>
4:53 pm - Friday May 25, 8846

የህወሃት ሴራዎችን ማክሸፍ እና ለውጡን ማሳከት የኢትዮጵያ ህዝብ ግዴታ ነው!!! (ብርሀን መስቀል አበበ)

የህወሃት ሴራዎችን ማክሸፍ እና ለውጡን ማሳከት የኢትዮጵያ ህዝብ ግዴታ ነው!!!
ብርሀን መስቀል አበበ
 
የኢትዮጵያ ህዝብ በአሁኑ ሰዓት ህወሃት እና ተባባሪዎቻቸው በጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስት አመራር ወደ ፊት እየተራመደ ያለውን ለውጥ ወይ 1) ለማዳከም 2) ለመቀልበስ 
3) ህወሃት ወይም የህወሃት አሻንጉሊቶች የጠቅላይ ሚንስትር አብይን መንግስት ተክተው ወደ ስልጣን እንዲመለሱ ለማድረግ የሚሰሩትን የተለያዩ የፖላቲካ ቁማሮች  ተገንዝቦ  ከጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስት ጎን  መቆም እና ራሱ ያመጣውን ለውጥ መጠበቅ እና ከግብ የማድረስ ግዴታ እንዳለበት መረዳት  አለበት።  
ነገሩን ግልፅ አድርገን እንመልከት። ህወሃትን ከስልጣን ያባረረው በቲም ለማ የተመራው የኢትዮጵያ ህዝብ በተለይም የኦሮሞና የአማራው ህዝብ አመፅ ነው። ስለዚህ ህወሃት ወደ ስልጣን ለመመለስ ወይም በለውጡ ምክንያት ሙሉ ለሙሉ እንዳት ጠፋ ማድረግ ያለበት ቲም ለማን ወደ ስልጣን ያመጣውን ህዝባዊ አመፅ መከፋፈል እና የጠቅላይ ሚንስትር አብይን መንግስት ማዳከም ወይም በህወሃት አሻንጉሊቶች ለመተካት መስራት ነው።
ይህን አላማቸውን ወደ ስራ ለመቶርጎም ህወሃት ባለፉት 7 ወራት ብቻ ከመቶ በላይ የምክክር ስብሰባዎች እና ከ95 በላይ የህወሃት የወደ ፊት ስትራቴጂ የመረመሩና ዓላማ አመላካች ጥናታዊ ፁሁፎችን በውጭ አገር እና በአገር ውስጥ ባለሙያዎች  ኣሰርተዋል። በተቃራኒው በተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ የተደረገ እዚህ ግባ የሚባል ውይይት እንኳን የለም።
ህወሃት ይህን አላማውን ለማሳካት ስድስት ዋና ዋና ስትራቴጂዎችን ነድፎ አየተንቀሳቀሰ ነው።
 ይኸውም ህወሃት:-
1ኛ) በትግራይ፣
  2ኛ) በአማራ፣
3 ኛ) በደቡብ፣
4 ኛ)  በኦሮሚያ፣
 5ኛ) በሶማሌ፣ቤኒሻንጉል፣በገምቤላ እና በአፋር እንዲሁም
6ኛ) በተቃዋሚ ፖርቲዎች ለይቶ በስራ ላይ ለማዋል እየጣረ ያላቸው ስትራቴጂዎችን ለውጡን ለመቀልበስ ያላቸውን  የፖላቲካ እንድምታቸው የኢትዮጵያ ህዝብ አንድ በአንድ መርምሮ ማወቅ አለበት።
1ኛ፣ የህወሃት ስትራቴጂ በትግራይ
ህወሃት በትግራይ ህዝብ ውስጥ ካልተደበቀ ሌላ ዋሻ የለውም። ስለዚህ ህወሃት ከስልጣን በነአብይ ሲባረር የህወሃት ሌቦቹን እና ነፈሰ ገዳዮች የሸሹት ወደ ትግራይ ነው። ህወሃት በትግራይ ሶስት አላማዎችን ይዞ ይንቀሳቀሳል። እነርሱም 1ኛ) ትግራይ መሽጎ ራሱን እና ሌቦቹን  ከጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስት መከላከል። 