>
7:50 am - Tuesday August 9, 2022

የሹም ሽር ፖለቲካ ሁነኛ የሀይል ሚዛን ማሳያ!!! (በፍቃዱ ዘ. ኃይሉ)

የሹም ሽር ፖለቲካ ሁነኛ የሀይል ሚዛን ማሳያ!!!

 

በፍቃዱ ዘ. ኃይሉ

 

የሹም ሽረት ፖለቲካ በኢትዮጵያ የትኞቹ ወገኖች ሥልጣን እየተቆጣጠሩ፣ የትኞቹ ወገኖች ደግሞ ሥልጣን እያጡ እንደሆነ የሚያመላክት የኃይል ሚዛን ማሳያ ነው፡፡ ባለፉት ሰባት ወራት ሹም ሽረት የፖለቲካ ለውጡ ዋነኛ ማሳያ ሆኖ ከርሟል፡፡ በትላንትናው ዕለት ብርቱካን ሚደቅሳ ለምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ተደርገው መሾማቸው የዚህ ትዕይንት ሁነኛ ማሳያ ነው፡፡

የቀድሞዋ ዳኛ፣ የተቃዋሚ ድርጅት አመራር፣ የፖለቲካ እስረኛ እና ኋላም ስደተኛ የነበሩት ብርቱካን ሚደቅሳ ሹመት ከሌሎች ቀደምት ሹመቶች በጉልህ የሚለይበት ነገር አለ፡፡ የ1997ቱ አገር ዐቀፍ ምርጫ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ዋነኛ መታጠፊያ ነበር፡፡ ከዚያ ቀደም የነበሩ አንፃራዊ ነጻነቶች በሙሉ ከዚያ በኋላ ታፍነው ከርመዋል፡፡ ብርቱካን የ1997ቱ ምርጫ ላይ ግንባር ቀደም ከነበሩት ተዋናዮች እንዲሁም በምርጫው ውጤት ባለመግባባት ቀውስ ከተፈጠረ በኋላ የቅንጅት ለአንድነት እና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (ቅንጅት) ፈርሶ በመሥራቾቹ “የቅንጅት የሞራል ወራሽ” የተባለለት አንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትሕ (አንድነት) ፓርቲ ሲመሠረት የመጀመሪያዋ መሪ ነበሩ፡፡ እርሳቸው የምርጫ ቦርድ መሪ ተደርገው መሾማቸው፤ ምንም እንኳን ላለፉት ዓመታት ለየትኛውም የፖለቲካ ኃይል ወገንተኝነት ሳያሳዩ የቆዩ ቢሆንም፤ በአንድ ወቅት ለስርዓቱ አደጋ የሚባሉ ሰዎች አሁን እየተመሠረተ ላለው ስርዓት ዋልታ እየሆኑ መምጣታቸውን ቀድሞ እያመላከተ ይመስላል፡፡

ምስለ “አዲሷ ኢትዮጵያ”

በቅርብ ጊዜ የተሾሙት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት መዓዛ አሸናፊ አዲሷን የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ – ብርቱካን ሚደቅሳን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውስጥ ቃለ መኃላ ሲያስገቧቸው የነበረውን ትዕይንት “የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ምስል ይህ ነው” በሚል የገለጹት ሰዎች አሉ፡፡ መዓዛ አሸናፊም እንደ ብርቱካን ከለውጡ በፊት በነበረው ስርዓት የተገለሉ ሴት ነበሩ፡፡ የአሁኗ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት የመሠረቱት የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር (EWLA) ከ1997ቱ አወዛጋቢ ምርጫ በኋላ ከወጡት አፋኝ ሕግጋት አንዱ በሆነው – በበጎ አድራጎት እና ማኅበራት አዋጅ – ምክንያት የገቢ ምንጩን ተነጥቆ ቀድሞ ከነበረው አቅም እጅግ ባነሰ የፋይናንስ አቅም እንዲሠራ የተገደደ ድርጅት ነበር፡፡

ሁለቱ የሕግ ባለሙያዎች እምቢተኞች እንዲሁም ለስርዓቱ ተገዳዳሪ የነበሩ ብርቱ ሴቶች ናቸው። አንዷ መሐላ ፈፃሚ፣ ሌላኛዋ አስፈፃሚ ሆነው በሕዝብ ፊት ሲታዩ በአንድ ላይ በርካታ መልዕክቶች ተላልፈው ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በጠንካራ ውሳኔ ሰጪነታቸው የሚታወቁ ሴቶች ቁልፍ የመንግሥት የኃላፊነት ቦታዎችን እየወሰዱ ነው – ይህ እውነት በዚህ ክስተት ታይቷል፡፡ ቀድሞ የስርዓቱ ተቃዋሚ በመሆናቸው የተገለሉ እና የተንገላቱ ሰዎችም እንዲሁ የተለያዩ ቁልፍ የኃላፊነት ቦታዎችን እየወሰዱ ነው – ይህም በዚህ ምስል ውስጥ ታይቷል፡፡

