>

"ሞትን ደብቆ እሬሳውን ምን ለማድረግ?!?" (ደረጄ ገረፋ ቱሉ)

“ሞትን ደብቆ እሬሳውን ምን ለማድረግ?!?”
ደረጄ ገረፋ ቱሉ
ሞትን ደብቆ እሬሳውን ምን ለማድረግ ነው ይባላል።  የአፋን ኦሮሞ አባባል ስለዚህ  በኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ ጎላ ያለ ስፍራ ያላቸውን አንዳንድ ወገኖች አንዳንድ ጥያቄ መጠየቅ እንቀጥላለን።
ዶር አቢይ እና ለማ ፦
በኢትዮጵያ እና በኦሮሚያ እጂግ ውስብስብ ችግር አለ።ህዝቡ የሚያሰማቸው መዓት ሮሮዎች እና ከበፊቱ ጀምሮ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች አሉት። እጂግ ብዙ ህዝብ በገጠር መሬት፤  በከተማ ስራ የለውም።ስለዚህ እነዚህን ችግሮች የሚረዳ እና የሚመልስ ሃይል አደራጅታችኃል ወይ?እነዚህን የህዝብ ጥያቄ አንጥሮ በማውጣት ለችግሮቹ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ የማይናወጥ ኮር( core)  አላችሁ ወይ?ለመሆኑ የለውጥ ሃይል ( change agent) ፈጥራችኋል?ባለፈው 7 ወራት ብዙ ነገር እንዳደረጋችሁ ዓለም የሚያውቅ ነው። ብዙ መፍረስ ያለበቸውን ሃይላትም እንዳፈረሳችሁ እኔ ብደብቅ ሳር ቅጠሉ ምስክር ነው።ነገር ግን የራሳችሁን ጠንካራ የተደራጀ ሃይል ፈጥራችኃል ወይ?መቼም የድርጅታሁን ማዕከላዊ ኮሚቴ እና ስራ አስፈፃሚ እንደማትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ። የት ነው ያሉት? ምን የፖሊሲ አቅጣጫ በየትኛው ሚዲያ ላይ ተንትነው አቀረቡ?
በየትኛው ጋዜጣ ላይ ስለ ወደፊቷ ኢትዮጵያ ተንትነው አስረዱ? አያስኬድም ለማለት ነው።
ለማንኛውም ተከታዮቻችሁ የሚመሩበት የኢኮኖሚ ፣የማህበራዊ ፣የፖለቲካ ፍኖታ ካርታ በተፃፈ መልኩ እንዲዘጋጅ አድርጋችኃል ወይ?ሀገሪቱ በፖለቲካው ፤በኢኮኖሚው በማህበራዊው መልክ የት እንደምትደርስ የሚያሳይ ፍኖታ ካርታ ተዘጋጅቷል? ወይም እየተዘጋጀ ነው?ወይስ የሚያዘጋጅ ሃይል ፈጥራችኃል? መልስ እንፈልጋለን!!እሄ እስካልተመለሰ ድረስ  የሚደረጉት ነገሮች በሽታውን ትቶ ምልክት ከማከም አይለይም። በሽታውን ትቶ ምልክት ማከም ደግሞ ከህመም  ያስታግሳል እንጂ አያድንም።
አቶ ገዱ፤ደመቀ ፤አምባቸው  እና ደጋፊዎቹ
በለፉት ጥቂት ወራት የአማራ ብሄርተኝነት የብሄርተኝነቶች ሁሉ ውሃ ልክ ሆኗል። ለመሆኑ ይህ የአማራ ብሄርተኝነት እንዴት አርጎ ከክልሉ ውጪ ያሉትን በሚለየን የሚቆጠሩ አማራዎች እና በክልሉ ውስጥ ያሉትን አማራ ያልሆኑ ብሄሮች ሰላም እና ሁለንተናዊ ደህንነት ያረጋግጣል?
ለመሆኑ በአማራ ክልል ውስጥ ያሉትን አንዳንድ  ወንጀል የሰሩ ወገኖች “ውጡ” ማለትስ ትርጉሙ ጋንቤላ ፤ ቤንሻንጉል ፤ሱማሌ እና ወዘተ ክልል ላይ ምን ይሆን? ምንም ችግር ቢፈጠር እሄ እንዴት ከአማራ ክልል ይጀምራል?