2ኛ) ትግራይን እንደ ኮማንድ ፖስት በመጠቀም የጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስትን የሚያዳክሙ ስራዎችን በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ እና በተቀረው የኢትዮጵያ ክፍል መስራት። 3ኛ) በዘላቂነት ህወሃት በኢትዮጵያ ፖላቲካ king maker የሚሆንበትን መንገድ በመተለም የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎች የህወሃት ጥቅም አስከባሪ የሚሆኑበትን መንገድ መቀየስ ናቸው።
ህወሃት የትግራይ ህዝብን ለዚህ አላማዎቹ ለመጠቀም  በተለያዩ መንገዶች  የኢትዮጵያ ህዝብ እና የጠቅላይ ሚንስት አብይ መንግስትን የትግራይ ህዝብ ጠላት እንደሆነ ማሳየት ነው።  በአጭሩ ለትግራይ ህዝብ ጠላት መፍጠር እና ከዚያ ጠላት የትግራይን ህዝብ መከላከል የሚችለው ህወሃት ብቻ እንደሆነ ህዝቡን ማሳመን ነው። በሌላ ቋንቋ  የትግራይን ህዝብ ከዚህ ሰፊ ጠላት የሚያድን ብቸኛው የታጠቀና የተደራጀ  ኃይል ህወሃት እንደሆነ ማስቀመጥ ነው።
ለዚህም ማሳያ የፌዴራል መንግስቱን እና የአማራ ህዝብን እንደጠላት በመፈረጅ ህወሃት ትናንት በተለያዩ የትግራይ ከተሞች የህወሃት ሌቦች እና ነፈሰ ገዳዮች በተቀረው የኢትዮጵያ ክልል ያሉ ህወሃት የመለመላቸው እና የሚያውቃቸው ሌቦች እና ነፈሰ ገዳዮች ለፍርድ ሳይቀርቡ( በነሱ አባባል selective justice)  የህወሃት ሌቦች እና ነፈሰ ገዳዮች ለፍርድ አይቀርቡም በማለት የተደረገው የሌቦች እና ነፈ ገዳዮች የድጋፍ ሰልፍ አስገራምና የዚህ ስትራቴጂ አካል ነው። ህወሃት በዚህ ዲርጊቱ የትግራይ ህዝብ ለፍትህ እና ለእኩልነት ከቆመው የጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስት ይልቅ ለአንድ ቀንም ቢሆን ለሌቦች እና ነፈሰ  ገዳዮች የቆመ አስመስሎታል።
 በዚህ የትግራይን ህዝብ  የህወሃት ዋሻ ማድረግ ስትራቴጂ  ላይ ብዙ ማለት ብቻ ሳይሆን ስትራቴጂውን ለመቀልበስ ብዙ መስራት ይጠበቅብናል።
2 ኛ) ህወሃት በአማራ ላይ የሚከተለው ስትራቴጂ፣ 
ህወሃት  የአማራን ህዝብ የትግራይ ህዝብ ጠላት በማድረግ፣ ራሱን በትግራይ ለማደላደል  አራት ስትራቴጂዎችን ቀርፆ እየሰራ ይገኛል።
 1ኛ) ህወሃት በትግራይ እንዲደላደል በአማራ የትግራይ ጠላት መፍጠር አስፈላጊ ነው። ህወሃት ይህን ለመተግበር ህጋዊ የሚመስሉ የቅማንት እና የአገዉ የራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ማራገብ እና የአማራ ህዝብ ጠብ አጫሪነቱን በመቃወም በትግራይ ህዝብ ላይ እንዲነሳ በማድረግ እና ህወሃት የትግራይን ህዝብ ከአማራ የሚጠብቅ ብቸኛ ኃይል እንደሆነ  በማስመሰል።
 2 ኛ) የወልቃይት እና የራያን ጉዳይ በትግራይ እና በኤርትራ መካከል ከነበረው ውጥረት ባልተናነሰ ሁኔታ በማራገብ  በአማራ እና በትግሬ መካከል ዛሬ ነገ ጦርነት እንደሚቀሰቀስ እና ህወሃት ለትግራይ ህዝብ ብቸኛ አዳኝ እንደሆነ በመሳል።
