>

ለትርጉም ክፍት የሆኑ የጠ/ምኒስትሩ አደገኛ ንግግሮች...!!! (ዮናስ ሀጎስ)

ለትርጉም ክፍት የሆኑ የጠ/ምኒስትሩ አደገኛ ንግግሮች…!!!
ዮናስ ሀጎስ
*  «ዋና ዋናዎቹ» ላይ ብቻ የሚያተኩር የእስር ዘመቻ
* «የቀን ጅብና ካንሰር» ማንን እንደሚወክሉ መግባባት ላይ ያልተደረሰባቸው
ዶክተር አቢይ አሕመድ ዛሬ ፓርላማ የወ/ት ብርቱኳንን ሹመት ለማስፀደቅ በተገኙበት ወቅት ባደረጉት ንግግር የሙስና ዘመቻው «ዋና ዋናዎቹ» ላይ ብቻ እንደሚያተኮርና ሁሉም ይታሰሩ ከተባለ ከኢህአዴግ አባላት በሙስና ያልተነካካ ማግኘት አዳጋች እንደሆነ በግልፅ ተናግረዋል።
•°•
ከ«ዋና ዋናዎቹ» ውጭ ያሉት ሙሰኞች እንደየደረጃቸው ወደፊት በሚቋቋም የእርቅ ኮሚሽን አማካይነት ከሕዝብ ጋር የሚታረቁበት መንገድ ይፈጠራልም ብለዋል።
•°•
አሁን አነጋጋሪው ጉዳይ «ዋና ዋናዎቹ» የተባሉት እነማን ናቸው የሚለው ጥያቄ ነው። በቢልዮን የሰረቁትን አስረን በሚልዮን የሰረቁትን ከሕዝብ ጋር ልናስታርቅ ይሆን ሐሳቡ? ወይንስ ዶክተር ደብረፅዮን እንዳለው የሙስና ዘመቻው የተለየ ብሔርን ብቻ ታርጌት ያደረገ ሆኖ ሊጠናቀቅ ነው?
•°•
የሙስና ወንጀል በይዘቱ በጣም አነካኪ ነው። በተለይ መንግስታዊ በሆኑ ተቋማት ውስጥ አንድ የሙስና ወንጀል ለመስራት ቢያንስ ከተቋሙ ሶስትና አራት ሰው ተሰተፊ ሊሆን ይገባል። ደላላውንና ሙስና የሚሰራለትን ባለኃብት ስንጨምር ቁጥሩ እየጨመረ ይሄዳል ማለት ነው። የሙስናው ገንዘብ እየጨመረ በሄደ ቁጥር ደግሞ የተሳታፊው ቁጥርም እየጨመረ መሄዱ አይቀርም።
•°•
እንደ ሜቴክ ላሉ በቦርድ የሚተዳደሩና ረዘም ላሉ ዓመታት የሙስና ሰለባ የሆኑ ተቋማት ቢያንስ ከሰራተኞቻቸው ሩብ የሚሆኑት ባንድም ሆነ በሌላ መልኩ ሙስናው ውስጥ እያወቁም ሆነ ሳያውቁ አሊያም ተገድደው ተሳታፊ የመሆናቸው ጉዳይ እርግጥ ነው። በሜቴክ ጉዳይ የቀረበው ዶኪዩመንታሪ ላይ የቀረቡት ጉዳዮች በሙሉ በክሱ ላይ ተካትተዋል ቢባል እንኳ ከ1000 በላይ ተከሰሾች ሊኖሩ በተገባ ነበረ።
•°•
እውነታው ግን የተከሰሱት ቁጥራቸው 100 ካለመሙላቱም በላይ ሜቴክን በቦርድ አመራርነት ሲመሩት ከነበሩት ሰዎች አንዳቸውም በቁጥጥር ስር አልዋሉም። ምክትል ጠ/ሚ/ር ደመቀ መኮንን ለስድስት ወራት ያህል፣ የቀድሞው መከላከያ ሚንስትር ሲራጅ ፈርጌሳ ዘለግ ላሉ ዓመታት የሜቴክ የቦርድ ሊቀመንበር ሆነው ማገልገላቸው ይታወቃል።
•°•
ደጋግሜ እንደምለው የአቢይ አንደኛውና ትልቁ ችግር ነገሮች ሁሉም ደስ ባለው መንገድ እንዲተረጉማቸው አድርጎ ለሕዝቡ የሚበትነው ጉዳይ ነው። «የቀን ጅብና ካንሰር» ብዙ የተባለባቸው ማንን እንደሚወክሉ በደንብ መግባባት ላይ ያልተደረሰባቸው ብዙ ጉዳት ያደረሱ ገለፃዎቹን እናስታውሳለን። አሁን ደግሞ የሙስና ዘመቻው የተወሰኑ አካላትን ብቻ እንደሚያካትት የገለፀበት የዛሬው ንግግሩ ማንን አካትቶ ማንን እንደሚተው ግልፅ የሆነ ነገር ያላስቀመጠበት መሆኑ ችግሩን የበለጠ እያባባሰው ይሄዳልና ቢታሰብበት መልካም ይመስለኛል።
Filed in: Amharic