>

መብራትን ያለገመድ (Wi-Power) ያስቻለ ኢትዮጵያዊው ጥበበኛ ተማሪ ! (ይድነቃቸው ከበደ)

መብራትን ያለገመድ (Wi-Power) ያስቻለ ኢትዮጵያዊው ጥበበኛ ተማሪ !
ይድነቃቸው ከበደ
ሀምዛ መሐመድ ይባላል፡፡ በጎንደር ዩንቨርስቲ የኤሌክትሪካልና የኮምፕዩተር ምህንድስና የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ ነው፡፡ ሐምዛ ገመድ አልባ ኤሌክትሪክን ፈልስፎ እንካችሁ ብሎናል፡፡ ይሄን መስራት በጣም ቀላል እንደሆነ ነው ሃምዛ የሚናገረው፡፡ ይሄ ባለተስጥኦ ተማሪ ገመድ አልባ ሃይሉን በራሱ ትራንስፎርመር እንዴት ማስተላለፍ እንዳለበት ነው እንጂ እያሳሰበው ያለው ገመድ አልባ ሃይሉን መፍጠር ግን ቀላል እንደሆነ ነው የሚገልፀው፡፡
ሐምዛ በተግባር ብዙ ኪሎሜትሮችን አቋርጦ ያለገመድ የመብራት ሃይል ማግኘት እንደሚቻል በተግባር ሠርቶ አሳይቷል፡፡ አሁን ዋናው ነገርና ቁልፉ ጉዳይ ያለው በመንግስትና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እጅ ነው፡፡ ምክንያቱም ልጁን በገንዘብ ከደገፍነው ከ80 ሚሊየን ህዝብ በላይ ከጨለማ ያወጣል ሲሉ የዩንቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ በግል ገፃቸው በlinkedin የማህበራዊ ድረገፅ ይናገራሉ፡፡
የሀምዛ ገመድ አልባ የመብራት ሃይል ፈጠራው በኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ፅ/ቤት የባለቤትነት ምዝገባውን ለማግኘት በሂደት ላይ ነው፡፡ አንድን የአዕምሮ ፈጠራ ለመመዝገብ ቢያንስ ለ6 ወር መጠበቅ ስላለበት የባለቤትነት መብቱ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ውስጥ ይመዘገባል ሲሉ የዩንቨርስቲው ፕሬዝዳንት አስተያየታቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ ፕሬዝዳንቱ አክለውም በሃምዛ በራሱ የተሠራው ትራንስፎርመር እስከ25 ኪሎ ሜትር ድረስ ኤሌክትሪክ ሃይል መስጠት የሚያስችል እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ ይሄም በዓለም ላይ ያለውን ከ3 እስከ 5 ሜትር የሆነውን የገመድ አልባ የኤሌክትሪክ ሃይል በብዙ እጥፍ የሚያሻሽል ነው፡፡
እንደሀምዛ ዓይነት አዳዲስ የቴክኖሎጂ ፈጣሪዎች እንዲበዙልን ሁሉም የድርሻውን ይወጣ!
ምንጭ፡- ከጎንደር ዩንቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ደሳለኝ መንገሻ የግል linkedin ገፅ
Filed in: Amharic