 3ኛ) የአማራ ህዝብ በመላው ኢትዮጵያ ተበትኖ እየኖረ ያለ ህዝብ ነው። የዚህ ህዝብ ብሄራዊ ጥቅም የሚጠበቀው በመላው ኢትዮጵያ ካሉ ብሄር፣ብሄረሰቦች ጋር ተቀባብሎ እና ተከባብሮ በመኖር ውስጥ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ  በህወሃት ጠብ አጫርነት በአማራ ህዝብ ውስጥ እየተቀሰቀሰና እንዲደራጅ እየተደረገ ያለው ፅንፈኛ የአማራ ብሄርተኝነት ግቡ ህወሃት በትግራይ እንዲደላደል ማድረግ ብቻ ሳይሆን የአማራ ፅንፈኛ ብሄርተኞች  በኦሮሚያና በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ላሉ ህዝቦች ስጋት እንዲሆኑ እና  የህወሃት አጋሮችን በነዚህ ክልሎች እንዲያገኝ ማድረግ ነው።
 ይህ ማለት ህወሃት የፌዴራል መንግስቱን እና  የአማራን ህዝብ የትግራይ ህዝብ ጠላት በማድረግ ድጋፍ ለማግኘት መጣር ብቻ ሳይሆን የሌሎች ክልል ህዝቦችን በአማራ ብሄርተኝነት ፍራት የህወሃት አጋር በማድረግ ራሱን  ትግራይ ውስጥ ያደላድላል ማለት ነው።
 ህወሃት የኦሮሞ ብሄርተኝነትን ላለፉት 27 ዓመታት እንዴት እንደ ጭራቅ በመሳል ከተቀሩት የኢትዮጵያ ህዝቦች በተለይም ከአማራ ህዝብ ድጋፍ ለማግኘት  እንደተጠቀመ የሁላችንም የትናንት ትዝታ ነው። አሁን የተፈጠሩት ፅንፈኛ የአማራ ብሄርተኞች የተፈጠሩት ህወሃት ተሸንፎ ከአዲስ አበባ ከሸሸ በኃላ መሆኑ አፈጣጠራቸው ውስጥ ራሱ የህወሃት እጅ ሳይኖርበት አይቀርም የሚሉ ብዙዎች ናቸው።
  4 ኛ) ህወሃት ከስልጣን የተባረረው በአማራ እና በኦሮሞ ህዝብ የትግል ህብረት በመሆኑ  አማራ እና ኦሮሞ ህዝብ አንዱ የአንዱ ጠላት እንዲሆን “የእሳት እና ጭድ” አጀንዳ ማራመድ ነው። ለዚህ ደግሞ የአማራ እና የኦሮሞ ብሄርተኞችን በማባላት ብቻ ሳይሆን ስልጣን ሁሉ በኦሮሞ ተያዘ የሚል ነጠላ ዜማ በጠቅላይ ሚንስትር አብይ  መንግስት ላይ ማዜም የተጀመረው በህወሃት ካዲሬዎች እንደነበረ ሁሉም ያስታውሳል። ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ እንደሚያውቀው የህወሃት የውሸት ዜማ እንደተጠበቀ ሆኖ   ኦሮሞ በፌዴራል መንግስቱ ውስጥ ያለው ድርሻ  ከ40% በታች መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው። የህወሃት አላማ ግን አማራ እና ኦሮሞን በማባላት የጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስት የሁሉም እኩል የሆነች ኢትዮጵያን እንዳይገነባ እና የህወሃት ሌቦችን ለፍርድ እንዳያቀርብ  ለውጡን ለማዳከም ወይም ለመቀልበስ የታቀደ ነው።
