>

የምስጋና እና የስጦታ ቀን!!! (ዳዊት ከበደ ወየሳ)

የምስጋና እና የስጦታ ቀን!!!
ዳዊት ከበደ ወየሳ
ከበአላት ሁሉ የአሜሪካኖቹ Thanksgiving ወይም የምስጋና ቀን እጅግ የሚያስደስት በአል ነው። ሰው ከቤተሰብ እና ከጓደኞቹ ጋር በመሆን አምላኩን ያመሰግናል፤ በህይወቱ መልካም ነገር ያደረጉለትንም ሰዎች እንዲሁ የሚያመሰግንበት በዓል ነው። ይህ በአል ከ እሮብ ማታ ጀምሮ እስከ መጪው እሁድ ድረስ በድምቀት ይከበራል። ከአንደኛው ስቴስ ወደሌላው ዘመድ ለመጠየቅ የሚሄዱ መንገደኞች ዋናውን ጎዳና እና የአየር ማረፊያ ጣቢያዎችን ያጨናንቃሉ። ፕሬዘዳንቱም በኋይት ሃውስ ሊታረዱ ከተዘጋጁት ተርኪ ዶሮዎች መካከል ለአንዱ ምህረት ያደርጋል። ፕሬዘዳንት ኦባማም በትላልንቱ እለት ለአንድ ተርኪ ምህረት አድርገዋል። ድሆችንም በመጎብኘት እለቱን አሳልፈዋል። በየቤተክርስቲያኑም ነጻ ምግብ የሚሰጥበት፤ ለልጆችም ነጻ መጫወቻ በየከተማው የሚበረከትበት እለት ነው – የምስጋና ቀን።
ቫለንታይንስን ጨምሮ… ኢትዮጵያ ውስጥ የአሜሪካ በአላት በጉራማይሌ መልክ  ሲከበሩ ይህ በአል ለምን እስካሁን እንዳልተከበረ አላቅም። አንድ የማውቀው ነገር ቢኖር፤ በአሉ በአሜሪካ ኢምባሲ ውስጥ በድምቀት እንደሚከበር ነው። ኢትዮጵያ በነበርኩበት ወቅት በተደጋጋሚ በኢምባሲው ውስጥ 4th of July እና የምስጋና ቀንን አክብሬያለሁ። ሆኖም አሁን አሜሪካ ውስጥ ሆኜ ሳከብረው የሚሰማኝ ስሜት የተለየ ነው።
የበአሉ ታሪካዊ አመጣጥ እንዲህ ነው። የዛሬ 400 አመት አካባቢ… አሜሪካዊያን ተርበው በሞት አፋፍ ላይ በነበሩበት ወቅት፤  እንደጠላት አይተው እያደኑ የሚገድሏቸው “ሬድ ኢንዲያንስ” ተርኪ ዶሮ፣ የበቆሎ እሸት እና ሌላም ምግብ መኖሪያ ሰጥተው የአሜሪካውያኑን ህይወት አተረፉ። ይህ ያልታሰበው የሬድ ኢንዲያንስ መልካም ተግባር አሜሪካዊያንን አስገረመ፣ አስደነቀ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አሜሪካዊያን ይህንን በአል በየአመቱ እየተሰባሰቡ፤ አምላካቸውን እና መልካም ነገር ያደረጉላቸውን ሰዎች በማመስገን ያከብሩት ጀመር። በመጨረሻም ከ1789 ጀምሮ በህግ የአሜሪካዊያን በአል ሆነ። (ካናዳ ውስጥ ኦክቶበር ላይ ነው የሚከበረው)
ከበአላት ሁሉ የሚወደድ በአል የሚያደርገውም ቤተሰብ፣ ዘመድ አዝማድ እና ጓደኛሞች አብረው ማክበራቸው ብቻ ሳይሆን ምስጋና ማቅረባቸው ነው። በርግጥ ለምናምነው አምላክ በየቀኑ ምስጋና ማቅረብ መልካም ሆኖ ሳለ፤ በአመት አንድ ጊዜ ደግሞ እንዲህ ተሰባስቦ ምስጋና ማቅረቡ የሚከፋ አይደለም። እናም ኢትዮጵያውያን ይህንን በአል ስታከብሩ… በዚህ ቀን በህይወታችሁ መልካም ያደረገላችሁን አምላክ እንደየሃይማኖታችሁ ማመስገን እንዳለ ሆኖ፤ ጥሩ የሰሩላችሁንም ሰዎች አስቧቸው።
አሜሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ እንድትመጡ የረዷችሁን፣ ከመጣችሁ በኋላ ያስተናገዷችሁን… በአጠቃላይ በህይወታችሁ መልካም ያደረጉላችሁን ሰዎች አመስግኑ።
እኔም ከምግብ እና ከመጠጡ በፊት ለሚቀጥሉት ጥቂት ደቂቃዎች በህይወቴ መልካም ነገር ያደረጉልኝን ሰዎች አስባቸዋለሁ። የነሱ ድጋፍ እና እርዳታ ባይታከልበት ኖሮ ህይወት አስቸጋሪ ልትሆን ትችል እንደነበር አስባለሁ። በትምህርት ቤት እና በስራ ዘመኔ አብረውኝ የነበሩ መልካም ትዝታዎች አስታውሳለሁ። ለዚህ ቀን በመድረሴም እራሴን እደለኛ አድርጌ በመቁጠር አምላክን አመሰግናለሁ። መልካም ያደረጉልኝ ሰዎችን ፈጣሪ ከነቤተሰባቸው እንዲባርክ እጸልያለሁ። ከዚያም ለነዚህ ሰዎች በመደወል፣ በኢሜይል ወይም በቴክስት “እንኳን አደረሳችሁ” እላለሁ። ከዚያ በፊት ግን… ለመላው የፌስ ቡክ ጓደኞቼ “እንኳን ለምስጋና ቀን አደረሳችሁ” ልበል። መልካም የምስጋና በአል ወዳጆቼ።
Filed in: Amharic