>

ነገ አብረን መኖራችን ላይቀር ዘንድሮ አንቃቃር!!!  (ስዩም ተሾመ)

ነገ አብረን መኖራችን ላይቀር ዘንድሮ አንቃቃር!!! 
ስዩም ተሾመ
ጦርነት ከጥንት ዘመን ጀምሮ ያለ፣ የነበረ እና ነገም ሊኖር የሚችል ነገር ነው፡፡ የእሱን አስከፊነትና አላስፈላጊነት እያነሱ መዘከርና መዘርዘር አያስቀረውም፡፡ የእርስ-በእርስ ግጭትና ጦርነትን ለማስቀረት ምንም ያህል ጥረት ብታደርጉ እንደ ህወሓት ያለ በዘረኝነት የናወዘና በጥላቻ የታወረ የፖለቲካ ቡድን አጋጣሚ ጠብቆ ወደ ስልጣን ይመጣል፡፡ ከዚያ በኋላ ሀገርን በዘረፋ በእንብርክኳ ያስኬዳል፣ በዜጎች ላይ ለመፈፀም ቀርቶ ለመስማት የሚዘገንን ግፍና በደል ይፈፅማል፡፡ እንዲህ ያለ የፖለቲካ ቡድን የተጠነሰሰው ከበታችነት ስሜትና ድንቁርና ስለሆነ መቼም ቢሆን አያድግም፣ አይሻሻልም፣… እድሜ ልኩን በትቀቅለው አይበስልም!! እነሱን ከጥላቻና የበታችነት ስሜት አውጥቶ የሃሳብና የሞራል ልዕልና ማጎናፀፍ በፍፁምአይታሰብም፡፡
በመጨረሻ በመጡበት መንገድ ከስልጣን ለመወገድ ሲቃትቱ ታገኛቸዋለህ፡፡ በትተዋቸው አይተውህም፣ ብትንቃቸው ሆነ ብታከብራቸው ለእነሱ ልዩነት የለውም፡፡ ምክንያቱም የአንተ ንቀት የሚገባቸው ለራሳቸው ክብር ሲኖራቸው ነው፤ አክብሮትህ እንዲገባቸው በቅድሚያ ለራሳቸው ክብር ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ለራሱ ሆነ ለሌሎች ክብርና ፍቅር የሌለው የዱኩማኖች ስብስብ እስካለ ድረስ ጦርነትን ጨርሶ ማስወገድ ሆነ ማስቀረት አይቻልም፡፡ ስለዚህ ጦርነትን ለማስቀረት ዘወትር ስትታገል እንደ ህወሓት ያለው ደግሞ ጦርነት ለማስነሳት በፆምና በፀሎት ይተጋል፡፡ በዚህ መሠረት ጦርነትን ብትሸሸውም የሚፈልጉት እስካሉ ድረስ በድንገት ሊቀሰቀስ ይችላል፡፡ በመሆኑም ወደ ጦርነት ከመግባትህ በፊት ከግንዛቤ  ማስገባት ያለብህ አንድ መሠረታዊ መርህ አለ፦ <<በጦርነቱ መካከል ነገም ከዛሬ ጠላቶችህ ጋር አብረህ እንደምትኖር እያሰብክ>> ይላል፡፡
የጠላትን ክፋትና መጥፎነት እያዩ በጥላቻ መንደርደር ከዕልቂት በተረፈ ሌላ ትርፍ የለውም፡፡ ህወሓቶች በሆኑትና በወረዱት ልክ መውረድ ለእኛ ሽንፈት ነው፡፡ እነሱ የዘረፉት ብር እና የፈፀሙት ግፍ ካሳበዳቸው ዕዳው የራሳቸው ነው፡፡ “ሲጀመር ካበደው በላይ አብሮት ያበደው #ሰይጣን ሆነ!” የሚሉት ዓይነት እንዳይሆን የህወሓቶችን ቀረሮቶና ሽለላ ችላ ብሎ ነገሮችን በትዕግስት ማለፍ አለብን፡፡ እነሱም መወደቃቸው ላይቀር፣ እኛም ከትግራይ ህዝብ ጋር አብረን መኖራችን ላይቀር ዛሬ ላይ መጣላትና ደም መቀባባት የለብንም፡፡ ነገ አብረን መኖራችን ላይቀር ዘንድሮ አንቃቃር!!!
Filed in: Amharic