የአማራም ሆነ የኦሮሞ ህዝብ  መረዳት ያለበት እውነታ  የጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስት ከተጠናከረ  ህወሃት ከስልጣን እንደሚወርድ እና ትልቅ የሚመስሉ  የወሰንም ሆነ ሌሎች እንቆቅልሾች ሁሉ  ልክ እንደ ኢትዮ ኤርትራው ጦርነት ድራማ  የህወሃት ሌቦች  በትግራይ ከስልጣን በተባረሩ ማግስት   በአንድ ጀንበር እንደሚፈቱ አውቆ የህወሃት ዕቃ እንዳይሆን ራሱን መጠበቅ  እና የጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስትን ማጠናከር ነው።
 
3ኛ) የህወሃት ስትራቴጂ በደቡብ ክልል፣ 
ህወሃት ወደ 56 የሚሆኑ ብሄር፣ ብሄረሰቦችን አንድ ላይ ሰብስቦ አንድ ክልል አድርጎ የሰራው የኦሮሞ እና የአማራ ፖላቲካን contain ለማድረግ እና እንደ ፖላቲካ balance መፍጠሪያ ደቡብን ተጠቅሞ ራሱን በስልጣን ላይ ለማቆየት ነበር። ሃራሪን የምታክል 20 ሺህ ህዝብ በላይ ያሌላትን ብሄረሰብ ሃረር ላይ ኦሮሞን ለማዳከም ክልል ሲያደርግ ሲዳማን የሚያክል ህዝብ እውቅና የሚነግፉበት ሌላ አላማ አልነበረውም። ቤኒ ሻንጉል እና ጋምቤላም የተፈጠሩት ኦሮሞ እና አማራን ለማዳከም እና ህወሃቶች መሬታቸውን እንዲቀሙ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት እንጂ ሁለቱ ክልሎች ሲደማን በደቡብ ውስጥ እንዳደረጉት ሁሉ በኦሮሚያና አማራ ስር የዞን ደረጃ ተሰጥቷቸው፣ ቋንቋቸው እና ማንነታቸው ተጠብቆ ራሳቸውን ማስተዳደር ይችሉ ነበር። አሁንም ህወሃት ከስልጣን ሲባረር ህወሃት በደቡብ የቀበራቸው ፈንጂዎች እየፈነዱ ነው። ይህ ደግሞ የጠቅላይ ሚንስትር አብይን መንግስት በእሳት ማጥፋት ስራ ለመጥመድ ነው። ያኔ ጠቅላይ ሚንስትሩ የህወሃት ሌቦች እና ነፈሰ ገዳዮችን ለፍርድ ከማቅረብ ይልቅ ለእሳት ማጥፋቱ ስራ ቅዲሚያ ይሰጣል። ህወሃት በሰላም ይኖራል። የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችም ይህን የህወሃት ስትራቴጂ ተረድተው ራሳቸውን የህወሃት ተላላኪ መጫወቻ እንዳያደርጉና ሰላማቸውን እንዲጠብቁ በአንክሮ እንመክራለን።
4 ኛ) የህወሃት ስትራቴጂ በሶማሌ፣ በአፋር፣ በቤኒ ሻንጉል እና በጋምቤላ፣ 
በሶማሌ እና በቤኒ ሻንጉል እንደታየው የነዚህ ክልሎች ሚልሻዎች በህወሃት የተደራጁት ኦሮሞ እና አማራን እንዲወጉ ነው። በኦሮሞ ቅዋሜ ጊዜ እንደታየው የሱማሌ ሚልሻ በህወሃት መሪነት በኦሮሞን ህዝብ ላይ ጦርነት ከፍቶ ከአንድ ሚልዮን ህዝብ በላይ አፈናቅሏል። በቤኒ ሸንጉልም ተመሳሳይ ሚልሻዎች በኦሮሞ ህዝብ ላይ ጦርነት ከፍተው ህዝብ እያፈናቀሉ ነው። በአፋር እና በጋምቤላም ተመሳሳይ ሙከራዎች በህወሃት ነፈሰ ገዳዮች እየተሞከረ ነው። የዚህ ዋና አላማ የጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስት ወደ እርስበርስ ጦርነት እንዲገባና ሰላማዊ ለውጡ እንዲደናቀፍ ህወሃት የቀየሰው መንገድ ነው። የጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስት እንዴት ባለ ጥበብ ኮሽ ሳይልበት የሱማሌውን ችግር እንደ ፈታ ህዝባችን ያውቃል። አሁንም በወለጋ ያለውን ችግር ለመፍታት በከፍተኛ ጥበብ እየሄዱበት ነው። ህዝባችንም ይህን አውቆ የህወሃትን ሌቦች ሴራ ማክሸፍ እና ከጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስት ጎን መቆም አለበት።
 
5ኛ) የህወሃት ስትራቴጂ በኦሮሚያ፣ 
ህወሃት በኦሮሚያ ሶስት ዋና ዋና ስትራቴጂዎችን አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው።
 1 ኛ) አንደኛው የህወሃት ስትራቴጂ አብይና ለማን በኦሮሚያ የህዝብ ድጋፍ በማሳጣት፣ መጣል እና የኦሮሞን ህዝብ ትግል ማጨናገፍ ነው። ቲም ለማ ህወሃትን ከኦሮሚያና አዲስ አበባ ያባረረው የኦሮሞን ህዝብ ጦሩ እና ጋሻው በማድረግ እንደሆነ ህወሃት ያውቃል። አሁን የህወሃት ተላላኪዎች ቲም ለማ  የኦሮሞን ህዝብ ጥያቄዎች መመለስ አልቻለም በማለት የጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስት የኦሮሞ ህዝብ ድጋፍ በማሳጣት ከስልጣን እንዲወርዱ ወይም እንዲዳከም  ለውጡን መቀልበስ እየጣሩ ነው።  ህወሃት ለ27 ዓመታት በኦሮሞ ህዝብ ላይ የሰራው የኢኮኖሚ፣ የፖላቲካ እና የማህበራዊ ችግሮች አብይና ለማ ህወሃት ያፈረሳትን ኢትዮጵያን  እየጠገኑ በአንድ ጀንበር እንዳማይፈቱ ያውቃሉ። ህዝቡ ይህን ውስብስብ ችግር  በቅጡ ስለማይገነዘብ በህወሃት የሚደገፉ  በየአደባባዩ  አብይ እና ለማ የኦሮሞን ጥያቄ አይመልሱም፣ ለኦሮሞ አልቆሙሙ፣ አልፎ ተርፎም የኦሮሞ ህዝብ ጥቅም እየሸጡ ነው የሚሉ  ህዝብ የሚያስለቅሱ አስለቃሾች ህወሃት በኦሮሚያ  ፈጥሯል።
 2ኛ) ሁለተኛው የህወሃት ስትራቴጂ  ቲም ለማ በኦሮሚያ  ሳይጠናከር እና ስር ሳይሰድ በእነርሱ ላይ ተቀናቃኝ የኦሮሞ ድርጅቶችን በእነርሱ ላይ በመፍጠር የጠቅላይ ሚንስተር አብይን መንግስት ድጋፍ በኦሮሚያ መቀነስ እና ማዳከም፣ ከተቻለም መገልበጥ ነው። በስመ ተቃዋሚ ምንም ለህዝብ መፍትሄ የሚሆን አጀንዳ ሳይዙ እነለማን ለማዳከም የሚንቀሳቀሱት እነዚህ ቡድኖች በአንድ በኩል  ህወሃት በቀድሞ ኦህዲድ ውስጥ ያደራጃቸውን ሌቦች እና ነፈሰ ገዳዮች ለውጡ ወደ ህዝቡ እንዳይ ወርድ በማድረግ ለውጡን ከውስጥ በማነቅ sabotage የሚያደርጉ ሲሆን ከውጭ ደግሞ ለህዝብ ተቆርቋር በመመሰል የኦሮሞ ህዝብ ለነለማ ያለውን ድጋፍ ይሸረሽራሉ።
 3ኛ) ሶስተኛው የህወሃት ስትራቴጂ የአንደኛው እና የሁለተኛ የህወሃት ስትራቴጂ  ተቃራን ሲሆን ለማና አብይ የኢትዮጵያን ህዝብ ጥያቄዎች ሳይሆን  የኦሮሞ ብሄርተኞች hostage ተይዘዋል  ወይም ለማና አብይ ኦነግ ናቸው በማለት የጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስት የኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፍ እንዳያገኙ ለማድረግ መጣር ነው። በሶሻል ሚዲያ  ይህን ብቻ የሚሰሩ የህወሃት ካዲሬዎች ለዚህ ምስክር ናቸው።
