>
4:42 pm - Monday January 18, 5283

ሕወሓት እንደ ድርጅት የወንጀል እንጂ የፖለቲካ ድርጅት አይደለም!  (አቻምየለህ ታምሩ)

ሕወሓት እንደ ድርጅት የወንጀል እንጂ የፖለቲካ ድርጅት አይደለም!  

አቻምየለህ ታምሩ

እነ ጌታቸው አሰፋ  ለመስማት የሚቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ቢፈጽሙም  እንደ ባለ አለኝታ አድርጎ የሚቆጥር፤ 

* እነ ክንፈ ዳኘው  ኢትዮጵያን በአጽሟ ቢያቆሟት የታገሉት  ኢትዮጵያን ገፈው ትግራይን ለማልበስና የተስፋይቱን ምድር ለመመስረት ስለሆነ እንደ ትግራይ ባለውለታ የሚቆጥር ድርጅት እንጂ  እንደሰው በወንጀላቸው የሚያፍር፣ ጭካኔያቸው የሚከረፋው፣ ልቡ የሚሰበርና አንገቱን የሚደፋ ድርጅት አይደለም!

ይህ የወንጀል ድርጅቶ ከምስረታው ጀምሮ  የፈጸማቸው ዘግናኝ ወንጀሎች ለየወንጅል ድርጅትነቱ  ከበቂ በላይ ምስክሮች ናቸው። ለወንጀል በወንጀለኞች የተቋቋመው ይህ የአረመኔዎች ድርጅት በኢትዮጵያ ላይ ለፈጸመው ሽብር፣ ግድያ፣ ዘረፋና ክብረ ወሰን የተቀዳጀ የሰብዓዊ መብት ጥሰት  እንደ ድርጅት አለመታገዱና በሕዝብ ችሎት ፊት ለፍርድ አለመቅረቡ ሲገርመን  በንጹሐን ዜጎች ላይ ግብረ ሰዶም  የፈጸሙ፣ ሴቶችን እየተፈራረቁ የደፈሩ፣መርከብና አውሮፕላን የዘረፉ፣ ከኢራቅ የጦር መሳሪያ እየገዙ በሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ንግድ ላይ ተሰማርተው ምናልባትም ለአልሸባብ አይነት አሸባሩ ቡድኖች የጦር መሳሪያ ሲሸጡ የነበሩና አገራችንን ገፈው  ባጽሟ ያስቀሩ ዓለም አቀፍ ወንጀለኞቻችን ተነኩብን ብለው ከቀናት በፊት ራሳቸው ያወጡትን መግለጫ ተቃውመው በዛሬው እለት መግለጫ አወጡ አሉ።

ፋሽስት ወያኔ  የሚባለው የቅሚያ፣ የግድያና የግብረ ሰዶም ፈጻሚዎች ድርጅት ከቀናት በፊት ያወጣውን የራሱን መግለጫ ተቃውሞ መግለጫ ያወጣው ክንፈ ዳኘውን የሚባለውን ዘራፊ ሲሽሽ ሲል እጁን ይዞ ሰጠ እየተባለ የተነገረለት ዜናም ከትውስታችን ሳይጠፋ ነው። ፋሽስት ወያኔ ራሱ ያወጣውን መግለጫ በሌላ መግለጫ ተቃውሞ ውድቅ ሲያደርግ የዛሬው ሁለተኛው ነው። ነውር ጌጡ የሆነው ይህ  ወንጀለኛ ድርጅት ባለፈው ሐምሌ ወር ያለ አንዳች ተቃውሞ አዲስ አበባ ላይ አብሮ የወሰነውን «የኢሕአዴግ» ውሳኔ መቀሌ ላይ ባደረገው ጉባኤው ተቃውሞ መግለጫ አውጥቶ ነበር። ከቀናት በፊት ያወጣውን መግለጫ በመቃወም ዛሬ ባወጣው መግለጫ የነውረኛነትን ክብረ ወሰን ሰብሯል።  በዚህም ከሽፍትነት ወደ «መንግሥትነት» የተለወጠው ይህ የማፍያ ቡድን  ባለም ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሚባል አኳኋን ከቀናት በፊት ያወጣውን የራሱን ድርጅታዊ ውሳኔ ለሁለተኛ ጊዜ ተቃውሞ መግለጫ  ያወጣ ብቸኛው ድርጅት ለመሆን በቅቷል።

ኢትዮጵያን ለሀያ ሰባት ዓመታት በብቸኛነት ሲገዛና በኢትዮጵያ ምድር የሲኦልን በር በርግዶ በመክፈት አገራችንን ምድራዊ ገሀነም ሲያደርጉ የኖሩት፣ አገር የገፈፉት እነ  ጌታቸው አሰፋ ወይንም ክንፈ ዳኘው  ብቻ አይደለም! በኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመው ዓለም አቀፍ ወንጀል የተፈጸመው  ለወንጀል በተቋቋመው ሕወሓት ነው። ሕወሓት ሳያውቀው፣ ሕወሓት ሳይመክርበትና ሕወሓት እንዲፈጸም ትዕዛዝ ሳይሰጥ በኢትዮጵያ ሰማይ ስር የተፈጸመች አንዳች ወንጀል የለችም። ለዚህ ከደብረ ጺዮን መግለጫ በላይ ምስክር የለም! ደብሪቱ  ከቀናት በፊት ያወጣውን መግለጫ ተቃውሞ  በዛሬው እለት መግለጫ ያወጣው የወንጀል ግብረ አበሮቹ በመታሰራቸው ነው። ሱሌይማን ደደፎ በቴሌኮሙኒኬሽን ኮርፖሬሽን  «ሜቴክ ማረኝ የሚስብል  ወንጀል ተሰርቷል» ሲል ሰምተነዋል። ሜቴክ ማረኝ የሚያስብል ወንጀል የሰራውን ቴሌን ሲመራ የነበረው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የኢኮኖሚና ፋይናንስ ክላስተር አስተባባሪና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር  የነበረው ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ነው። ስለዚህ ደብሪቱ እነ የጌታቸው አሰፋንና የክንፈ ዳኘውን  ወንጀል ቢከላከል የወንጀል ማኅበርተኛቸው ስለሆነ ነው።

ባጠቃላይ ፋሽስት ወያኔ እንደ ድርጅት  እነ ጌታቸው አሰፋ  ለመስማት የሚቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ቢፈጽሙ  እንደ ባለ አለኝታ አድርጎ የሚቆጥር፤ እነ ክንፈ ዳኘው  ኢትዮጵያን በአጽሟ ቢያቆሟት የታገለው  ኢትዮጵያን ገፈው ትግራይን ለማልበስና የተስፋይቱን ምድር ለመመስረት ስለሆነ እንደ ትግራይ ባለውለታ የሚቆጥር ድርጅት እንጂ  እንደሰው በወንጀላቸው የሚያፍር፣ ጭካኔያቸው የሚከረፋው፣ ልቡ የሚሰበርና አንገቱን የሚደፋ ድርጅት አይደለም።  ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ የፍትሕ ሂደት እየተጀመረ ከሆነ  አቃቢ ሕጉ ብርሀኑ ጸጋዬ እንዳለው በመንግሥትነት ተሰይሞ የሽብር ስራ ሲፈጽም የኖረው  አሸባሪው ፋሽስት ወያኔ  እንደ ድርጅት  ተግባሩን በሚመጥነው በአሸባሪነት ተፈርጆ  በዓለም ወንጀለኞች ችሎት ለፍርድ መቅረብ አለበት።

Filed in: Amharic