>

ድሮና ዘንድሮ!!! (ዮሀንስ ደጉ)

ድሮና ዘንድሮ!!!
ዮሀንስ ደጉ
ድሮሮሮሮሮሮ…..
ሐበሻ ሆነህ ዮኒቨርስቲ ከገባህ ያመልኩሃል፡፡ ያጨበጭቡልሃል፡፡ ያደንቁሃል፡፡ ጀለስካዎች ይቀኑብሃል፡፡ ጸዴ፥ የተማረች፥ የተቀሸረች ቸከስ ትጠብሳለህ፡፡ ላይፍ ይገባሃል፡፡ ራስህን ትችላለህ፡፡ ሰው አያነብልህም፡፡ በአውራ ጣትህ አትፈርምም፡፡ ፈረንጅ ማውራት ትችላለህ፡፡ ፖለቲካ ታውቃለህ፡፡ የመንግስት ስራ ትይዛለህ፡፡ ኮት ትገዛለህ፡፡ ምናምን ምናምን ብለው ያስባሉ፡፡
ቤተሰቦችህ ደረታቸውን ይነፋሉ፡፡ እህቶችህ የመጠበሻ ክላሳቸው ከፍ ይላል፡፡ ወመኔው ወንድምህ በስምህ ተበድሮ ያጨሳል፡፡ የሰፈሩ ቅያስ በስምህ ይጠራል “ያ ዮኒቨርስቲ የገባው ጨዋ ልጅ ቤት ጋ” ምናምን ነገር፥ የሰፈሩ ሼባዎች ያከብሩሃል፥ ወመኔ ጀለሶችህ በሹክሹክታ ያሙሃል፥ የተለየ ወጥ ይሰራልሃል፥ ትኩስ እንጀራ ይቀርብልሃል፡፡ ትከበራለህ፡፡
የዋለልኝን አርቲክል ታነባለህ፡፡ ጥላሁን ግዛው ይናፍቅሃል፡፡ መንግስትን ትጠላለህ፡፡ ቦርጫም ቢሮክራት ይደብርሃል፡፡ ፀጉርህን ታጎፍራለህ፡፡ ፂም ይኖርሃል፡፡ ፍልስፍና፥ ታሪክ፥ ፖለቲካ፥ ትንሽ ሳይንስ ትለበልባለህ፡፡ ትከራከራለህ፡፡ በካሴት ሙዚቃ ትሰማለህ፡፡ ሲጋራ ታጨሳለህ፡፡ ወሬህ ፀዴ ይሆናል፡፡ አይዲያሊስት ሆነህ ቁጭ ትላለህ፡፡ ምድር ላይ ገነት ትፈልጋለህ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ባንተ ትግል ነፃ እንደሚወጣ ታምናለህ፡፡
ትመረቃለህ፡፡ በት በት ብለህ የመንግስት ስራ ትይዛለህ፡፡ ቤት ትከራያለህ፡፡ ኮት ትገዛለህ፡፡ መፃህፍት ይኖሩሃል፡፡ መንግስትን በጎሪጥ ታያለህ፡፡ እሱም ይገላምጥሃል፡፡ ሲመሽ ቢራ ትጠጣለህ፡፡ መንግስትን በሹክሹኩታ ታማለህ፡፡ መኖር ትጀምራለህ፡፡ ለናትህ ሻሽ ትገዛለህ፡፡ ለአባትህ የጠጅ መጠጫ ትሸጉጣለህ፡፡ ጨረቃን በገመድ ለማውረድ እንደሞከርክ ይገባሃል፡፡ ኒያላ ለኩሰህ ከት ብለህ ትስቃለህ፡፡ ታገባለህ፡፡ እናትህን አያት ታደርጋለህ፡፡ ሰፈሩ ለሚያሰራው መንገድ ሊቀመንበር ትሆናለህ፡፡
ዛሬሬሬሬሬሬ…..
በእድል ትገባለህ፥ ትኮርጃለህ፥ ወይ ትንሽ ታነብ እና ትገባለህ፡፡ አንዱ ክልል ይወረውሩሃል፡፡ ጉዳይህ አይደለም፡፡ ግቢ ትደርሳለህ፡፡ የሆነ ቋንቋ የሚያወሩ ቢጤዎችህ ይቀበሉሃል፡፡ ያወሩሃል፡፡ ጠላትህን ያሳዩሃል፡፡ ፌሮ የሚቀመጥበትን ቦታ ታያለህ፡፡ ፋራሽህ ስር ቆመጥ ትቀረቅራለህ፡፡ ይሄን ለምን እንደምታደርግ አታውቅም፡፡ አጠይቅም፡፡ አያገባህም፡፡
የሆነ ትምህርት ትጀምራለህ፡፡ ሲመችህ ታነባለህ፡፡ ብዙ ስለማይመችህ አታነብም፡፡ ሌክቸር ያመልጥሃል፡፡ ትናንት ከጀለሶች ጋር አዳር ስለጠጣህ ደክሞሃል፡፡ ትተኛለህ፡፡ ህንዱ ሰውዬ ስለሚደብርህ ከሰዓት ትቀጣዋለህ፡፡ ፈተና ይደርሳል ትፈተናለህ፡፡ እናትህ ስልክ ተውሳ ትደውላለች፡፡ ትንሽ መላ ትቀፍላታለህ፡፡ በሶስተኛው ቀን ይደርስሃል፡፡ ይቃማል፡፡ ይጠጣል፡፡ ቸከስ ትመቻቻለህ፡፡
ቋንቋህን የሚያወራ፥ ጥብቅ ያለ ጨርቅ ሱሪ የለበሰ፥ የተወጠረ፥ አጭር፥ ደማቅ ካናቴራ ያደረገ መንጋ ይከብሃል፡፡ ውሎህ እዛው ነው፡፡ በቋንቋ ተደራጅተህ ትኮርጃለህ፡፡ ታስኮርጃለህ፡፡ ሽመል ይዘህ ትፋለማለህ፡፡ አታነብም፡፡ አትመረምርም፡፡
የእናትህ ሐሳብ ልጄ በየትኛው ብሔር ሽመል ይሞታል የሚል ነው፡፡ ሲኒየር ስትሆን አዲስ ጅንስ ትገዛለህ፥ ጫማ ትቀይራለህ፥ ያንተን ቋንቋ የምታወራ ሴት ትፈልጋለህ፥ በቋንቋህ ሙዚቃ ትሰማለህ፥ የብሔር ፀብ ትሳተፋለህ፡፡ ሙዚቃ፥ ፍልስፍና፥ ሐሳብ፥ ክርክር፥ ሳይንስ አይገባህም፡፡ እየተፋለምክ ትመርቃለህ፡፡ ባንተ መመረቅ ማንም አይገረምም፡፡ መመረቅህን ስታውቅ የራስህን ባዶ ጭንቅላት ይዘህ ትስቃለህ፡፡
ኒቼ፥ አውግስቲን፥ ፕሌቶ፥ ቮልቴር፥ ከበደ ሚካኤል፥ ገ/ህይወት ባይከዳኝ፥ ምናምን ምናምን ላንተ ምንም ናቸው፡፡ የአንተን ቋ ንቋ አያወሩም፡፡ ካንተ ብሄር አይደሉም፡፡ ላንተ ትልቁ ሰው ጃዋር፥ ቬሮኒካ፥ ሚኪ አማራ….ምናምን ናቸው!
ውነቴን ነው የምልህ አንተን ሳስብ ኤሊ እየጋለብኩ ወደሰማይ መብረር ያምረኛል!
Filed in: Amharic