የህወሃት የኦሮሚያ  ስትራቴጂ የቀድሞው የኦህድድ መጥፎ ስም ከነለማ እና አብይ እንዳይላቀቅ   ከዚህ በፊት በህወሃት ሲሰቃዩ የነበሩትን እና ቲም ለማ ከህዝቡ ጋር የቀላቀሏቸውን የኦሮሞ ተቃዋሚ ቡድኖች ለስልጣን እና ለገንዘብ ያላቸውን ፍላጎት በመጠቀም ቲም ለማ የኦሮሞ ህዝብ ድጋፍ እንዲያጣ ፀረ ቲም ለማ ቅስቀሳዎች እንዲያደርጉ በማድረግ ጭምር የታገዘ ነው።  በኦሮሚያ በአንዳንድ  የኦሮሞ ተቃዋሚ ቡድኖች የሚጠሩት ስብሰባዎች እና ሰልፎች በትርክታቸው ካልሆነ በስተቀር በግባቸው ትናንት በትግራይ ከተደረገው ህወሃትን በማጠናከር፣ የጠቅላይ ሚንስትር አብይን የለውጥ መንግስት ለማዳከም ከተጠሩት ሰልፎች በይዘትም ሆነ  ግብ የተለየ አላማ ዬላቸውም።  በአጭሩ በነዚህ ቡድኖች በኦሮሚያ የሚጠሩት ሰልፎች ትርክት እነአብይ የኦሮሞ ህዝብን ጥያቄ ስላልመለሱ ወይም መመለስ ስለማይችሉ ቶሎ ምርጫ ይደረግና በነአብይ ምትክ እኛን ምረጡ የሚል ነው። ላይ ላዩን ብቻ ለሚያይ ይህ ትርክት ትክክለኛ የተቃዋሚ ፖላቲከኛ ስራ ይመስላል።  እውነተኛ ግቡ ግን አሁን በቲም ለማ የተጀመረው ለውጥ ስር ሳይሰድ የኦሮሞን ህዝብ ድጋፍ አጥቶ በቶሎ እንዲነቀል እና በህወሃት የሚደገፍ አሻንጉሊት በኦሮሚያ ስልጣን እንዲይዝ ለማድረግ ነው። ያ ሁኔታ ከተፈጠረ የህወሃት ሌቦች ነፃ መውጣት ብቻ ሳይሆን  እነአብይን ይበቀላሉ፣ የኦሮሞ ትግል ይመክናል፣ አገር ይፈርሳል ወይም ኢትዮጵያ በህወሃት ሌቦች እጅ ዳግም ትወድቃለች። (በኦሮሚያ ቲም ለማ ካልተመረጠ ሌላ ኢትዮጵያ አቀፍ  አጀንዳ የለው የኦሮሞ የፖላቲካ ድርጅት እንዳሌለ ህወሃት ስለሚያውቁ እነ አብይን በሌላ የኦሮሞ ቡድን ማጥፋት ለህወሃት ግንባር ቀደም ስትራቴጂ ነው።) የኦሮሞ ህዝብ ይህን አውቆ የነለማን ድክመት እና ጉድለት በማጠናከር እና ለኦሮሞ ህዝብ በእውነት የቆሙ ቡድኖች ሁሉ ከጠቅላይ ሚንስትር አብይ መንግስት ጋር እንዲደመሩ እና የኦሮሞ ህዝብ እስከ ዛሬ ያገኘውን ድል ጠብቆ፣ በቀጣይነት ቀሪ የኦሮሞም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ የፍትህ እና የእኩልነት ጥያቄዎች እንዲመለሱ ትግሉ እና ድጋፉን መቀጠል አለበት።
6ኛ) ስድስተኛው የህወሃት ስትራቴጂ የኢትዮጵያ ተቃዋሚዎችን እንደመሳሪያ መጠቀም ነው፣ 
በኢትዮጵያ ሁለት ዓይነት ተቀዋሚዎች አሉ። የመጀመሪያዎቹ ወደ 60 የሚሆኑ በህወሃት ደህንነት ደሞዝ እና ስራ ማስኬጂያ ተመድቦላቸው በምርጫ ጊዜ ብቅ  እንዲሉ ላለፉት 27 ዓመታት ለፈረንጆች መደለያ ህወሃት ያቋቋማቸው ተቃዋሚዎች ናቸው። እነዚህ ህወሃት ዝለሉ ሲላቸው የሚዘሉ፣ ቁጭ በሉ ሲላቸው የሚቀመጡ ናቸው። ሁለተኛዎቹ አይነት የህወሃትን መንግስት ለመቃወም ብቻ የተቋቋሙ resistance ፖላቲካ ውስጥ የነበሩ፣ ከህወሃት ቁዋሜ ውጭ ምንም አይነት አገር የማስተዳደር አጀንዳም ሆነ መሪ ያላዘጋጁ ተቃዋሚ የፖላቲካ ድርጅቶች ናቸው።
