡ ተወዳዳሪነትህ ጊዜያዊ ነው፡፡ ዘላቂ ተወዳዳሪት የግድ ነው፡፡ ይህቺ ደግሞ ጭንቅ ናት፡፡ ዘላቂ ተወዳዳሪነት ከቢሮክራሲ ጥራት ጋር ይያያዛል፡፡ Competitive and comparative advantage ሲባል ከቀበሌ አገልግሎት ጥራት ይጀምራል፡፡ [ስለጥራት ምንነት ሌላ ቀን እናወራለን]
በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ ጫማ ለመሸጥ backward linkage ላይ ከከብት እርባታውና ቆዳ አቅርቦቱ ጥራት ጋር forward linkage ደግሞ ከገበያው እስከ ደንበኞች ፍላጎት ምርጥ መሆን አለብህ ማለት ነው፡፡ ይህ በፈጠራና ምርምር ካልታገዘ አይታሰብም፡፡ አገራዊና ተቋማዊ የadaptation እና Innovation ባህልና ልምድ ያስፈልጋል፡፡ ፈጠራና ምርምር በሌለበት ዘላቂ ተወዳዳሪነት ህልም ነው፡፡ ተዘርረህ መቀመጥ ብቻ ነው፡፡ New version of the product is mandatory. የያዝከው ስልክ የዚህ ውጤት ነው፡፡
ይህ ካልሆነ እንደምንም እድገት ቢመጣ እና የመካከለኛ ገቢ ኢኮኖሚ ላይ ቢደረስ እንኳ ፈጠራ የሌለው ኢኮኖሚ የመካከለኛ ገቢ ማነቆ [middle income Trap] ውስጥ ይወድቃል፡፡  Innovative ኢኮኖሚ መገንባትና አዳዲስ ምርት እያመረቱ የሚስፋፉና ወደ ገበያ ማቅረብ ካልተቻለ በየአመቱ የሚመጣው ወጣት የገቢ ምርትን እየተካፈለ የሚበላ ነው፡፡ ያንን ማድረግ ያልቻሉት እነ ግብፅ፡ ቱኒዝያ፡ እና የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ኢኮኖሚያቸው በኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ ዘርፍ ሊሸጥ የሚችል ምርት ማምረት አቅቶት በመካከለኛ ገቢ ማነቆ ውስጥ ወድቀው፡ ከፍም ዝቅም ማለት ሳይችሉ ወደ ሸማችነት ተሸጋገረው አሉ፡፡ የግብፅን ኢኮኖሚ የተሸከመው ወታደራዊ ኃይል የሰው ምርት ሸምቶ የሚያከፋፍል ኪራይ አዳይ ሆነ፡፡ የሰው ምርት እየሸመተ በመብላት የሰፋ ሆድ ደግሞ በቀላሉ አይመለስም ፡፡ በነዚህ አገራት የአዲሱን ትውልድ የስራ እድል ፍላጎት የሚሸከም አዲስ የፈጠራ ስርዓት ጠፋ፡፡ እናም የተቃውሞ ማዕበል አነደዳቸው፡፡ የተፈጥሮ ኪራይ የታደሉት ያላቸውን ሃብት ሸጠው ሸምተው ያድራሉ፡፡ እነ ኳታር  ለዜጎች ገንዘብ በነፍስ ወከፍ አድለው ማዕበሉን የሸወዱት ለዚያ ነው፡፡
እናም ማምረት፡ መላክ፡ በዘላቂነት መወዳደር ምርጫ አይደለም፡፡

ይህ የእኛም ግዴታ ነው፡፡ በዚህ ዓለማቀፋዊ የግዴታ ግዴታ ውስጥ ኢትዮጵያውያን ተስፋ ያደረግነው ደግሞ አንድም እነ’ሜቴክን አቋቁመን ተቋማቱ  በወታደራዊና ሲቪል ዘርፎች በሚጥሉት የኢንዱስትርያል ኢንጂነሪንግ ቴክኖሎጂ የadaptation እና Innovation ባህል፡ ልምድና አገራዊ አቅም ነገ ቆሞ መሄድ መቻልን ነበር (ነው):: በፈጠራና ምርምር ፡ ክህሎት ያለው አምራች ኢንደስትሪያሊት መፍለቂያ በመሆን አቅም ፈጣሪ አቅሞች እንዲሆኑ ነበር ተልዕኮው፡፡ This is the very cause of existence for METEC/INSA!