አንድ ሰው ወንጀል ቢሰራ እዚያው በአማራ ክልል ውስጥ ወይም ህጉን ጠብቆ በፌደራል መንግስት ደረጃ እንደማንኛውም አማራ ይጠየቃል እንጂ እንዴት በእንደዚህ  ሁኔታ ከክልሌ ውጣ ይባላል? በእርግጥ እሄ በመንግስት ሚዲያ እንዳልተደረገ አውቃለሁ።ነገር ግን ብዙ በአማራ ብሄርተኝነት ስም የሚንቀሳቀሱ ኃይላት እሄንን ሲያደርጉ ክልሉ ምን አለ? እኔ ምንም  አልሰማሁም።
ዶ/ር ደብረፅዮን እና ደጋፊዎቹ
እውነት አሁን እየሄዱበት ያለው መንገድ የትግራይን ህዝብ ይጠቅማል ወይ?እውነት ለውጡ ያራገፋቸው ኃይሎች ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ቀውስ እያስተባበሩ እንደሆነ አያውቁም?ያለፈው እንኳን ቢያልፍ እንዴት ቀውሱን እያቀጣጠሉ እንደሆነ ምንም መረጃ የሎትም? እንዴትስ ለሚመሩት ህዝብ ብለው እረፉ አይሉዓቸውም?ለመሆኑ አሁን ባለው ሁኔታ ከፌደራል መንግስቱ ጋር እሰጣ ገባ ውስጥ ገብተው እንዴት የአብዛኛውን ተጋሩ ጥቅም ያስከብራሉ? እውነት በዚህ መልኩ አይደለም የአብዛኛውን ተጋሩ የኢፈርትን ህልውና  እንኳን ማስጠበቅ ይችላሉ ወይ?
የደኢህዲኗ ወይዘሮ ሙፈራያት 
እርሶ ወደ ደኢህዲን ስልጣን ከመጡ ክልሉ እየፈረሰ ነው።እሄንን እያደረጉ ያሉት ደግሞ የድርጅቶ ስራ አስፈፃሚዎች እና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ናቸው።ለመሆኑ ድርጅቱ አለ ወይ? ድርጅቱ እና ክልሉ ስፈርስ እርሶስ ምን አደረጉ?
ታከለ ኡማ 
ባህር ዳር መሄድህን ሰማሁ።ጥሩ ነው። ነገር ግን በዙሪያ ያሉትን ገበሬዎች ሄደሄ ጎበኘሃቸው ወይ ?
የባህርዳር እና የሸገርን ህዝብ  ከተራራቁ ማቀራረቡ ጥሩ ነው። ነገር ግን የሸገርን ህዝብ ከአከባቢው ህዝብ ጋር ማቀራረቡ አይቀድምም ነበር ወይ?እሄ እኮ ክቡር ፕረዝዳንቱ ያኔ ባህርዳር  ላይ ኢትዮጵዊነት ሱስ ነው ያሉ ቀን ተቃጠለ።በቃ ከዚያ በኃላ ምንም ቢደረግ የአንድን ሰው ክብደት አይጨምርም ።ይቀንልሳ እንጂ!!
በአጠቅላይ ከተማዋ ያልተደገመ  ኦርጂልና ሃሳብ ነው የጠማት!!በዚህ የጭንቅ ወቅት ለማስመሰል የሚደረግ ነገር ምንም አይፈይድም።ችግሩ ከዚያ በላይ ነው።
6 ለጀዋር መሃመድ
 
በየአከባቢው ህዝቡን እየሄድክ እያናገርክ ነው።በብዙ ቦታዎች ላይም ከየክልሉ ባለስልጣን ጋር እየተመካከርክ ነው።ነገር ግን ከምክክሩ እና ከውይይቱ በኃላ የሰማሃቸውን ችግሮች ምን ለማድረግ አሰብክ?ለመንግስት ለማቅረብ ወይስ እራስህ ችግሩ መፍትሄ እንዲያገኝ የሚታደርግበት እርከን አለህ?ወይስ እንደተለመደው ችግሮቹን መያዣ በማድረግ ለሌላ ዙር አቢዮት እየተዘጋጀህ ነው።እኔ ከሱም ችግር የለምኝ።
ከአቢዮቱ ማለቴ ነው። ነገር ግን ከአቢዮቱ በኃላ ምን ልታደርግ ነው?የምታስፈፅመው ፕሮግራም እና ማስፈፀሚያ እርከን (ፓርቲ) አላህ? ወይስ እንዲኖርህ ትልፈጋለህ? እየሰራህ ነው?
