>
4:51 am - Friday July 1, 2022

ልቅለቃ ነዉ ፍቅፈቃ? (በፍቃዱ ሞረዳ)

ልቅለቃ ነዉ ፍቅፈቃ?
ፍቃዱ ሞረዳ
የለዉጥ ወቅት ይብዛም ይነስም አስቸጋሪ ነዉ፡፡ ብዙ ተዋንያን፣ ብዙ ተዉኔቶች…ይታያሉ፡፡ ወደፊት አንዳንዱን እንነቁራለን፡፡
አንዳንዴ ንፁህ ይቀጣና ወንጀለኛ ነፃ ይሆናል፡፡ አንዳንዴ ግንዱ ሥሩን አንሰራፍቶ ይቆምና ቅርንጫፉ ይቆረጣል፤ ይቃጠላል፡፡ ትዕዛዝ ሰጪዉ ተቀምጦ ትዕዛዝ ተቀባዩ ዕዳ ከፋይ ይሆናል፡፡
    የኢሕአዴግ መንግሥት ሰሞኑን በተለይም ኢሰብዓዊ ድርጊት ‹‹ ፈፅማችኋል›› ባላቸዉ አባሎቹና ሠራተኞቹ ላይ እርምጃ እየወሰደ ይገኛል፡፡ የምስጋናና የአድናቆት ጎርፍም እየፈሰሰለት ነዉ፡፡ እርምጃዉም፣ ጎርፉም አሪፍ ነዉ፡፡
       ሰሞኑን ከተያዙት የደህንነት ባለሥልጣናት መሐከል አንዱ ያሬድ ዘርይሁን ( ፎቶ የእርሱ ነዉ) ነዉ፡፡ የአቶ ጌታቸዉ አሰፋ ምክትል ነበር፡፡ ያሬድ የተያዘዉ ዱከም ሆቴል ዉስጥ ነዉ፡፡ ከቤቱ ወጥቶ ሆቴል የገባዉ እነማን መክረዉት፣ ‹‹እስቲ ለጊዜዉ ዘወር ብለህ ቆይ›› ብለዉት ዱከም እንደሄደ አንድ ቀን ራሱ ይነግረን ይሆናል፡፡
   ያሬድ ዛሬ የእርሱን ወንበር ከተረከቡት ከአቶ ደመላሽ ጋር   እስከተያዘበት ድረስ አርቦሽ ነበሩ፡፡ያሬድ፣ ‹‹ ጌታቸዉ አሰፋ አንድ ቀን ሊበላኝ ይችላል›› ብሎ  በስጋት ይኖር እንደነበር ማስረጃዎች አሉ፡፡ እና ዛሬ የያሬድ ስጋት የነበረዉ ሰዉ ‹‹ሕጋዊ ጥበቃ›› እየተደረገለት ፣የያሬድ የጦስ ዶሮነት ቢያነጋግር አይገርምም፡፡
    ሰዉን ለእነሕይወቱ ቆሼ ዉስጥ ሲቀብሩ የነበሩት እነወልደሥላሴ የት አሉ? በማዕከላዊ ምርመራ ማስተባበሪያ አናታችንን በሽጉጥ ሰደፍ ሲወቅጥ የነበረዉ የማዕከሉ ኃላፊ ታደሰ መሠረት አሁንም ተጀንኖ የሚቃጠል አሮጌ ብር ይጠብቃል? ብሔራዊ ባንክ ዉስጥ ፡፡ እንደደህና ሰዉ፡፡ ማን ያዉቃል እርሱም ዛሬ ‹‹የለዉጥ ኃይል ነኝ፤ ተደምሪያለዉ›› ብሎ ቢሆን፡፡ያኔ በሽጉጡ ሰደፍ አናቴን መዉቀሩ ሳይሆን፣ የተመታሁበትን ቦታ እንዳላሽ የከለከለኝ  አበሳጭቶኛል፡፡ ቁስሉ ሳይሆን ቁጭቱ አሁንም ያመኛል፡፡
    አሟሟቱ አወዛጋቢና ምስጢር ሆኖ የቀረዉ የሀገር ዉስጥ ደህንነት ባለስልጣን የታሪኩ ሶዶ ጉዳይ መቼ ነዉ ይፋ የሚወጣዉ? ደብረ ዘይት መንገድ ‹‹በመኪና አደጋ ሞተ›› ነዉ የተባለዉ፡፡ ሌላ ጉዳይም አለዉ፡፡
  በአጠቃላይ የእነአቢይ ኢሕአዴግ መንግሥት ሰሞነኛ እርምጃ ጥሩ ነዉ፡፡ ነገር ግን፣እዚያም እዚህም ያለዉን ግንድ ግንዱን ትቶ በቅርንጫፉ ላይ ማተኮር ግብረመልሱን ጥሩ ላያደርገዉ ይችላል የሚል ቅዱስ ስጋት አለ፡፡ ወይ መጀመሪያዉኑ እንደተባለዉ ያለፈዉን ምዕራፍ በይቅርታ ዘግቶ ወደፊት በድምር ወደፊት መቀጠል፤  አለያም ገጣሚዉ እንዳለዉ ‹‹ከማለቅለቅ፣ መፈቅፈቅ››ብሎ በእጁ ላይ የወገኑ ደምና ሀቅ ያለበትን ሁሉ ሰብስቦ ማጎር፡፡ (ግን ማን ሀገር ይመራል ያኔ?)
  ባለፉት ሃያ ምናምን ዓመቶች የተፈፀመዉ የሙስና ወንጀልም በክንፈ ላይ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀልም በያሬድ ላይ ደርሶ ይቆማል ወይስ ይቀጥላል? በያሬድ ላይ የሚቀርበዉን የወንጀል ክስ ለመስማት ቋምጫለሁ፡፡ ከወፈፌ ትፋት የሎስ ይታደገን፡፡
Filed in: Amharic