((በርግጥ ኢትዮጵያ የ70/30 ስርዓተ ትምህርት ድርሻ ፖሊሲ፡ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተቋማት ፡ ድምፅ አልባዎቹ የጥናት ምርምር ኢንስቲቱዩቶች፡ የሳይንስ አካዳሚ ፡ ዓመታዊ የሳይንስና ቴክ ሽልማት፡ 2ቱ ልዩ ዩኒቨርስቲዎች፡ ወዘተ..መነሻቸው ይሄው ከማነቆው የመውጣት ዓለማቀፍ ፈተና ነው፡፡))
ሆኖም;
➋☞ ከሜቴክ ጋር የተያያዘ ቅራኔ አንዱ ምንጭ በዘርፉ ፍላጎትና በተቋሙ ራዕይ ዙሪያ አገሪቱም፡ ተቋሙም፡ ዜጎችም አልተግባቡም ነበር፡፡

ሜቴክና የፍላጎቶች ውጥረት(1) :- ምርምር ፡ ገንዘብና ገበያ

ዛሬ በኢንዱስትሪ በልፅገዋል ለሚባሉት አገራት ታዲያ ከመካከለኛ ገቢ ኢኮኖሚ ወደ ከፍተኛ ገቢ ኢኮኖሚ ለማደግ ያበቃቸውና ለስኬታቸው ገበያ ትልቅ ሚና ነበረው፡ አለው፡፡ እንዴት?
አሜሪካውያንም ሆኑ አውሮፓውያን ገና ከጅምሩ የኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ ላይ እጃቸውን ማፍታታት ሲጀምሩ የማኑፋክቸሪንግ እና ፋብሪኬሽን ምርቶቻቸው ጥራት እዚህ ግባ የሚባል አልነበረም፡፡ አዳዲስ የፈጠራ ምርት እንደመሆኑ  በጅምሩ ምርጥ የሚሆን ነገር የለም፡፡ ጥራት progressive /incremental ነው፡፡ በዚህ ላይ ብልሽትና ብክነት አለ፡፡ እናም በምርቶች ላይ የሚደረግ ጥናትና ምርምር በተለይ የአዳዲስ ምርት ዓይነቶች ፍለጋ capital intensive ነው፡፡ በድሃና እድገት ጀማሪ አገር ለመማሪያ የሚሆን ትርፍ ካፒታል የለም፡፡
በዚህ ረገድ ታዲያ ቀዳሚዎቹ የኢንዱስትሪ ጀማሪዎች ስራቸውን ለመደጎም የሚያስችል የገበያ እድል ነበራቸው፡፡ ቀሪው ዓለም የኢንዱስትሪና ፈጠራ ሽታ በሌለው ወቅት አመረትን ያሉትን ወልጋዳ ምርት ሁሉ ጉድ እያለ ይገዛቸው ነበር፡፡ ሸጠው ባገኙት ገንዘብ እየተመራመሩ የጥራት መሻሻል እያመጡ ቀጠሉ፡፡ ዘግይተው የጀመሩት እነኮርያና ጃፓንም ቴክኖሎጂን ከአውሮፓና አሜሪካ እያስመጡ ከመላመድና መቅዳት ጀምረው ቀጠሉ፡፡ የዛሬዎቹ እነ ሳምሰንግ፡ ሁንዳይ፡ LGና ሌሎችም የአውሮፓና አሜሪካን ምርት በመገጣጠም ላይ የተጠመዱ ነበሩ፡፡ ገጣጣሚዎች ነበሩ፡፡ እነሱም በበኩላቸው የሞከሯቸውን ምርቶች በአነስተኛ ዋጋ ለእስያ፡ ላቲን አሜሪካ ፡ አፋሪካ እየሸጡ ለልጆቻቸው የምርምር ጥረት የሚሆን ካፒታል መፍጠር ቻሉ፡፡ እድሜ ለድሃው ሸምቶ አዳሪ፡፡ በሂደት የተሻሻሉ ምርቶችን ደግሞ የጥራት ፍጆታ ባህል ለገነባውና ከፍጆታ ምርት ማኑፋክቸሪንግ ወደ ሃይቴክ ምርምር ለገባው አሜሪካ እና አውሮፓ እየሸጡ አገራዊ የምርምርና ጥናት አቅም ፈጠሩ፡፡
“ክሽ ክሽ እንደጃፓን ዕቃ” እንዳልተባለ የጃፓን የቴክኖሎጂ ልማት አቅም ሲጎለብት ሸማች የነበሩት የእስያ ነብሮች በቻይና እየተመሩ የቴክኖሎጂና ኢንዱስትሪ ልማቱን ተያያዙት፡፡ በዚያው ልክ የጀማሪ ምርት ተጠቃሚዎች እንደሚቀንሱ ልብ እንበል፡፡ ቢያንስ አውሮፓ፡ አሜሪካ እና ጃፓን ማንም የተለማመደበትን መለማመጃ ምርት እንደማይጠቀሙ ግልፅ ነው፡፡ የምርትና ምርታማነት ደረጃቸው ብቻ ሳይሆን የዜጎች የፍጆታ ምርጫቸው ጥራትም ስላደገ፡፡
በየተራ የኢንዱስትሪ ልማትና ምርምርን የተቀላቀሉ አገራት በአንድ በኩል ባለው ካፒታል ከመሸመት ውጭ አማራጭ የሌለው ክፍለዓለም መኖር የገበያ እድል አላሳጣቸውም ÷ እናም የቴክኖሎጂ ክህሎትን ለማሳደግ የሚረዳቸውን ካፒታል በየጊዜው  ‘እየተለማመዱበት’ የሚወጣን ምርት ገዢ ማግኘታቸው በእጅጉ ጠቅሟቸዋል፡፡ በሌላ በኩል የድንበር ተሻጋሪ ቴክኖሎጂ እያደገ መምጣት የመማሪያ ጊዜንና ዑደቱን (learning curve) አጭር አድርጎላቸዋል ፡፡ አሜሪካና አውሮፓም፡ እስያም ገዢ ነበራቸው፡፡ የኢንዱስትሪና ቴክኖሎጂ ልማትን በአፍሪካ እንጀምር ሲባል ግን የጀማሪን ምርት የሚገዛ አይገኝም፡፡
➌ ☞ ወደ ሜቴክ ስንመጣ አንደኛውን የቀውስ ምንጭ የምናገኘው እዚህ ላይ ነው፡፡ ድንበር ተሻጋሪ ገበያ በሌለበት “እየተማሩ መስራት፡ እየሠሩ መማር” ÷ ካፒታል በሌለው አገር በመማርና መስራት ሂደት ገንዘብ ለማባከን መፍቀድና መፈለግ አልተገናኝቶም!
