>

ይድረስ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቻችን የነፃነት ቀንዲሎቻችን!!! (ከአፈንዲ ሙተቂ)

ይድረስ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቻችን የነፃነት ቀንዲሎቻችን!!!
ከአፈንዲ ሙተቂ
እናንተ ማለት የሀገሪቷ ዐይን ናችሁ። እናንተ የሀገሪቷ የወደፊት ተስፋዎች ናችሁ። ሀገራችን ከየትኛውም ዜጋ በላይ ትፈልጋችኋለች።
ባለፉት 27 ዓመታት ጨቋኙን ስርዓት በመቃወም ለተደረጉት ንቅናቄዎች ሁሉ እንደ እርሾ ሆኖ ያገለገለው በዩኒቨርሲቲዎቻች የተሰሙ የተቃውሞ ድምጾች ናቸው። በተለይም ባለፉት ሶስት ዓመታት በተከታታይ የታዩት ህዝባዊ ንቅናቄዎች ሁሉ መነሻቸው እናንተ ያሰማችኋቸው የተቃውሞ ድምጾች ናቸው። የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል የሚወክሉ ጥያቄዎችን በማንገብ የጨቋኙ ስርዓት የጸጥታና የአፈና መዋቅሮችን በግንባር እየተጋፈጣችሁ ለህዝባችሁ ነፃነት የከፈላችሁት መስዋእትነት በታሪክ ዘወትር ሲታወስ የሚኖር ነው።
 እነሆ የፈጣሪ ፈቃድ ታክሎበት በትግሉ ሂደት ያፈሰሳችሁት ደም የነፃነት አዝመራ ሆኖ በየማዕዘናቱ እየበቀለ ይገኛል። በብዙሃኑ የሀገራችን ዜጎችና በዓለም ዙሪያ ባሉት የእኩልነት እና የነፃነት ዘማሪዎች እንደተመሰከረው በእናንተ ፊታውራሪነት ለትግሉ የተነቃቃው ህዝባችን ጨቋኙን ስርዓት አፈራርሶ ለራሱ የሚፈልገውን መንግስት በምርጫ ከሚሰይምበት ዋዜማ ላይ ደርሷል።
—–
ይህ በብዙዎች ትግልና መስዋእትነት የመጣው የነፃነት አየር እና የዲሞክራሲ ሽታ ስር ሰዶ ሀገራችንን ወደ እድገት እና ብልፅግና ጎዳና እንዲመራት ከተፈለገ መላው የሀገራችን ህዝብ አንድ ልብ ሆኖ የለውጥ ሂደቱን መጠበቅ ይኖርበታል። በዚህ ረገድ ከፍተኛ ሃላፊነት የተጣለው ደግሞ የነፃነት ቀንዲሎቻችን በሆናችሁት በእናንተ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎቻችን ላይ ነው። በተለይም የለውጥ ሂደቱን አደናቅፈው የድሮውን የአፈና ስርዓት ሊመልሱብን የሚፈልጉት ማጅራት መቺዎች በየአካባቢው የሚለኩሷቸውን የግጭት እሳቶች በማጥፋት የለውጡ ጠባቂ ጋሻ እና መከታ የመሆን የዜግነት ግዴታ አለባችሁ።
ስለሆነም ማጅራት መቺዎቹ በያላችሁበት ግቢዎች በሰገሰጓቸው ጀሌዎቻቸው አማካኝነት የሚሸርቡትን የተንኮል፣ የጥላቻ እና የግጭት ሴራ ሁሉ በጥንቃቄ በማክሸፍ አብዮታችሁን ከቅልበሳ እንድትጠብቁት የአደራ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ።
—-
አፈንዲ ሙተቂ
ኢኮኖሚስት እና የኢትኖግራፊ ተመራማሪ
Filed in: Amharic