ከመጀሪያው ጀምሬ ካንተ አካሄድ ጋር አንድ መሰረታዊ  ልዩነት አለኝ። ነገሮችን structured በሆነ መልኩ አታስኬድም። ወይ ፓርቲ መስርተህ ፕሮግራም አውጥተው ህዝብ አደረጅተህ ለስልጣን አትታገልም።ወይም ቁመትህን ቀንሰህ በስርዓት አክቲቭስት አትሆንም ።ከድርጅት በላይ ለብቻህን ገዝፈህ ደስ ስልህ  ፀጉር ታስላጫለህ ፤ደስ ስልህ ደግሞ በየቦታው ዘመቻ ትከፍታለህ።
በአጠቃላይ ለዚህ ሁሉ ትላልቅ ውሳኔዎችህ በጎም ይሁን መጥፎ ውጤት  አንድም ቀን በስርዓቱ ተገምግመህ አታውቅም።ምክንያቱም በቃ ማዕከላዊ ሆነ ስራ አስፈሚ የለህም። የሚትወስናቸው ነገሮች ግን ከዚያ በላይ ናቸው። አንተም ከዚያ በላይ ነህ።
ልክ እንደ ቻይናው ማኦ ወይም ኢራኑ አያቶላህ ወይም እንደ አለፉት ንጉሶቻችን ውሳኔ ትወስናለህ እንጂ ለወሰንከው ውሳኔ ውጤት ስልንጣህ ከፍ (ወዴት ከፍ ይላል?) አይል ዝቅ አይል(ማን ዝቅ አርጎት?) ለዚያም ነው ሲቸግረን አያቶላ ያልነው።
እናም ወንድሜ በአጭሩ ወይ ድርጅት መስርት እና ፕሮግራም አውጥተህ ታጋል።በእውነቱ ቁመትህ ረዝሟል።
ይህ ቁመትህ ከዚህ በኃላ በዚሁ ከቀጠለ ልክ እንደ ባህር ዛፍ (በዙሪያው ያሉትን እፅዋት እና አዛዕርት እንደሚያቀጭጨው) ኦሮሚያ ውስጥ ተቋማት እንዳይገነቡ ያደርጋል።ወይም ያቀጭጫል ።
ለኔ ጥሩው አማራጭ እራስን ከንጉሳዊነት/አያቶላነት  ወደ ተቋምነት መለወጥ ነው።ያኔ ፕሮግራምህን አይተን  ወይ እንደግፈሃለን ወይ እንቃወመሃለን።አሁን ግን ቁመትህ አስቸግሯል ።
ልክ እንደባህር ዛፍ። ስልጣን ያባልጋል ።ተጠያቂነት ያሌለው ስልጣን ደግሞ በጣም ያባልጋል እንደሚባለው ነው። አንተ እኮ ምንም ተጠያቂነት ያሌለበት ብቸኛው ተፅዕኖ ፈጣሪ ፖለቲከኛ ነህ።
አሁን አንተን ለምትውስናቸው ውሳኔዎች ማን ይጠቃሃል? ምክንያቱም አድናቂ እንጂ ጠያቂ እንዳይኖርህ አድርገህ አደራጅተሃል።
 አንድ ነገር ልንገርህ
 ከላይ ብዙ ሰው ተችቻለሁ።ከሁሉም መዘዙ ያስፈራኝ አንተ ላይ ያሳረፍኩት ትችት ነው። ትችቱ ክፉ ስለሆነ አይደለም። ውሸት ስለሆነም አይደለም። ምክንያቱ ያ አይደለም። ምክንያቱ ያንተ አደረጃጀት አድናቂ እንጂ በኃላፊነት የሚጠይቅህ አይደለም።ሌሎቹ ይነስም ይብዛ ያንን አላቸው።በ1980ዎቹ እና ዘጠናዎቹ ኦነግም እንዲሁ ዓይነት ነገር ፈጥሮ እንድናደንቀው እንጂ እንዳንተቸው ከልክሎን ነበር።ያ ግን ምን አደረገለት? የሚታውቀው ነው።ያንተ ግን ከኦነግም ባሰ !!ኦነግ እኮ ቢያንስ ከላይ ያልናቸውን ነገሮች ነበሩት።እንዴት ከአይነኬ ድርጅት ወደ አይነኬ ግለሰብ ትሸጋገራለህ?አሁን ደጋፊዎችህ ቢያንስ እንዲህ ይልሉ።1ጀዋር እኮ ብዙ ነገር አድርጓል።2 ፀረ ኦሮሞዎች እየተቹት አይደለም ወይ እና ወዘተ የሚገርመው ለኦነግም እንዲሁ ተብሏል።
Filed in: Amharic