እናማ ዓለም በነበረው የገበያ እድል የተማረበትን የቴክኖሎጂ ልማት ሜቴክ ሲጀምር የእኛ ወጣቶች የተለማመዱበትን ምርት የሚገዛ  ገበያ የለም፡፡ ስለዚህ የሜቴክ አመራር የመንግስት ተቋማት ይግዙን አሉና በየቢሮው ዱላ ይዘው መንቀሳቀስ ጀመሩ፡፡
የመንግስት አስፈፃሚ አካላት ደግሞ ከላይ በቁጥር ➊ እንደገለፅነው በሜቴክ ኢንዱስትሪያል ዓላማ ላይ እንደህዝቡና መንግስት አልተግባቡም፡፡ ስለዚህ ጥራት የሌለው ምርት አንገዛም እያሉ ማንገራገር ያዙ፡፡ ሜቴኮች በኢንዱስትሪው ሂደት ተወለጋግደው የሚወጡ ምርቶች ነገ ይቃናሉ ÷ ዛሬ ተበላሽቶብንም ካልሞከርነው የሚመጣ ክህሎት የለም እንደማለት እንዲያውም ” የተሻለ ምርት ከሆነ ፡ አመራርም ከውጭ የተሻለ ማምጣት ይቻላል” እያሉ ተናካሽ ሆነው ቀረቡ፡፡
ጥራት እያደገ የሚሄድ መሆኑን ከራሳቸው ተሞክሮ (ለምሳሌ በመጀመሪያዋ አውቶብስና በመቶኛዋ መካከል) እያነሱ ማስረዳት ሲችሉ ባገኙት ላይ ማጉረጥረጥ ስራዬ ብለው ያዙት፡፡ መቼለት ሜ/ጀ ክንፈ “..ጠቅላይ ሚኒስትርነትን ጠቅላይ ሚኒስትር ከሆነ በኻላ ነው የሚማሩት..”  ያለው በዚህ አስተሳሰብ ነው፡፡ እናማ ‘እሰራለሁ ትገዟታላችሁ’ የፍጥጫው ማዕከል ሆነ፡፡ በዚህ መሐል ወጭ አለ፡፡ ወጭውን ገበያ ካልደጎመው እየሠሩ መማር የለም፡፡ አውሮፓ የተማረው ለእስያና አፍሪካ እየሸጠ ነው፡፡ እኛ ያ እድል የለንም፡፡ ስለዚህ ልትማርና ልትሠራ ከሆነ ገንዘብ ያስፈልግሃል፡፡ ገንዘብ ከሽያጭ ይገኛል፡፡ ሜቴክ ግን with its arrogance እና በኢንዱስትሪያል ዓላማ አለመግባባት ከሁሉም ሴክተር አመራር ጋር ተናከሰ፡፡ ኃይለማርያም ደሳለኝም ዝም ብሎ ይመለከታል፡፡
ስለዚህ የሜቴክ አመራር ሁሉንም እሰራለሁ፡ የሠራሁትን ትገዛላችሁ ባህሪው ሆነ፡፡ ካልሸጠ መቀጠል ስለማይችል ነው በየከተማው አውቶብስ የተሸጠው፡ ለዚያ ነው አዲስአበባ ሶስኛ የአውቶብስ ድርጅት የተቋቋመው ፡፡ አንበሳ አውቶብስ ፡ ፐብሊክ ባስ፡ ሸገር ኤክስፕረስ ባስ፡፡
የገንዘብ ፍላጎቱን ለመሙላት የዋጋ ማስተካከያ እንኳ ማድረግ ሳይችል፡ በብድር ተዘፈቀ፡፡ በአንድ ወቅት ከCBE ሊወስደው በነበረ ብድር ከባንኩ አመራር ጋር መግባባት አቅቷቸው ነበር፡፡ ባንኩ ተቋሙን ብቻ ሳይሆን አገርን ይጎዳል በሚል በብድሩ ላይ አልስማማም አለ፡፡ ከዚያም ጀነራል ክንፈ ሁለት ወታደሮችን ወደ ባንኩ ዋና ስራ አስኪያጅ በመላክ ሳይፈርም እንዳይወጣ አሉ፡፡ ቢሮው ውስጥ ወታደሮች የነበሩት ስራ አስኪያጅ እስር ቤት ከሆነ እንሂድ አገሬ ላይ በደል አልፈፅምም ብሎ ምሳ ጋብዞ ሸኝቷቸዋል፡፡ ይህ አይነት አጋጣሚ የሜቴክና የብዙ ተሿሚዎች ገጠመኝ ነው ፡፡  ምርምርና የኢንዱስትሪ ልማት ገንዘብ ይፈልጋል፡ ገበያ ከሌለህ ደግሞ እንዲህ ትዋረዳለህ፡፡ እንግዲህ የሜቴክና የመንግስት ፍላጎት ተቃርኖ አንዱ ገበያ ነው፡፡ “እያመረትኩ ልማር ግዙኝ ÷ አይ አዘግይተሃል፡ ጥራት የለህም”
Filed in: Amharic