>

ገጠሬነት ላይ ጎሰኝነት ሲጨመር!!! (ሳምሶም ጌታቸው)

ገጠሬነት ላይ ጎሰኝነት ሲጨመር!!!
ሳምሶም ጌታቸው
ዳኛቸው አሠፋ (ዶ/ር) በቅርቡ በአንድ መድረክ ላይ ተገኝተው እንደተለመደው አንድ ጥሩ ንግግር አድርገው ነበር። ንግግራቸው ስለ ከተሜነት ነው። በግርድፉ፦ የከተማ ልጅ መሆን በራሱ ተጠቃሚ ያደርግሃል። ታክሲ ስትሰለፍ፥ ስትሳፈር፣ ከረዳቱ ከሹፌሩ፣ መንገድ ስትጓዝ፦ ከእግረኛው፥ ከባለመኪናው፥ ከመንገድ ላይ ቸርቻሪው፣ በየአገልግሎት መስጫው፣ ብቻ በየደረስክበት ከሰዎች ጋ የመደራደር፣ የመነጋገር፣ የመዋዋል (negotiate) የማድረግ ዕድሉን በየቀኑ፥ በየቦታው ይሰጥሃል።
በተቃራኒው ሩቅ ገጠር የሚኖር አብዛኛው ሰው ደግሞ ከብዙ ሰዎች ተግልሎና ርቆ ይኖራል። ከገጠር ተነስቶ ከተማ ወይም ወደ ሌላ ቦታ ለመጓዝ ደግሞ በትንሹ ከ20 እና 30 ኪ/ሜትሮች በላይ ዱላውን ወይም ጦሩን በትከሻው አጋድሞ፣ ፀጥ ብሎ በጫካ ውስጥ ብቻውን መንገዱን ያስነካዋል። በዚህ መሃል እባብ ቢያጋጥመው በያዘው ዱላ ጭንቅላቱን ብሎ መንገዱን ይቀጥላል። እንዲሁ ሌላም የዱር አውሬ ከመጣበት ጫካ ለጫካ አሯሩጦ በዱላው አናቱን ብሎ ይገድላል ወይም ያባርራል። There is no negotiation. ድርድር፣ መነጋገር የሚባል ነገር አያውቅም። ዱላ ነው ቋንቋው።” ብለው ታዳሚውን ሁሉ አስቀውት ነበር።
***
ዶ/ር ዳኛቸው ካሉት በተጨማሪ የከፋው ነገር የሚመጣው ደግሞ ገጠሬነት ላይ እርኩሱ ጎሰኝነት ሲታከልበት ነው። ከጅምሩ ጥቂት ሰዎችና ከብቶቹን ብቻ ለሚያውቅ፣ ከቴክኖሎጂ ርቆ ለሚኖር ሰው መንደሩ አለም ትመስለዋለች። እዚያ ላይ ጎሰኝነት ሲታከልበት የእሱ ቋንቋ የመልዓክት መግባቢያ፣ የእናቱ የጠላ ማሰሮ የእግዜር ፅዋ ይመስለዋል። ከእሱ ምርጥ ዘር ውጭ ያለው ሌላው ሰው ሁሉ ምራጭ እና እሱን ለማጣበብ የተፈጠረ አረም ነው ብሎ ያስባል፣ ስለዚህ ለሁሉም ነገር ዱላውን ይስባል። ገጠሬነት ላይ ጎሰኝነት ሲደመር ገጠሬው በዱላው የሚያናግረው “የአውሬ” አይነት በዛለት ማለት ነው። የምን መወያየት ነው? ማስወገድ፣ መግደል፣ ፀጥ ማድረግ ከጭቅጭቅ የመገላገያ ፍቱን መፍትሔ እያለ ብሎ ያስባል።  ስለሆነም መግባቢያ ቋንቋውን ዱላ ያደርጋል። ወይ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ¡ ያሳፍራል።
Filed in: Amharic