የሹም ሽረት መራር እውነታ

በኢትዮጵያ እየተካሔደ ያለውን የለውጥ ሒደት ምንነት እና አቅጣጫ በቅጡ ለማስረዳት የሚያስችል ግልጽ ፍኖተ ካርታ በሌለበት በዚህ ጊዜ ሹም ሽረቱን እንደመከታተል “የአዲሲቷን ኢትዮጵያ” ገጽታ የሚነግረን ሌላ ነገር የለም፡፡ ይሁን እንጂ የሹም ሽረት ፖለቲካ ሥር ነቀል ለውጥ መምጣቱን ለማረጋገጥ ዋስትና አይሆንም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ አሊያም ደግሞ እርሳቸው የሚመሩት የሚኒስትሮች ካቢኔያቸው ለውጡን እያስኬዱ ያሉት፣ ለውጡን ያስገደደውን ሕዝባዊ አመፅ ለመቀስቀስ በበቃው የችግር ፈጣሪ አካሔድ ነው፡፡ ሹመቶችም ይሁኑ ሽረቶች በድብቅ “ላይ ቤት” ይጠነሰሳሉ፣ ለይስሙላ በሚመስል መልኩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በመፅደቅ ለብዙኃኑ እንደ ጠበል ጣዲቅ በሰበር ዜና ይዳረሳሉ፡፡ በድግሱ ላይ ሕዝብ የሚመክርበት ዕድል ዛሬም እየተሰጠው አይደለም፡፡

በለውጡ ስርዓት ወይም አካሔድ ላይ ተስፋ የሚጣልባቸው አካሔዶች አሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ የአፋኝ ሕግጋት እና መመሪያዎች ክለሳ ዋነኛው ነው፡፡ ይህም ቢሆን የሕግ እና ፍትህ ጉዳዮች አማካሪ ጉባኤ እና በሥሩ ያሉት የሥራ ቡድኖች አባላት አመራረጥ ላይ ግልጽነት የጎደለው ነው፡፡ ይሁን እንጂ የተመደቡት ሰዎች አወዛጋቢ ባለመሆናቸው እና በሙያቸውም የተመሠከረላቸው በመሆናቸው ቅሬታ አልተነሳም፡፡ ለውጡ ከሚጠይቀው ጥድፊያም አንፃር ጉዳዩ ተቀባይነት ሊኖረው ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ የሥራ ቡድኑ እነዚህ መከለስ አለባቸው ብሎ የሚያቀርባቸው የሕግ እና መመሪያ ማሻሻያ ጥቆማዎች በፊት ሹም ሽረቱ መቅደሙ ችግር ሊፈጥር ይችላል፡፡

ለምሳሌ ይህል የብርቱካን ሚደቅሳ ሹመት የምርጫ ሒደቶችን ያውካሉ ተብለው የሚታመኑ ሕጎች ለክለሳ እየተጠኑ በሉበት ወቅት የተፈፀመ ነው፡፡ ይህ አካሔድ የቅደም ተከተል መዛባት ያስከተለ ይመስላል፡፡ ብርቱካን በብዙኃን ዘንድ ለሕግ ታማኝ በመሆናቸው እና በተጋፋጭነታቸው የሚታወቁ ሰው እንደመሆናቸው ለተሾሙበት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢነት የገዘፈ እንጂ ያነሰ ተክለ ሰብእና እንደሌላቸው መታወቁ በብዙኃን ዘንድ የጎላ ቅሬታ አላስከተለም፡፡

ሹም ሽረቶች ብዙኃኑን ያላስማሙ በሚሆኑበት ጊዜ ገላጋይ ሆኖ የሚቀርበው ተቀባይነት ባለው ወይም ፍትኃዊ ሕግ በሚያስቀምጠው የሥነ ስርዓት አግባብ፣ ሕዝባዊ ቅቡልነት ያለው ምክር ቤት ሲያፀድቀው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በምሥጢር ሳይሆን ይፋዊ ሕዝባዊ ውይይት ያስፈልጋል፡፡ ይህ አለመሆኑ ሹም ሽረቶቹ የኃይል ሚዛኑን መለወጥ የሚነግሩንን ያህል፣ ነገሮች ከሥር መሠረታቸው ወደ ዴሞክራሲያዊነት እየተለወጡ መሆን አለመሆኑን ማረጋገጥ እንዳይችል አድርጎታል፡፡ ይህም በፅናታቸው እና አቋመ ብርቱነታቸው ለሚታወቁት እንደ ብርቱካን እና መዓዛ ያሉ አዳዲስ ተሿሚዎች ከባድ ፈተና ከፊታቸው ያስቀምጣል፡፡ አዳዲሶቹ ተሿሚዎች በሚመሯቸው ተቋማት ውስጥ ያሉ የለውጥ ሒደቶችን በተለመደው የኢሕአዴግ የተማከለ ዴሞክራሲ ሥነ ስርዓት በምሥጢር መክረው ውጤቱን ይፋ ያደርጋሉ ወይስ የሕዝብን ተሳትፎና ይሁንታ በሚያረጋግጥ ግልጽ አካሔድ ሥራቸውን ያከናውናሉ? መልሱን በጊዜ ሒደት እንመለከታለን፡

Filed in: Amharic