>

ህወሀት የትግራይን ህዝብ  ''ለዋልኩልህ ውለታ አብረሀኝ አንድ ጉድጓድ በመግባት መልስልኝ'' እያለ ነው!! (መሳይ መኮንን)

ህወሀት የትግራይን ህዝብ  ”ለዋልኩልህ ውለታ አብረሀኝ አንድ ጉድጓድ በመግባት መልስልኝ” እያለ ነው!!
መሳይ መኮንን
* የትግራይ ህዝብ ጨዋ ነውና ብልት ላይ ሃይላንድ ውሃ የሚያንጠለጥሉትን አይደግፍም። የትግራይ ህዝብ የሴት ልጅ ጡት በኤሌክትሪክ ሽቦ የሚተለትሉትን የሚያቅፍበት ባህልና ማንነት የለውም። የትግራይ ህዝብ ጥፍር የሚነቅሉ፡ የሰውን ልጅ ክቡር ገላ በእሳት የሚጠብሱ አረመኔዎችን አያበረታታም። የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያዊ ነውና ኢትዮጵያዊ ወገኑን በጠራራ ጸሀይ የሚገድሉትን አያቅፍም። ይህ ሰልፍ የትግራይ ህዝብ ሰልፍ አይደለም። የህወሀት የስንብት ለቅሶ እንጂ። 
ህወሀት በወልቃይትና በራያ ምድር በየከተሞቹ ሰልፍ አዘጋጅቷል። በሁመራ ትላንት ተካሂዷል። በተለያዩ ከተሞች ደግሞ ዛሬ በመካሄድ ላይ ነው። ዓላማው ወልቃይትና ራያ ትግሬ እንጂ ሌላ አይደሉም የሚል እንደሆነ በትዕይንተ ህዝቡ ላይ በተሰሙትና በተያዙት መፈክሮች ከተላለፈው መልዕክት መረዳት ተችሏል። አስገራሚና ምናልባትም በዓለም ታሪክ የመጀመሪያ ተደርጎ ሊመዘገብ ይችላል። መሬትን የትግራይ ነው ብለህ ልትከራከር ትችላለህ። ወሰንና ድንበር እስከዚህ ድረስ የትግራይ አካል ነው የሚል አቋም ይዘህ በፍርድ ቤትም ይሁን የትም ልትሟገት መብትህ ነው። ማንነትን ግን ምን ታደርገዋለህ?
ወልቃይቶች ቋንቋችን አማርኛ፡ ስነልቦናችን የአማራ፡ ባህል ወጋችን ከአማራ፡ ቅዳሴ መዝሙራችን አማርኛ፡ ለቅሶ ዜማችን የአማራ ብለው ከተነሱ በኋላ የለም ትግሬ ናችሁ ብሎ መድረቅ ምን ማለት ነው? የራያዎችም ተመሳሳይ ነው። እንደውም በአብዛኛው የራያ አከባቢ ትግርኛ የሚናገር አለመኖሩን ያወቁት የትግራይ ክልል የቀድሞ አስተዳዳሪ አቶ አባይ ወልዱ ” እስከአሁን ትግርኛ ለምን አልተማራችሁም?” ብለው በመቆጣት ሰፈር መንደሩን በሙሉ ንግድ ቤቶች በትግርኛ ማስታወቂያቸውን እንዲያደርጉ በአንድ ሌሊት ማዘዛቸውን አስታውሳለሁ። በእርግጥ በየአደባባዩ እየወጡ ”እኛ ትግሬ ነን” የሚሉት ሰልፈኞች ትግሬዎች ስለመሆናቸው የተከራከራቸው የለም። አይደላችሁም ያላቸውም ካለ አልተሰማም። ችግሩ በወልቃይቶች ስም እኛ ትግሬዎች ነን ማለታቸው እንጂ። ራያዎችን ወክለው ትግሬ መሆናቸውን ማወጃቸው እንጂ።