 ጠቅላይ ሚንስትር አብይ የፖላቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እና  አጋር ይሆኑኛል ብሎ ወደ አገር የመለሳቸው እና አገር ውስጥ የነበሩትን  ድርጅቶች ጨምሮ አብዛኞቹ አሁንም መንግስት ከመኮነን ውጭ  በምዕራቡ አለም መመዘኛ ፖርቲ ልባሉ የሚችሉ ድርጅቶች አይደሉም። ወደ ምርጫ ለመግባት የሚያስቡትም  ኢህዴግን የጠላና ምርጫ የሌለው ይመርጠናል ወይም protest vote እናገኛለን  በሚል ተስፋ ነው።
የኢትዮጵያ ህዝብ አሁን  እነዚህ ድርጅቶች ማን እንደሆኑ መመርመር መጀመር አለበት። እነዚህ ድርጅቶችም  ምንም አገራዊ አጀንዳ ሳይኖራቸው ሲሻቸው  የሽግግር መንግስት ይቋቋም፣ወይም elites bargain ይደረግ እና ስልጣን ይሰጠን፣ ወይም ከአንድ አመት በኋላ በ2020 ምርጫ ይደረግ እያሉ የጠቅላይ ሚንስትር አብይን መንግስት ለውጡን ስር እንዳያሰድ ማደናቀፍ ማቆም አለባቸው።
 አወቁም፣ አላወቁም ተቀዋሚ በሚመስሉ ነገር ግን ገና የፖላቲካ ፖርቲ ባልሆኑ ተቃዋሚ ቡድኖች የሚቀርቡ የሽግግር መንግስት የማቋቋም ጥያቄ፣ በ elites bargain ስም የስልጣን አካፍሉን ጥያቄ እና የምርጫ ፖላቲካ የህወሃት ሌቦችን  የጠቅላይ ሚንስትር አብይን የለውጥ መንግስት የማዳከም ወይም የመቀልበስ አጀንዳ ከማራመድ  ውጭ  ሌላ ምንም ፋይዳ የለውም።
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ነገ ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር ይሰበሰባሉ። ከሁለቱም አይነት ተቃዋሚዎች ጋር። እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ለጠቅላይ ሚንስትሩም ሆነ ለተቃዋሚዎች መልዕክት አለኝ። በመጀመሪያ  ጠቅላይ ሚንስትሩ የጀመሩትን ለውጥ መልክ ለማስያዝ እና አገርቷን አረጋግቶ ለመጨረስ ያለውን ውስብስ የአገርቷን ሁኔታ በግልፅ ለድርጅቶቹ ማስገንዘብ አለባቸው። በሁለተኛ ደረጃ የተቃዋሚ ድርጅቶች በጠቅላይ ሚንስትሩ የተጀመረው ስር ነቀል ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና በ2020 የታቀደው ምርጫ  በሁሉም ስምምነት ወደ 2025 ለአምስት አመት እንዲሸጋገር ለመጠየቅ ተዘጋጅተው መሄድ  አለባቸው።
 ተቃዋሚዎች ምርጫው ለአምስት አመት ተራዝሞ  በ2025 እንዲደረግ ሲጠይቁ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር በሚቀጥሉት  ትላልቅ አገራዊ Roadmaps ላይ ስምምነት ቢደርሱ ይመከራል።እነርሱም ጠቅላይ ሚንስትሩ እና መንግስታቸው  እስከ 2025 ባለው አምስት አመት:-
  1ኛ) ህወሃት የኢትዮጵያ መንግስት እና ኢህዴግን አንድ አድርጎ እና ቆላልፎ ለ27 አመታት ያደረጀውን የደህንነት፣ የመከላከያ፣ እና የኢትዮጵያ መንግስት  የቢሮክራሲ መዋቅሮች እና የሰው ኃይሉ  ለ multi-party በሚመች መልኩ independent ተደርጎ እንደገና  እንዲያዋቅር።