ህወሀቶች ዘራፍ እያሉ ነው። ወልቃይትንና ራያን አትንኩ የሚለውን ቀረርቶ ባሰሙባቸውና ሊያሰሙባቸው በተዘጋጁባቸው ትዕይነተ ህዝቦች ሌላም መልዕክት ከፍ ብሎ እንዲሰማ አዘዋል። መልዕክቱም ”እየተወሰደ ያለው የእስር እርምጃ ትግራይን ለማንበርከክ በመሆኑ አጥብቀን እናወግዛለን” የሚል ነው። የህወሀት አቋም፡ የትግራይ ክልል መግለጫ፡ የደብረጺዮን ሀተታ ወደ ህዝብ ወርዶ እንዲስተጋባ ተወስኗል። ህወሀት ሌብነትን የብሄር አድርጎታል። ዘራፊዎቹና ገዳዮቹ ሲያዙና ለፍርድ ሲቀርቡ ”የትግራይ ህልውና ተነካ” የሚል ሃላፊነት የጎደለው ጸረ ህዝብ አቋም በመያዝ ህዝብን ለአመጽ ጠርቷል። ዛሬ በህዝብ ስም በየአደባባዩ የተስተጋባው ጩሀት የህወሀት የመጨረሻ የሲቃ ድምጽ ነው።
በእርግጥም የትግራይ ህዝብ ሌብነትን ይጠየፋል። የትግራይ ህዝብ ሃይማኖተኛ ነውና ግብረሰዶም በመፈጸም ወንጀል የሰሩትን አይመርቅም። የትግራይ ህዝብ ጨዋ ነውና ብልት ላይ ሃይላንድ ውሃ የሚያንጠለጥሉትን አይደግፍም። የትግራይ ህዝብ የሴት ልጅ ጡት በኤሌክትሪክ ሽቦ የሚተለትሉትን የሚያቅፍበት ባህልና ማንነት የለውም። የትግራይ ህዝብ ጥፍር የሚነቅሉ፡ የሰውን ልጅ ክቡር ገላ በእሳት የሚጠብሱ አረመኔዎችን አያበረታታም። የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያዊ ነውና ኢትዮጵያዊ ወገኑን በጠራራ ጸሀይ የሚገድሉትን አያቅፍም። ይህ ሰልፍ የትግራይ ህዝብ ሰልፍ አይደለም። የህወሀት የስንብት ለቅሶ እንጂ።
አዎን! ህወሀት ወደ መቃብር ብቻውን መውረድ አስፈርቶታል። ህዝብ አብሮት ይወርድ ከሆነ በሚል እየተፍጨረጨረ ነው። የትግራይ ህዝብን ”ለዋልኩልህ ውለታ አብረሀኝ አንድ ጉድጓድ በመግባት መልስልኝ” የሚል ከፊል ማስገደድ በከፊል ልመና የሆነ መልዕክት ከህወሀት ቢሮ እየተላለፈ ነው። እውን ህወሀት ለትግራይ ህዝብ የዋለው ውለታ ምንድን ነው? የትግራይ ህዝብና ህወሀት ምንና ምን ናቸው?
የእርዳታ እህልን ለፖለቲካ ትርፍ በማዋል በአስርሺዎች የትግራይ ልጆች ያለቁበት አስከፊው የረሃብ አደጋ እንዲከሰት ያደረገው ማን ነው? በደርግ መንግስት ከተገደሉ የትግራይ ልጆች አንጻር ህወሀት ያጠፋቸው ተጋሩዎች ቁጥር እንደሚልቅ ያውቁ ኖሯል? የሀውዜን ትራጄዲ የህወሀት የፖለቲካ ድጋፍ ማሰባሰቢያ ስልት አንዱ እቅድ እንደነበረስ? ትግራይን ኢፍትሃዊ በሆነ መልኩ ማልማትና ማሳደግ ጤናማ ያልሆነ፡ ህወሀት ለትግራይ ህዝብ የቀበረው አደገኛ ፈንጂ መሆኑንስ? ህወሀት በተከተለው የዘር ፖሊሲ የተነሳ የትግራይ ህዝብ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ወገኑ ያተረፈው ምንድን ነው? ከህወሀት ልቆ ለትግራይ ህዝብ ጠላት የሆነ እውን ማን ነው? በሚቀጥለው ጽሁፍ እመለስበታለሁ።
Filed in: Amharic