 2 ኛ) በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በህወሃት ሌቦች እና ተባባሪዎቻቸው የተቀሰቀሱት ጦርነቶችን አቁመው ሰላምና መረጋጋት በኢትዮጵያ እንዲመልሱ።
3ኛ)ከአገር ውስጥ እና ከውጪ ድጋፍ በማሰባሰብ  ከ3 ሚልዮን በላይ በኢትዮጵያ ውስጥ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሰው እንዲያቋቁሙ።
4 ኛ) በኢትዮጵያ የፈረሱትን የአገራዊ አንድነት ስሜት፣ የመንግስት ተቋማት እና በህወሃት የሌብነት እና የግድያ ዘመን የፈረሱትን የኢትዮጵያ ህዝብ  ማህበራዊ እሴቶች መልሶ ለመገንባት ተቃዋሚ ድርጅቶችን ሁሉ ባካተተ መልኩ nation building እና  state building አጀንዳ ቀርፀው  የኢትዮጵያ ህዝብ አገሩን መልሶ   አንዲገነባ አገራዊ ጥሪ ማድረግ።
5ኛ) የህወሃት እና የሌሎች የኢህዴግ ድርጅቶች ተባባሪ ሌቦች እና ነፈሰ ገዳዮችን ማስተማሪያ እና መቀጣጫ ሊሆን በሚችል መልኩ ለፍርድ እንዲያቀርቡ እንዲያደርጉ። 6ኛ) ህወሃት የተከላቸውን መርዞች ነቅሎ ህዝብ የሚያስታርቁ truth and reconcilation comission አቋቁመው ሰላም በኢትዮጵያ እንዲያወርዱ። 7ኛ) በፌዴራል ክልሎች መካከል ያለውን የወሰን እንዲሁም አዲስ ክልል እንሁን የሚሉ ብሄሮችን ጥያቄ  በህገ መንግስቱ መሰረት እንዲፈቱ። 8ኛ) ከ2025 በፊት የህዝብ እና የቤት ቆጠራ በመላው ኢትዮጵያ  እንዲያደርጉ። 9ኛ) በ2025 በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ዴሞክራሳዊ ምርጫ እንዲደረግ ገለልተኛ  የምርጫና የፍትህ ተቋማት እንዲገነቡ መጠየቅ እና ስምምነት ላይ መድረስ አለባቸው።
ይህ ከሆነ የህወሃት ሌቦች እና ነፈሰ ገዳዮች ተቃዋሚ ድርጅቶችን በመጠቀም አንዴ በሽግግር መንስት ስም፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በelites bargain፣ ሲያሻቸው ደግሞ ምርጫ እያሉ የጠቅላይ ሚንስትር አብይ የለውጥ መንግስት ስር እንዳይሰድ እና  አገር እንዲፈርስ፣ ለውጡ እንዲደናቀፍ እና እነርሱ ከተጠያቂነት እንዲያመልጡ በእጅ አዙር የሚሸርቡት ሴራ እንዲፈርስ ያደርጋል። የኢትዮጵያ ህዝብም ይህን ፈታኝ ሁኔታ ተገንዝቦ በተቃዋሚ ድርጅቶች ላይ ምርጫው በአምስት አመት ተራዝሞ በ2025 እንዲደረግ ብርቱ ግፊት ማድረግ አለበት።
በአጠቃላይ፣ እነዚህ ከአንድ እስከ ስድስት የተዘረዘሩት የህወሃት ስትራቴጂዎች የኢትዮጵያ ህዝብ በሚገባ ተገንዝቦ እንዲያፈርሳቸው እና የተጀመረው ለውጥ ስር ሰዶ በኢትዮጵያ ህዝባዊ መንግስት ተቋቁሞ ኢትዮጵያ የፍትህ እና የእኩልነት አገር እንድትሆን ትግሉን ለመቀጠል በአንክሮ መምከር እና የፀረ ለውጥ ኃይሎችን ሴራ መክሸፍ ይጠበቅበታል።
Filed in: Amharic